Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 7

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 7

የሸገር ወጎች 7:
ኃይሌ ገ/ስላሴ ለፕሬዚዳንትነት … ሰራዊት ፍቅሬ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት?  

Tales Of Sheger

Tales Of Sheger

ጆሮ አይሰማው የለ ይኸው ሰማን፣ አይን አላይም አይል ይኸው አየን ‹‹ጉድ በል ጎጃም አማርኛ አስተማሪ ከ… መጣልህ›› አሉ ሴትዬዋ ቢጨንቃቸው? ምድረ የሸገር ሕዝብ ደግሞ ‹‹ጉድ በል ሸገር ሙሰኛ ከ…ተገኘልህ›› ሲል ሰነበተ፡፡ ውይ… ውይ… ወዳጄ እኔን ሞት ይርሳኝ፡፡

እኔ ሠራዊት ዛሬ መላው የኪነጥበብ አፍቃሪና መላው የእኔ አድናቂ በእውነት ያገለግለናል፣ ጥበቡን ከመቶ ፐርሰንት በላይ አሳድጋት… የጥበብ ንግዱን …. ይቅርታ የጥበብ እድገቱን ያሳየናል ብላችሁ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዳገለግላችሁ ስለመረጣችሁኝ እጅጉን አመሰግናለሁ፡፡ ማመስገን ብቻ አይደለም ለአንድ አገር እድገት ፎቅ፣ መንገድና ችግኝ ተከላ ብቻ ሣይሆን ጥበብን ትልቅ ዋጋ አላትና በዚህች ታላቋ የጥበብ ስም ምዬ ላገለግላችሁ ቃል እገባለሁ፡፡ …

ቸብ …..ቸብ …. ቸብ .. ደስ ሲል ፡፡ መላው የጥበብ አፍቃሪ ብቻ ሣይሆን ዘወትር በኢቲቪ ማስታወቂያ ላይ እያየው የሚያደንቀው ሕዝብ ሁሉ የቃለ መሃላውን ፐሮግራም በኢቲቪ ውይ አበዛው ልክ እንደ አሪፍ ፍቅረኛ ኢቲቪ ከአፌ አልጠፋ አለኝ እኮ/ እናም በቀጥታ ስርጭት እየተከታተለ በተስፋ ሲቦርቅ።

እውነት ግን ሰርሽ ለምን አትወዳደርም ኃይሌ ይኽው ፓርላማ ገብቶ ለፐሬዝዳንትነት ሊወደዳደር አይደል ምን ልዩነት አላችሁ፣ እሱም ዓለም አቀፍ እውቅና ቢኖረውም አንተ በሀገር ውስጥ ከ-እስከ የማይባል እውቅና ተጎናፅፈሃል፡፡ የአምባሳደር ሱፍህን ግጥም አድርግና ውይ ይቅርታ ደሞ ሳላዲን ሰይድ ለካስ ተረክቦሃል፡፡ እውነቱን ነው መተካካት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጊዜ የፊልም ተመልካቾች አዲስ ፊት ናፈቀን አይደል የሚሉት፡፡ እናም ቂቅ ብለህ ሀብትህን ከሙስና በፀዳ መልኩ እንዳፈራህ ገልፀህ በቅን ልቦና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ንገረው ፡፡ በቅን ልቦና እሱም በነቂስ ወጥቶ ይመርጥሃል፡፡

ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድመው ጠቅላይ ማኒስትር መለስ ዜናዊ ጎን ያኔ ተቀምጠህ ስትታይ ያለህ ግርማ ሞገስ ልዩ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የጥያቄ አወጣጥ ፕሮግራሞችና ጠያቂዎችን ተራ ስታስይዝ ማዳላት አይታይብህም፣ ድርሰትህስ ቢሆን ምን ይወጣለታል፣ ደራሲው በወረቀት ምክንያት ሲሰደድ ተዋናዩ የሚበላው አጥቶ መድረክ ላይ ሲወድቅ በምሳሌ ያቀረብከውን ዝግጅት በቤተ-መንግስት ግቢ ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እኩል ቁጭ ብለህ በማየቴ የእውነት ትልቅ ክብር ይሰማኛል፡፡

ያኔ አንተ በፃፍከው ድርሰት አይደል እንዴ አሁን የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ተስፈንጥሮ 100 ፐርሰንት እና ከዚያ በላይ አድርጎ ለዚህ የበቃው። ማን እንዳንተ ፃፈ፣ እነ ጋሽ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ እነ ጌትነት እንየውና ሌሎች መች ይህንን የሚያክል ድርሰት ፃፉ።
መቼም በርግጥ ምቀኛ አይጠፋምና በማግስቱ ፕሮፖዛል ይዞ ሄደ ብለው ሊያሙህ ይችላሉ። ሙት አትስማቸው ሰው ድሮም የማያገኝውን ይመኝና ሲያጣ ስም ያጠፋል ፡፡
ግን እስኪ አንወሻሽ፡- ያኔ ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጎን ስትቀመጥ እኔስ መቼ ነው ጠቅላይ ማኒስትር ሆኜ የኢትዮጵያን ኪነጥበብ ብቻዬን የምጠቀልለው ብለህ አልተመኝህም ውይ አታደርገውም አንተ ምን በወጣህ፡፡

ግን እውነት ለምን አትወዳደርም ሰማያዊ ፈረስ ብለህ በመፃፍህ እንደ ነብይ ተቆጠርክ /ምቀኞች ድርሰቱ የሱ አይደለም ገዝቶ ነው ቢሉህም / ምቀኛ ድሮም አያልፍለትም ብለህ ለምን አትወዳደርም 2007 ሩቅ አይደለም፡፡ እስከዚያ «ቀይ ፈረስ፣ ጥቁር ፈረስ፣ ነጭና ቢጫ ፈረሶች» እያልክ ቅልብጭ ያለች ፕሮፖዛል እያዘጋጀህ ፊልም ብትፅፍ የእውነቴን ነው የአራት ኪሎን ባዶ ቦታ /የፈረሰውን/ ወርቅ አንዲዘንብበት የሚያደርግ ጥናት አለኝ ብትል በቃ ለሰማያዊ ፈረስ ነብይ የተባልክ ለዚህኛው ደግሞ መልአክ መባልህ የማይጠረጠር ነው፡፡

ይሄኔ እድሜ ለዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዝናህን ከዳር እስከ ዳር ያራግፉትና /ይቅርታ ያራግቡትና/ ዝናህ ከኃይሌ እኩል አልሆነም፣ በቃ እውቅና ዓለም አቀፍ ከሆነ ደግሞ ለፕሮፖዛል ማን ብሎህ በዓለም ላይ ወርቅ አዘንባለሁ ብለህ ደግሞ ከነ ኦባማና ከሌሎች ጋር እየተቀጣጠሩ እራት መብላት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ላንተም ለኛም ክብር ነው፡፡

ግን የእውነት እስኪ አስበው ለምን አትወዳደርም? መቼም በቃላት አጠቃቀም አትታማም፡፡ ምቀኞች የሰራዊት ድርሰቶች በቃላት የመጠቁና በታዋቂ ተዋንያኖች የታጨቁ ናቸው፡፡ ግን ታሪካቸው ባዶ ናቸው ይላሉ፡፡ ተዋቸው ምቀኛና እንትን ከጀርባ አይወርድም ብለህ ናቃቸው፡፡ በኋላ እስኪንቁህ ድረስ …. ይቅርታ በኋላ እስኪያውቁህ ድረስ፡፡ አሁንም ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአማርኛ ቋንቋ ክህሎታቸው ምን ያህል የበረታ መሆኑን ሁሉም ያውቃል፡፡ አንድ አዲስ ቃላት ወርወር ያደረጉት እንደው ከላይ እስከ ታች ከፓርላማ እስከ ወረዳ ቀበሌ ድረስ ያሉት ሹማምንቶች የሚያጋድሙት ያቺን ቃል ነው፡፡

ታዲያስ አንተ ምን ያንስሀል ብቻ ተወዳድረህ አልፈህ ጠ/ሚኒስትራችን ሁንና ያተለመዱ ቃላትን ጣል አድርግና ከምሁር እስከ መምህር ከፕሮፌሽናል እስከ አማተር ያንተን ቃላት እንደ ውዳሴ ማርያም ይደጋግም፡፡ ግን በዚህ መሃል ሰራዊት የነጋዴ እንጂ የጥበብ ነፍስ የለውም ቢሉህ ለደቂቃ እንዳይሰማህ፡፡ ምቀኛ ሳይበላው ያካል፣ በቃ እርሳው፡፡
እኔ በጣም አድናቂህ ነኝ፡፡ መተወን ብቻ ሳይሆን ማስመሰል ማለቴ ገፀባህሪ የሚሉት ዓይነትን ነገር በጣም ትችላለህ፡፡ ሕዝብንም መንግስትንም ላለማጣት የምታደርገው ተነሳሽነት እንደ ክሬዲት ይያዝልሃል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግን ብዙ ጥሩ ነገር እያለህ ባንተ ቅር የሚለኝን ሳልደብቅ ልንገርህ፡፡ ምን አትለንም?

ብዙ ጊዜ ዋና ገፀባሕሪያትን ወክለህ መጫወትህን አልጠላውም፡፡ ግን ዋና ጓደኞችህን አንሰው እንዲተውኑ ታደርጋለህ፣ ምሳሌ ካልከኝ ሄሮሽማ ላይ ከእናት በላይ ሆና መተወን የምትችለውን የ ሸምጋይ ሬዲዮ ድራማ እማማ ፋናዬን አብዬ ዘርጋው ላይ ማለቴ ነው፣ ድርብ የቡና ቤት ሰራተኛ …. እሱ ብቻ አይደለም፣ ከልጅነት እስከ እውቀት ከጦር ሜዳ እስከ መድረክ ድረስ አብሮህ የዘለቀው የልብ ጓደኛህን አንዴ እብድ ….. አንዴ ጫማህን ጠራጊ እያደረክ ታስተውነዋለህ፡፡

ብዙዎች ሌሎችን አሳንሶ እሱ ገዝፎ መታየትን የሚወድ ነው ሲሉ እኔ ኧረ እሱ ይህንን አያስብም አልኳቸው፡፡ ይህንን ልነግርህ ባለው ቢሮህ ብመጣ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እስክል ደረስኩ፡፡ ገነት እንኳ መግባት የሚቀል መሰለኝ፡፡ ምነው ያኔ እንኳ ቤተመንግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ተፈትሸን ብቻ ነው እኮ የገባነው፡፡ ያንተ ቢሮ ፍተሻ፣ ሪሴፕሽን፣ ሶስት ቁጥር፣ አራት ቁጥር እንደገና ሌላ ሰው በመጨረሻም ሄደው ሄደው ስራ ላይ ነው ቀጠሮ ያዙ ተብለን እንመለሳለን፡፡
እንዲህ ነው ክብር፡፤ ታዲያ በዚህ ክብር ላይ ብትወዳደርና ቤተመንግስትን ብትጠቀልለው ገብርኤልን ባሕታን ለመሳለም ቀጠሮ ያዙ እንባላለን ወይም ትምህርት ሚኒስትር ወይም ስላሴ ስንሄድ ታጅበን ይሆናል፡፡ ይሁን ለደህንነት ከሆነ ማን ይጠላል፣ ማንም ግን የእውነት ለምን አትወዳደርም አንተ አኮ የቦታን እግር በመረዳት ፎቅ ለመስራት ስትል የ250 ሺህ ቤት ላይ የደፈርክ ጀግና ነህ፡፡ የደፈርክ ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ባለፈው አንዱ ምቀኛህ ምን እንዳለን ታውቃለህ? ጆሮ ለባለቤቱ መቼስ ባዳ ነው፣ መለስ ዜናዊ አባይን የደፈር ጀግና ሲባሉ ሰምቶ እሱም እንትን ደፈረና ከተማዋ ባንዴ በወሬ ተጠለቀለቀች፡ አለኝ፡፡ ተወው ባክህ የሄ ምን ላውራ፡፡ ግን እሱ ወሬ ምነው ቶሎ ጠፋ ሰው ግን ካንተ ራስ መውረድ አይፈልግም፡፡
ደሞ የደርግ ወታደር መሆንህን ለማንም እንዳትናገር ሰው ክፉ ነው፡፡ ይቺን ምክንያት አድርጎ ያማህና ብዙ ያሳጣሃል፡፡ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? ጠይቀኝ ካልክ «ግራና ቀኝ» ለምን ቆመ እኔ እኮ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እያለሁ ከገበሬና ከወዛደር የቱ ይበልጣል ወይም ከሴትና ከወንድ ማነው ኃላፊነት የሚበዛበት? እሉ የአማርኛ አስተማሪያችን በቡድን የሚያከራክሩንን ጊዜ ነው ቁልጭ አድርገህ ያሳየኸኝ፡፡

ያኔ በታምራት ገለታ ዙሪያ ወሬ ሲናፈስ ያንተም ስም ተነሳና ሰራዊት ይሄዳል ሲሉ አንተ ዝም አልክ፡ በኋላ በቅርብ ወዳጅህ «እኔ የኡራኤልን ፈረስ ጋለበ ሲሉኝ ምንም አይመስለኝም» አልክ አሉ፡፡ መቼስ መልስ አታጣ፡፡ የእውነት ተወዳደርና አሸንፈህ አራት ኪሎ ግባና ከስተህ ማለቴ አይደለም ቤተመንግስት አካባቢ ማለት ነው እኛን ምቀኞችህን ድራሻቸውን አጥፋ፡፡
ብዙዎች ምን ግራና ቀኝ ይላል ግራና ግራ አይደል እንዴ ቢሉም አንተ ናቅ አድርገህ ተዋቸውና ተወዳደር፡፡ የእውነት ተወዳደር፡፡

ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ አንተ እውነትም የጥበብ ሰራዊት እኮ ነህ፡፡ አውራ ጥበብን ብቻህን ድብን አድርገህ የያዝክ አርበኛ፡፡ አንተ ደራሲና ዳይሩክተር እንዲሁም ተዋናይ ባለቤት ዳይሬክተር፡፡ ምንም እንኳ ምቀኞች የማይመስል ነገር በሞናፖል እንዳይባል ነው ቢሉህም አትስማቸው፡፡ ደሞ ሰራዊትና ሴዲ አፍሮ ግርግር ይወዳሉ ሲሉ አትስማቸው፡፡ እንዴ አንተ እኮ ችግረኞችን የምትረዳ፣ ሕፃናትን የምታሳድግ፣ በተጠራኽበት የምትደርስ አይደለህም ቢሉህም አትስማቸው፡፡
ቢያንስ ቢያንስ በቲቪ የሚተላለፍ ፕሮግራም ላይ በዚያው ራስህንና ድርጅትህን በማስተዋወቅ ሰጠ ደግ ነው ለመባልም የሆነች ነገር ጣል አድርገህ ታስጨበጭብ የለም እንዴ? የሰው ውለታ መርሳት ነውር ነው፡፡ ደሞ ምን አለህና ያንተ ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደል እንዳለ ትላልቅ ኢቨንቶችን ነው የሚይዘው ቢሉህም እንኳን ዝም በላቸው፡፡ ምቀኛ ሁላ፡፤ ይልቅ ሁሉን እርግፍ አድርገህ ቁጭ ብለህ ሰራዊት ለጠ/ሚኒስትርነት ቢወዳደርስ ብለህ ጠይቅ፡፡ በቃ ትሆናለህ፡፡ ከዚያ ኃይሌ ፕሬዝዳንት አንተ…..

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top