Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 6

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 6

የሸገር ወጎች 6  

አጩሌ –  ከሸገር

Tales Of Sheger

Tales Of Sheger

ጆሮ አይሰማው የለ ይኸው ሰማን፣ አይን አላይም አይል ይኸው አየን ‹‹ጉድ በል ጎጃም አማርኛ አስተማሪ ከ… መጣልህ›› አሉ ሴትዬዋ ቢጨንቃቸው? ምድረ የሸገር ሕዝብ ደግሞ ‹‹ጉድ በል ሸገር ሙሰኛ ከ…ተገኘልህ›› ሲል ሰነበተ፡፡ ውይ… ውይ… ወዳጄ እኔን ሞት ይርሳኝ፡፡

ሰላምታዬን ዘንግቼው ወደ ቀደዳዬ ተንደረደርኩብህም አይደል? ይቅር በለኝ! አፉ በለኝ! ብያለሁ መቼም ሰሞኑን ሸገር እንዴት ግራ ተጋብታ እንደሰነበተች አልሰማሁም ካልከኝ ስቄም አላባራ፡፡ እንዲህም ሆኖ አንዲት እውነተኛ ነገር ነግሬህ ወደ ጨዋታችን እናምራማ ያኔ… ያኔ… በአፄ ምኒልክ ዘመን ተሽከርካሪ ለማሽከርከር የሚያበቃ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ውጣ ውረድ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ሙሴ ጋርዲያን የሚባሉ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው የተሽከርካሪ የብቃት ማረጋገጫ ፈትነው የሚሰጡ ባለስልጣን ነበሩ፡፡ የሚገርምህ ወዳጄ የፈተናው ነገር ነው፡፡ ፈተናው መነሻ ጊዮርጊስ መድረሻ ለገሀር ባቡር ጣቢያ ደርሶ መልስ ነበር፡፡ የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ… እንደፈለገው ያሽከርክር ደርሶ መመለሱ በቂ ሆኖ የብቃት ማረጋገጫ ይሰጠው ነበር፡፡ አስቂኙ ነገር ፈታኙ ሙሴ ጋርዲያን ራሳቸው ስለመኪና መንዳት እውቀት የሌላቸው እና መንጃ ፈቃድም ያልነበራቸው መሆኑ ነው፡፡

ይታይህ ወዳጄ የፈጀውን ይፍጅ እየተባለ እውቀት የሌላቸውን ማስቀመጡ ከአፄ ምኒልክ ተጀምሮ ይኸው አሁንም ያለው መንግስት ‹የፈጀውን ይፍጅ ዋናው ገንዘቡ መገኘቱ ነው› ብሎ ገቢና ጉምሩክ ላይ በዘመድ አዝማድ ያስቀመጣቸው ቱባ ቱባ ባለስልጣናት እንዲህ ጉድ ሲያደርጉን ለማን አቤት ይባላል?

እስቲ ይታይህ ዲያስፖራው ወዳጄ በሰው ሀገር ላብህን ጠብ አድርገህ፣ በቢል ስትረስ ተጨናንቀህ፣ ቀን አልሞላ ብሎህ በባዕድ ሀገር ብቻህን እንደ እብድ እያወራህ የሰበሰብካትን ጥሪት አንድ ማሽን ቢጤ ገዝቼ ሀገሬ ገብቼ አርፋለሁ ብለህ የጫንከውን ሁሉ እንደዘበት እንደ ልጅነት ጨዋታችን ‹‹እሟ ቀሊጥ›› ሲሉህ የነበሩት እነዛ ትልልቅ ሰዎች ተሰብስበው ‹‹ቃሊቲና ቂሊንጦ›› ገብተውልሀል /አትዘን ወዳጄ ሆድህ አይባባ/ አየህልኝ አይደል ጉዳቸውን? እኛ ቤት አባቴ ደመወዝ ሲቀበል በወር አንድ ቀን ብቅ የምትለው መቶ ብር በእነዚህ ሰዎች ቤት በተደረገ ፍተሻ የመቶ ብር መዓት ወለል ላይ ተዘርግቶ ባየው አምርሬ አዘንኩ፡፡ ለነገሩ የቀረበው በE.T.V በመሆኑ (እሷን ማመን ቀብሮ ነው) እንዳሉት እትዬ አለሚቱ እኔም ጠርጥሬያታለሁ፡፡

ለነገሩ የእነዚህኛዎቹ የጭቦ አምላክ፣ የደሀ እንባ አወጣባቸው እንጂ እኚያ ሰውዬ እንዳሉት‹‹ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራረጡ›› አይነት ነገር ላይ እኮ ነው ያለነው፡፡ ወዳጄ ሙት! በአንተ እምላለሁ ገና እናንተ ጋር ለገበያ ከቀረቡ አንድና ሁለት ሳምንት ያልሞላቸው ፓርሽ፣ እስካሌድ፣ ፌራሪ፣ ላምበርጊኒ የመሳሰሉ የቅንጦት መኪናዎች እዚህ ሀገር እንደ ጉድ የሚገቡት እውነት በላባቸው፣ ሰርተው ባመጡት ገንዘብ ከመሰለህ ተሞኝተሃል፡፡ ሌላው ቀርቶ መኖሪያ ቤታቸውን በአስር ሜትር ግንብ፣ ከግንቡ ላይ እሾህማ ሽቦ፣ በአናቱ አደገኛ የኤሌክትሪክ ሽቦ፣ እንዲሁም በሁለት ጎልያድን በሚያካክሉ የሰለጠኑ ጠባቂዎችና በአራት ውሾች ዙሪያቸውን የሚያስከብቡትና የሚያስጠብቁት በሌላ ከመሰለህ ተሳስተሃል፡፡ ሀብቱ የተገኘው በዘረፋ፣ በሙስና በመሆኑ የዘረፉትን ደሃ ላለማየት እና የኅሊና ሰላማቸውን በሙስና ስለለወጡ እኮ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጋር ቀርበህ ‹‹ደሀ የደሀ ልጅ ነኝ፡፡ እናቴ ቅጠል ሸጣ ነው ያሳደገችኝ›› ስትል ቢሰሙህ ‹‹ትቀልዳለህ እንዴ ቅጠል መሸጥ የሀብታም ስራ በሆነበት ዘመን እንዴት እንዲህ ትላለህ?›› ብሎ በሳቅ ይደክምብሃል፡፡
እሱ የሚያውቀው ከአምቦ ጀምሮ እስከ ጅማ፣ ከደብረብርሃን ጀምሮ እስከ ደሴ ያለ መሬትና ዛፍ በሙስና የተሸጠ በመሆኑ ያንተ እናት እንጦጦ ሄዳ ቅጠል ተሸክማ አምጥታ በመሸጥ አምስት ቤተሰብ እንደምታስተዳድር እንዴት ይግባው፡፡

በቃ ሰዎቻችን እውቀቱ ሳይኖራቸው ሀገር እየመሩ የፈጀውን ይፍጅ… እየተባባልን መኖር ከተባለ እንኖራለን፡፡ (ወዳጄ ይቅርታ ቢብሰኝ ቢመረኝ ነው ምርር ያለ ወሬ ያወራሁህ) በነገርህ ላይ ይህች ሀገር ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን መሪዎቿም ቀልደኛ ሆነውልሀል፡፡ ሰሞኑን በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ከፍተኛ ባለስልጣናትን በተመለከተ አንዱ ባለስልጣን በቴሌቪዥን መግለጫ ሲሰጥ ‹‹ሰዎቹ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ከመሞታቸው በፊት ትዕዛዝ የሰጡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒቴር መለስ ዜናዊ ናቸው›› ብሎልህ አረፈው፡፡ ይሄን ነገር መለስ ቢሰሙ እንዴት እንደሚስቁ ታየኝ፡፡ ኧረ ሼም ነው! ሼም! ሼም! እንዴ ምናለ ሰውዬው ቢያርፉበት ወይስ ኃ/ማርያምን በአሽሙር መሳደባቸው ነው? በነገርህ ላይ ሸገር እንኳን ይህን ሰምቶ እንዲሁም መቀለድ ይወድ የለ፤ ይህች ወሬ እንደተሰማች አንድ ቀልድ ተወልዳ አደረችልህ፡፡

ሚኒስትሮቹና ባለሀብቶቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ለስራ ጉዳይ ኳታር ነበሩ፡፡ ይህንንም ተከትሎ እንዲህ ተቀለደ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርፖርት እንደደረሱ ሊቀበሏቸው የመጡትን ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደነገሩ ሰላም ካሉ በኋላ በምሬት ‹‹ምንድነው የምሰማው? እውነት ነው እንዴ እነ እከሌ ታሰሩ የሚባለው? ለምንድነው እኔ በሌለሁበት እንዲህ እያደረጋችሁ ስሜን የምታስጠፉት?›› ብለው እርፍ፡፡ ለካ እሳቸውም የሰሙት ልክ እንደኛው በቴሌቪዥን ኖሯል፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የደበቀ ፓርቲ ለሕዝብ… ቂ…ቂ…ቂ…ቂ፡፡

ሌላኛው ከአሳሪዎች አንዱ የሆኑት ኮሚሽነር ደግሞ በፓርላማ ለምን እስካሁን ምርመራው ዘገየ? ተብለው ቢጠየቁ ‹‹ኮሽ ባለ ቁጥር አይተኮስም›› ብለው ሲመልሱ ፕሮግራሙን በቴቪ ሲከታተሉ የነበሩ በ97 ምርጫ ሁለት ልጅ ያጡ የመርካቶ እናት እንዲህ አሉ ተባለ፡፡ ‹‹ያኔ የተኮሳችሁት ኮሽ ስላለ ሳይሆን ስለተንኮሻኮሸ መሆኑ ነው? እንዲህማ አይቀልዱ! ያው ያቺ የኤቲቪን መከረኛ ፉገራ ታውቋት የለ፡፡ አንድ ነገር ሲፈጠር ከመቼው ሰርተው ከመቼው እንደሚያቀናባብሯት እንጃ እንጂ እነሱ ዶክመንተሪ የሚሏት ነገር አለች፡፡ ‹‹ጃሀዳዊ ሀረካት››፣ ‹‹አኬልዳማ›› የመሳሰለ ታዲያ ከሰሞኑ በዚሁ ጉዳይ ላይ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተናገሩት እያለ ጆሮአችንን ሲያደማው ነበር፡፡ እየደጋገመ አቀረባቸው፡፡

ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መሀከል አንዱ ‹‹መንግስት በደንብ ማበጠር አለበት፣ ማነፈስ አለበት፣ ስንዴና እንክርዳዱን ለይቶ ማበጠር ይጠበቅበታል›› ሲል የሰማው አባቴ ጋቢውን አፉ ላይ ጣል እንዳደረገ ‹‹ይሄን ሰውዬ ያገኙት ከወፍጮ ቤት ነው ወይ?›› ብሎልህ አረፈው፡፡

እንደመሰናበቻ አንድ ነገር ላውጋህማ ከተከሰሱት ሚኒስትር ዳይሬክተሮች የአንዱ ክስ ደረጃውን ያልጠበቀ ሲሚንቶ አስገብተዋል የሚል ነው፡፡ (ከተማ ላይ ሁለት መርከብ ነው እየተባለ ይወራል) ታዲያ ሰሞኑን ሲሚንቶ ሊገዛ ገበያ ብቅ ያለ አንድ ወዳጄ የገጠመውን እንዲህ ሲል አወጋኝ›› ሲሚንቶ ልገዛ ሄጄ ሲሚንቶ ብላቸው ‹‹ሙገር ነው የምትፈልገው ወይስ ገብረዋህድ?›› አይሉኝ መሰለህ፡፡ ቂ…ቂ..ቂ ገብረዋህድ የተከሰሰው ሰው ስም ነው፡፡ ነጋዴ ደግሞ ሕገ ወጡን ሲሚንቶ ስም አውጥቶለት ቁጭ! ‹‹ገብረዋህድ!›› አይ የሸገር ሰው! የወር ሰው ይበለን!!

ኢትዮጵያን እግዚብሔር ይባርክ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top