Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 9

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 9

የሸገር ወጎች 9

  እነዚህ እና እነዚያዎቹ

 
Tales Of Sheger‹‹ አይ አጩሌ መቼም አታመጣው የለ፡፡ ደግሞ ምን መዓቱን ይዘህብን መጣህ›› ብለህ ባትጠይቀኝም ልትጠይቀኝ እንዳሰብክ ገምቼ ልቀጥልማ ….ዲያስፖራው ወዳጄ እኔ ድብን ልበልልህ ነው የምልህ…ያሉትም የሄዱትም ሁሉ ነገራቸው አንድ ቢሆንብኝ…ግራ ቢያጋባኝ እኮ ነው መቼም ተፈረንጅ ሀገር ያለው ሰው ወሬ አያጣም ብዬ ልጠይቅህ መነሳቴ፡፡

እኔ የምለው ግን ያ ሰሞኑን የላክነው ዲቪ በሰላም ደርሶ ይሆን? አኸ ከባህር ማዶ ‹‹ አጩሌዬ ና እስቲ እንዲህ የምትወዳትን አሜሪካ ተመልከታት ብሎ የግብዣ ወረቀት የሚልክ ቢጠፋ ይኸው የሰማዩ የምድሩ ፈጣሪ አይቁጠርብኝና ‹‹አሁንስ ተስፋዬ ማነው እግዚያብሔር አይደለምን?›› የሚለውን ጥቅስ ከግድግዳ ላይ አውርጄ ‹‹አሁንስ ተስፋዬ ማነው  ዲቪ አይደለምን?›› በሚል አጽፌ ከሰቀልኩ ዘንድሮ ድፍን ሃያ ሶስት አመታት ተቆጠሩ (እናንተ ሞኞች ደግሞ ይህንንም ፖለቲካ ነው በሉ አሉዋችሁ!) ቂ..ቂ..ቂ ለነገሩ ተውት ኮረሪማና ኮሰረት አሜሪካንን በረገጡበት ጊዜ ከሰልና ጀበና ግሪን ካርድ ባገኙበት ዘመን እኔ ይኸው ….ባካችሁ ሆድ አታስብሱኝ (ለመጻፍ ስለማይመች እንጂ አጩሌ አምርሮ ማልቀሱን አንባቢያን ታስቡ ዘንድ አደራ ብያለሁ)

መቼም ፈጣሪ አይቁጠርብኝ ብዬ አንዴ ለምኜዋለሁና በጥንት ዘመን የተፈጠረ አንድ ታሪክ ሹክ ብያችሁ ወደ ጨዋታችን እንለፍማ፡-

በጥንቱ ያኔ በደጉ ዘመን ራስ ሃይሉ በጣም የሚወዱት ባለሟል ነበራቸው፡፡ ታዲያ ሹመት ቢሰጡት ከእርሳቸው ገለል እንደሚልና እንደሚርቃቸው ስለተገነዘቡ ‹‹ዛሬ ሹመት ልሰጥህ ነበር ግን እግዚአብሔር ሳይልልህ ቀርቶ ሹመቱ ለቀኝ አዝማች …ለፊታውራሪ… ለብላታ…እገሌ ተሰጠ›› እያሉ በየጊዜው ይነግሩታል፡፡ ታዛዡ ሎሌም ከቀን ቀን እግዜር ብሎ ሹመቱን ይሰጡኝ ይሆናል በሚል ቢጠባበቅ እንደተለመደው ‹‹እግዚአብሔር አልልህ ብሎ የዛሬ ሹመት ለእገሌ ተሰጠ›› ይሉታል፡፡

ባለሟሉ ምርር ቢለው ቀን ጠብቆ በሕማማት ሳምንት በዕለተ አርብ (የስቅለት ቀን) ወደ ራስ ሃይሉ ቤተመንግስት ቀጥ ብሎ በመግባት ምን እንዳላቸው ሠምተህልኛል?…‹‹ጌታዬ ዛሬ እየሱስ ክርስቶስ ወይም እግዚአብሔር ተሰቅሏልና በሌለበት ሹመቱን ይስጡኝ›› ብሎልህ እርፍ..ቂ..ቂ.. እኛም እንግዲህ አናታችን ላይ የተከመሩትን መቼ ይሆን የምትለቁን ብንላቸው እሱ የሌለ ቀን እንደማይሉን ምን ማረጋገጫ አለ ብለህ ነው?

ውይ…ውይ ዲያስፖራው ወዳጄ እኔን ሞት ይርሳኝ ሰላምታውን ዘነጋሁት አይደል? ለነገሩ እንደልብህ መናገር፣ መጻፍ እና መጮህ በምትችልበት ሀገር እየኖርክ ሰላምታን መጠየቅ ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ነው፡፡ መጠየቅስ ያለብኝ እኔ ነበርኩ ለነገሩ እኔንም ብትጠይቀኝ ‹‹ ጤፉ ከደጃፍ ..ወተቱ በቧንቧ…ሜትሮው በመኝታ ቤቴ አቋርጦ ነው የሚያልፈው ከማለት አልመለስም (ትቀልዳለህ እንዴ እኔ እኮ ያለሁት ሸገር ነው፡፡ ሆሆይ በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ አሉ እትዬ ሻሼ፤ ወይ ዲያስፖራው ወዳጄ ያ ሁሉ ጋዜጠኛ ፋይሉ ዲሌት ተደርጎ ቂሊንጦና ዝዋይ የገባው ታንክ እና ጦር አሰልፎ መሰለህ እንዴ? ደግሞ እንደፋራ ታዲያ በምንድን ነው? ብለህ እንዳትጠይቀኝ!! ደፋር! አትጠይቀኝ እያልኩህ ትጠይቀኛለህ እንዴ?

ለማንኛውም ዛሬ ስለነዚህ እና እነዛኛዎቹ ቀዳዳ ከመጀመራችን በፊት ሰሞኑን የምርጫዋን መዳረስ አስመልክቶ ሸገር ላይ የተፎገረች አንድ ጨዋታ ባቀርብልህስ? አንድ ቻይናዊ፣ አሜሪካዊና ኢትዮጵያዊ መንገደኞች በድንገት ይገናኙና እየተጫወቱ ከቆዩ በሁዋላ የሀገር እድገትን በተመለከተ ሲነጋገሩ ግን የማያግባባቸው ነገር ይፈጠርና መጨቃጨቅ ይጀምራሉ፡፡

ቻይናዊው፡-

‹‹የኔ ሀገር ዓለም ውስጥ ካሉ ሀገራት በሙሉ በከፍተኛ መጠን እያደገችና እየዘመነች ያለችው የኔ ሀገር ናት፡፡ ለምሳሌ በኔ ሀገር ምርጫ ከተደረገ በኋላ በሚቀጥለው ቀን አሸናፊው በግልጽ ይታወቃል፡፡››ይላል…

አሜሪካዊው፡-

‹‹ ይሄማ በጣም ውሸት ነው፡፡ ሊያውም እልም ያለ ነጭ ውሸት፡፡ በኔ ሀገር እኮ ምርጫ ባደረክበት በዛው ቀን ነው አሸናፊውን የምታውቀው፡፡ እና እኛ እያለን አንደኛ እኛ ነን ስትል አታፍርም? ›› ሲል ቻይናው ላይ ያፈጥበታል፡፡

ኢትዮጵያዊው፡

ኢትዮጵያዊው ዝም ብሎ ሲሰማ ቆየና…‹‹እናንተ ግን ይቺን ትልቅ ነገር አድርጋችሁ አድገናል ምናምን እያላችሁ ትደነቃላችሁ እንዴ? የኔ ሀገር አለች አይደል እንዴ ገና ምርጫው ሳይከናወን አሸናፊው የሚታወቅባት፡፡ ምድረ ቱልቱላ ሁላ ብሎ ቁጭ፡፡ ይህቺ ናት ዴሞክራሴ አሉ ሰውዬው፡፡

እናልህ ወደ ጉዳያችን ስንመለስ ባለፈው እዚህች መጽሔት ላይ የዋና አዘጋጁ መልዕክት ላይ ‹‹ኢንቬስተሩ ደራሲያን›› ስለተባሉት እነዛኛዎቹ እና እነዚህኛዎቹ ሰዎች ያነበብኳት ግርም ብላኝ እና እዚህ ሸገር ላይም መነጋገሪያ የሆነች ጉዳይ ብትሆን እናውጋባት ብዬ እኮ ነው፡፡ አኸ በመንግስት ስልጣን ላይ ቁጭ ብለው ‹‹በሳንጃ መቀመጫውን ውጋልኝ…ከርቸሌ ወርውርልኝ!››  እያሉ ሲፎክሩብን ‹‹የምርጫ 97 አደገኛ ቦዘኔና አድሃሪ የአብዮታችን ጠላት ›› እያሉ ስም ሲለጥፉብን የነበሩ፤ ምን እሱ ብቻ እኛ በሄድንበት እንዳናያችሁ እያሉ ለስደት ዳርገውን የነበሩት ሹማምንት ሁሉ ካለው መንግስት ጋር በተጎራበጡ ወይም ዋናው አዘጋጅ እንዳሉት ላለው ስርዓት የሚያዋጡት ሲያልቅባቸው ተጠርገው ሲጣሉ በደም እንዳላጠቡን አሁን ደግሞ በደራሲ ስም ኪሳችንን ሊያጥቡ ‹‹የእነ እንቶኔ ትሩፋት፣ እኔና የትግል ጉዞዬ፣ ኢትዮጵያና የእኔ እርምጃ›› ምናምን የሚል ዳጎስ ያለ ነገር እየጻፉ አዲስ ኢንቨስትመንት መጀመራቸው ኢትዮጵያውያንን አይደለም የልማት አጋሮቻችንን ቻይኖችንም ሆዳቸውን ይዞ ያሳቀ ነገር ሆኖዋል፡፡

እኔ የምለው ያኔ ወንበሩ ላይ ቁጭ ብለው ‹‹ውጋ ንቀል!›› እያሉ ሲያዙ የነበሩ ሁሉ ዛሬ ምን ታይቷቸው ይሆን ሰብሰብ ብለው ደራሲ ሆነናል እና የምናውቀውን እንንገርህ የሚሉን? ያኔ የት ሄደው ነበር? መቼም ይቺን ሙድ ከመንግስቱ ሃ/ማርያም ጀምሮ ከአሁኖቹም አብዛኞቹ እየተከተሏት ያለች አዲስ ፈጠራ መሆኗ ኪሳቸው ባዶ ሳትሆን የፈጠሯት ቢዝነስ እንደሆነች ሀበሻ ያላወቀ መስሎአቸው ከሆነ በእውነት ተሸውደዋል !!!!ኤጭ…ለዚህ ለዚህ ታምራት ላይኔ በስንት ጣዕሙ ‹‹ ኢየሱስ ጌታ ነው››! በቃ ግልግል፡፡ አሜን! ሀሌ ሉያ!!!!

የእነዚህኞቹ እኮ ወይ እውነቱን አይናገሩ እራሳቸውን እንደመላዕክት አድርገው ጥፋቱ የእነ እገሌ ነው ብለው ጣት መቀሰራቸው ሳያንስ እኔ ፍጹም ነኝ ብለው ራሳቸውን ከደሙ ንጹ ማድረጋቸው አሳፋሪም ….አስፈሪም ነው፡፡ አዳሜ የፈለግሽውን ብትይ በያንዳንዱ ልብ ውስጥ ያስቀመጥሽውን ክፋት ይልቁኑ በይቅርታ ማንጻት መፍትሔ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሆሆሆ….ቀኝ ቂጣችንን በሳንጃ የወጋ ሁሉ ከግራ ኪሳችን ገንዘብ ሲወስድ ግርም አይልም ወዳጄ ?

ለማንኛውም እኔ እንደነሱ ክፉ አይደለሁም ከዚህ በላይ ማለትም አይገባም፡፡ ግን ከሰሞኑ ከወደናንተ ሀገር የደረሰኝ መልዕክት ግርም ብትለኝ ላካፍልህ ወደድኩ፡-

አንዱ ሀበሻ ከላይ የተዘረዘሩትን መጽሐፍት አይነት የጻፈ አንድ የድሮ ሹመኛ የአሁን ኢንቬስተር ደራሲን ያገኘው እና ‹‹ ምናለ ይሄን ህዝብ እንደ ጥገት ላም ገንዘቡን ከማለብ ብትቆጠቡ? ›› ሲል ጥያቄውን ያቀርብለታል፡፡ ኢንቬስተሩ ደራሲ እንዲህ ሲል መለሰ አሉ፡፡ ‹‹ እንደ ከብት የምነዳው ጅል እስከሆነ ድረስ እንኳን እንደ ጥገት ላም ማለብ እንደጠቦት አጋድሜ ባርደው አንተ ምን ጥልቅ አደረገህ?›› እ…ር…ፍ! ማለት ይሄ ነው፡፡ በል ወዳጄ እንደከብት ከመነዳትም እንደጠቦት ከመታረድም ይሰውረን አሜን በል! እንደ ጥገት መታለብ ከጀመርንማ ቆየን ቂቂ..ሃሃ..ሃሃ…( አሁን ይሄ ምኑ ያስቃል)

ያው እኔ አጩሌ ነገር ማክረር እንደማልወድ እንኩዋን ናፍቆትን የሚያነብ ቀርቶ ራሳቸው ኦባማ እራሱ ማወቃቸውን በሚሼል በኩል ስለሰማሁ ለዛሬ ለስንብት በእነዚህም በነዛኞቹም ላይ ትንሽ አልምጠን ብናልፍስ? ድንቅ ሃሳብ! ያው በፊት በፊት ይወጡ የነበሩ እና አሁን አሁን እየወጡ ያሉ ስሞች አንዳንዴ ፈገግታን ይጭራሉ እነሆ ጥቂቱን፡-

በእነዚያኛዎቹ ዘመን

ደርጉ ገነነ

ሽብሩ ነገሰ

ለገሰ ጨፍጭፌ

አብዮት ገስግስ

ሰፈራ መጣብህ

አሰብ ድንበሬ

መንግስት ደምስሳቸው

ቀይሽብር በላይነህ

አንድነት ኢትዮጵያ

ቀይ ኮኮብ ቀለጠ እና የመሳሰሉት በዋናነት ተጠቃሽ አብዮታዊ ስሞች ነበሩ፡፡

 

በእነዚህኛዎቹ

ግብሩ ጫንያለው

አሰብ ተስፋዬ

ፌዴራል እርገጤ

አኬልዳማ ታዬ

አምስት ለአንድ አደራጀው

ሙስና ገነነ

ኢቲቪ ሽብሩ

ጭቆናው አየለ

ቅንጅት ደምመላሽ

ምንድነሽ ደሞዜ

የመሳሰሉት ተጠቃሽ ሆነው እንዲያውም አንዳንድ የቻይና ዜጎች ዣንግሊ፣ ሊንግያን፣ ኒሆ ያዥን የመሳሰሉ ስሞቻቸውን በእነዚህ ልማታዊ ስሞች ለመቀየር እያሰቡ እንደሆነ ኢቲቪ ዘግቧል፡፡ ለዝርዝሩ እኔ የለሁበትም!!!

በስተመጨረሻ  ይህቺን ደግሞ አንዱ ክፉ ወዳጄ ያጫወተኝ ነች፡፡ ያኔ ጳጳሱ በጠና ታመው በማጣጣር ላይ እያሉ ከመሞታቸው በፊት ሁለት ባለስልጣናት (ማን ስም ጠቅሶ በአሸባሪነት ይወነጀላል ወዳጄ?) አጠገባቸው እንዲሆኑ እንደሚፈልጉ ለሆስፒታሉ ሀኪሞች ይናገራሉ፡፡ ሀኪሞቹም በፍጥነት እንደተባሉት ያደርጉና ሁለቱ ባለስልጣናት ጳጳሱ ጋር ይደርሳሉ፡፡

ጳጳሱም የሙት ሙታቸውን እያጣጣሩ ባለስልጣናቱ ከአልጋቸው በስተግራና በስተቀኝ እንዲሆኑ ያዛሉ፡፡ ባለስልጣናቱም ጳጳሱ በመሞቻቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ማግኘት የፈለጉት እነሱን በመሆኑ ክብር እየተሰማቸው እንደተባሉት ካደረጉ በሁዋላ ‹‹አባታችን ብዙ ብጹአን አባቶች እና ጻድቃኖች እያሉ በዚህ በመጨረሻ ሰአትዎ እኛ አብረንዎት እንድንሆን  ለምን ፈለጉ?›› ብለው ቢጠይቋቸው ጳጳሱ እያጣጣሩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ሞቴ ልክ እንደ ክርስቶስ ከሌቦች እና ወንበዴዎች መሀል እንዲሆን ፈልጌ ነው››  ሃሃ…ሃሃ…በል ወዳጄ ከዚህ በላይ እንደለመድከው አታስለፍልፈኝ ሆሆይ…

‹‹በለፈለፉ በሽብርተኝነት ይከሰሱ ›› አለች አያቴ፡፡

 

 ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top