Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 8

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 8

የሸገር ወጎች 8:

 Tales Of Sheger እንዴት ከርመሀል ወዳጄ? ዲያስፖራው ወዳጄ ሙት ነው የምልህ እኔ ካንተ ከወዳጄ ሀሳብና ናፍቆት በስተቀር በጣሙን ደህና ነኝ፡፡

እንደው መቼም ሰሞኑን እዚሁ ሸገር ላይም ሆነ እናንተ ጋርም ወሬው ሁሉ እኚያ ‹‹ ደክሞኛል፣በቃኝ፣ ማረፍ ፈልጋለሁ›› ብው ኢቲቪ ላይ ስለተናገሩት ሰውዬ ከሆነ ሰነባበተም አይደል? ሰውዬው ግን እውነት እልሀለው ግራ አጋቢ ቢጤ ሳይሆኑ አይቀሩም ( ወዳጆቻቸው እንዳይሰሙኝ ብቻ ) አሃ ከወር በፊት ‹‹ ወጋ! ንቀል!›› ባሉበት አንደበታቸው ‹‹ ማረፍ አማረኝ!›› ምናምን ሲሉ ሼም አይዛቸውም እንዴ?

እኚህ ጎረቤቴ አቶ ሞላ ‹‹ ሰው ምን ነካው? በተደላደለ ሀገር እየኖረና እየተንፈላሰሰ ምን በወጣኝ ብሎ ነው እዚህ ከተጣላናቸው ጎረቤቶቻችን ጋር ቡና ሊጠራራ በየመን በኩል የሚመጣው?›› ብለው በቀደም እለት ፈገግ አስደርገውኛል፡፡ እርግጥ ነው ‹‹ እንኳን ከአሜሪካ ከመንግስተ ሰማያትም ቢሆን አመጣሀለው!›› የሚሉ ስንት ሳጅኖችን ያፈራችን ሀገር እንዲህ በቀልድ መመልከታቸው ሰውዬው አራድነት የራቃቸው ቢሆን ነው›› እያሉ የሸገር ሰዎች እያንሾካሾኩልህ ነው፡፡ ለነገሩ አራዳስ እዛ እናንተ ጋር ያለት ቁንጮው ሰውዬ ናቸው በማለት ባሉበት ጸሀዩ መንግስታችን የሞት ፍርድ ጀባ ሲላቸው የሸገር ስራ ፈት ደግሞ የ ‹‹ አራድነት ›› ማዕረግን ሸልሟቸዋል፡፡

‹‹ ሳይያዙ ነው ማምለጥ ሳይያዙ
ከተያዙ በኋላ ብዙ ነው መዘዙ›› አለ ያ አውቆ አበድ አንዳንዴ ከጤነኛውም እኮ ያበደው የሚሻልበት ጊዜ መምጣቱ እንዲያው ግርም አይልህም? ሰውዬው ደግሞ በቲቪ ያሉትን፣ የዘረዘሩትን በገዛ ጆሮዬ ሳዳምጥ አንዲት የቆየች እውነት አዘል ቀልድ ትዝ አለችኝ አድምጠኝማ፡-

በዘመነ ደርግ ነው አሉ አንዱ መንገድ ላይ አላፊ አግዳሚውን ‹‹ ወዲህ በሉ›› እያለ የሚቀፍል ወጣት ነበር፡፡ በዚህ ሰው የፖለቲካ ‹ፉገራ› ፈገግ የሚሉም ሳንቲም ጣል ያደርጉለታል፡፡ ታዲያ በአንዱ ቀን‹‹ ኢሰፓአኮ ባዶፓኮ›› እያለ ሲቀልድ ካድሬዎች አይን ውስጥ እንደገባ ይነቃና ማምለጫ ዘዴ ፈጠረ፡፡ የነበረው አንድ አማራጭ ደግሞ መንጌን ማወደስ ነበር፡፡ ታዲያ‹‹ የሰው ጥራቱ እንደመንግስቱ›› እያለ ከተማውን አቀለጠው፡፡ ይህም ዘዴ ከተደገሰለት ሞት ቢያስመልጠውም ከእስር ግን አላተረፈውም፡፡ የማታ ማታ በሚሊሻዎች ተይዞ ታሰረ፡፡ እዛው አንድ ሁለቴ ሾጥ ሲደረግ እንዲህ አለ አሉ፡- ‹‹ እኛ ያልነው ለፉገራ እነሱ ግን ለመግደል ሙከራ…›› ቂ ቂ ቂ ቂ….

ታዲያ ወዳጄ የሰሞኑን ሁኔታ ለታዘበ ከየመን ለኢትዮጵያ የተበረከቱትን ሰውዬ ‹‹ ማረፍ እፈልጋለሁ!›› ልብ ብሎ ላዳመጠ ‹‹ እኛ ያልነው ለፉገራ…!›› የምትለዋን የዘመነ ደርግ ቀልድ ቢያስታውስ ይፈረድበታል ትላለህ?

መቼም ባለፈው በዚችው ቦታ ላይ ያስተዋወቀኩህን አባቴን አትረሳውም አይደል? ታዲያ ሲፈጥርበት የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ብቻ ሳይሆን አምላኪም ጭምር ነው፡፡ እኚህ ከእናንተ ወደ የመን ከየመን ወደ እኛ የመጡት ሰውዬ ደግሞ የገዥውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ብር ላይ ‹‹ የብሄራዊ ባንክ ገዥ›› የሚለውን ጽሁፍ ሲያዩ ፣ የሰማይና ምድር ገዥ የሆነውን ፈጣሪ…ተብሎ ሳያልቅ‹‹ ገዥ›› የሚለውን ቃል ከገዢው ፓርቲ ጋር እያገናኙ ነስር ይቀድማቸዋል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እናቴ በበኩሉዋ የሰውዬው አላማ ደጋፊ ትሆን( ወይ አባቴ ደክሞበት ይሆን እንጃ!) ሰውዬውን አጥብቃ ትወዳቸዋለች ሳይሆን ( አባቴ እንዳይሰማ እንጂ ታፈቅረዋለች!) በቲቪ በቀረቡ ጊዜ ሁሉ አይ ወንድነት፣አይ ቁመና፣ አይ ጸጉር ማለቷን የሰማው አባቴ እንደያውም በአንድ ወቅት ምርር ብሎት ‹‹ አንቺ ሴትዮ ይሄን ‹ አሸባሪ› እንደዚህ እንደምታደንቂ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ብታደንቂ ኖሮ ኮንዶሚኒየም ተሰጥቶሽ እኔንም እዚህ ከቀበሌ ቤት በገላገልሽኝ ነበር ሲል ተሰምቷል፡፡ ‹‹ አልያ ትገቢያታለሽ!!›› ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር፡፡

እኔ ደግሞ ገዥው ፓርቲንም ሆነ በመቶ ብር ላይ ገዥ ተብሎ መጻፉን ስለማላውቅ ( የት አግኝቼው ብለህ ዲያሥፖራው ) ስለ ገዥው መደብ ያለኝ እውቀት በጣም ውሱን ነው፡፡ ቆይ አሁን ምን የሚያስቅ ነገር ተናገርኩ? መቶ ብርን አላውቅም ማለቴ ነው እንዲህ ያስገለፈጣችሁ? እኔ የምለው የአርባ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ መቶ ብር አለማወቅ ብርቅ ነው እንዴ? እንኳን እኔ እኛ የቀድሞው ጠቅላዩ ሰውዬስ የ100 እና 50 ብር ልዩነትን አያውቁም ነበር ሲባል ሰምተን አምነን የለ እንዴ? ታዲያ ምን እኔ አጩሌ ላይ ታካብዱታላችሁ?

ወጣም ወረደም ከሰውዩው መያዝ በላይ ያሳሰበኝ አሜሪካ አሪጎን መጥተው የጠፉት አትሌቶች ጉዳይ ነው ያሉት ሚስተር ኦባማ ሌላውን ጉዳይ ላሽ ብላችሁ አትሌቶቹን ፈልጋችሁ ለየመን ስጡልኝ አሉ ተብሎ እዚህ ሸገር ላይ ቀላል መቀለጃ ሆኑ መሰለህ? የእሳቸውስ እሺ የእንግሊዝ መንግስት አትሌቶቹን የሚፈልግ አንድ ባህር ሰርጓጅ መርከብ እልካለሁ ማለቷም እየተነገረ ነው አልገባ አላቸው እንጂ ባህር ሰርጓጅስ መላክ ወዲህ ነበር‹‹ አሳው ከባህሩ በታች እየዋኘ ነው›› እንዲሉ የሲሲሊ ሰዎች፡፡……… ደግሞ ለዚህ ትርጉም ጣሊያን ግባ አሉህ…ሰምተሀል ባክህ!!!!

የምንወዳት ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top