Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 5

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 5

የሸገር ወጎች 5

አጩሌ –  ከሸገር

Tales Of Sheger

Tales Of Sheger

ሠላም ብያለሁ ዲያስፖራው ወዳጄ እንዴት ከርመህልኛል? እኔ የሸገሩ አጩሌ በጣሙን ደህና ነኝ ብልም ወዳጄ ሙት እልሃለሁ ለደህንነቴ ማረጋገጫ አቅርብ ብትለኝ ስቄም አላባራ፡፡ ጥርስህ ይርገፍና ምን ያስቅሃል? እንዳትለኝ እንጂ ምድረ አዲስ አበባ እንደ ዘንድሮ ስቆም አያውቅ፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ የምልህ ደግሞ ወዶ የሳቀ እንዳይመስልህ ገዢዎቻችን ኰርኩረው በግድ አስቀውት እንጂ፡፡ ነገሩ እንዴት መሠለህ ፀሃዩ መንግስታችን ሰሞኑን በምርጫ ዜና እና ወሬ ድንቁር አድርጐን የለ? ዛዲያልህ ለአዲስ አበባ ከንቲባነት ዕጩ አድርጐ ካቀረባቸው ሰዎች መሀከል የፌዴራል ፖሊስ አዛዡ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን አብዝቶ አብዝቶ እንደገናም አብዝቶ ይማርልን) ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ይገኙበታል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ለዕጩነት መቅረባቸው ምን ያስገርማል? ምኑስ ያስቃል? እንደምትለኝ አውቄያለሁ፡፡ ግን የሸገርን ሕዝብ ያሳቀው ምን እንደሆነ ታውቃለህ፡፡ ከነዚህ ሁለት ሰዎች ፎቶ ስር የትምህርት ደረጃ ተብሎ ምን እንደተፃፈ ሰምተሃል? ዲግሪ!

የሸገር ሕዝብ ታዲያ ሣንምንቱን ሙሉ ሲደክምልህ ሰነበተ በሳቅ፡፡ ወዳጄ ዲግሪ እንዲህ መቀለጃ ትሁን? ኧረ ሼም ነው! በእውነት ሼም!ያኔ ያኔ በመንደራችን በሠፈራችን አንድ ሰው ዲግሪ ጫነ ሲባል እንደ ተአምር ለታሪክ የምናየው የምንሰማው ቀርቶ አሁን አሁን የቀበሌያችን ሊቀመንበር እና ካድሬዎች ጭምር ባለ ማስተርስ እና ባለ ፒ.ኤ.ች.ዲ ናቸው ብባል በእውነት… በእውነት አንድ ነገር ጠረጠርኩ፡፡ ይሄን ሁሉ መሃይም በአንድ ጊዜ ባለዲግሪ ያደረጉት የሰውዬውን ራዕይ ለማስፈፀም ይሆን እንዴ?ቂ…ቂ..ቂ..

ታዲያ እንዲህ እንዲህ አይነቱ ሲያጋጥምህ ዘንድሮ ያለህ አማራጭ መሳቅ ብቻ ነው፡፡ ፌዴራልም አያንጓጥጥህ፣ ደህንነቱም አይቀጠቅጥህ ዝም ብለህ ብቻ እነሱ የሌሉበት ቦታ እየመረጥክ በሳቅ ፍርስ ማለት ብቻ! እንደ 97ቱ ልጩህ ብትል ወደ ጆሮ ግንድህ አካባቢ የሚጮህ ነገር ያለው በቅርበት ስለሆነ ከመጮህ ‹ላፌንጋዝ› እንደወሰደው ሰው በባዶ ሆድህ መሳቅ ድሮስ ዘመኑ መሳቂያ ሆኖ እንዴት ተደርጐ ይጮህ? በነገርህ ላይ ዲያስፖራው ወዳጄ ኢትዮጵያ ካለህ፣ ኢትዮጵያ የምትኖር ከሆነ ትልቁ መብትህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? መብራት ጠፍቶ ሲመጣ መጮህ ብቻ፡፡

እውነቴን እኮ ነው አይ መብቴ ተነክቷል ክብሬ ተዋርዶአል ዓለም ጩኸቴን ይስማ ምና ምን ብለህ እጮሀለሁ ብትል እንኳን ከአሜሪካ ከመንግስተ ሰማያትም ቢሆን እናመጣሀለን የሚሉ ሺ ኢንስፔክተሮች ሃገርህ ፈልፍላልሀለች፡፡

እናንተዬ የእኚያ ጁነዲን ሳዶ የሚባሉ ሰውዬ ነገር ግርም አላላችሁም? ወይ ኢህአዴግ መቼም ሰው አይበረክትለት እኔን የገረመኝ አሜሪካ ያለ ጋዜጠኛን እንኳን አሜሪካ መንግስተ ሰማያትም ብትሆን አስርሃለሁ እያሉ የሚፎክሩት ኢንስፔክተሮቻችን ምን ዓይነት እንቅልፍ ላይ ቢሆኑ አጠቃቀስኩ ብለው ኬንያ መግባታቸው ወይ ጂነዲን አቦ ይመችዎት፡፡
«ሳይያዙ ነው ማምለጥ ሳይያዙ
ከተያዙ በኋላ ብዙ ነው መዘዙ»ን አቀንቅነው ባለቤታቸውን ወሕኒ ቁጭ አድርገው የመልካሙ ተበጀን ‹‹ደህና ሁኚ ፍቅሬ… ሠላም ሁኚ››ን እያቀነቀኑ ‹ካሪቡ› ብለው ኬንያ ጥልቅ፡፡

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ አንዲት ቀልድ ሲያካፍለኝ የፀሐዩ መንግስታችን ስራም እንዲሁ ነው በማለት ነበር ቀልዷ ምን መሰለችህ አንድ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ወደ መማሪያ ክፍል አርፍዶ ይገባል፡፡ ይህን ግዜ አስተማሪው በንዴት፣
አስተማሪ፡- አንተ ምን ሆነህ ነው ያረፈድከው?
ተማሪ፡-አንድ ሰውዬ 100 ብር ጠፍቶት ነው
አስተማሪ፡-ታዲያ አንተ ብሩን ስታፋልገው ነበር?
ተማሪ፡-አይ በእግሬ ብሩ ላይ ቆሜበት ነበር፡፡

አየህ ወዳጄ ሰዎቻችን ደስ የሚል ነገራቸው ምን እንደሆነ ታውቃለህ? በሞቴ እስቲ ሞክር? አዎ ደርሰህበታል ችግራችን ላይ ቆመው ችግራችሁ ምንድነው እያሉ መጠየቃቸው እኮ ነው። ብላቴናውን እንደ መንግስት፣ ብር ጠፍቶበት የሚሰቃየውን ደግሞ እንደ ሕዝብ አስበው… ሕዝብ ግራ ገብቶት በዚህ የኑሮ ውድነቱ፣ በዚህ ሰሞኑን የጫኑብን ‹ለሁሉ› የሚባል የክፍያ ስርአታቸው በዚህ እነ ኤፈርትና ትዕምት ቆመውብን የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ከየት ጠብ ይበል? አንዱ ወዳጄ እስቲ አዲሱ ጳጳስ ወይ በፀሎት አልያም በቋንቋቸው አነጋግረው ቁልፉን ያመላክቱን ይሆናል ብሎኝ አረፈው፡፡ ማን ነበር ከእጅ አይሻል ዶማ የሚል ግጥም የነበረው?

ዲያስፖራው ወዳጄ የእኛም ነገር እናንተ ጋር ደርሶ አንድ ቤተክርስቲያን መዘጋቱዋን ስሰማ እነዚህ መተካካት በማለት መልቀቃቸው የተነገረን ቱባ ቱባ ሰዎቻችን እዛም ሄዱ እንዴ? ብዬ ማሰቤን አልደብቅህም፡፡ ሲያመጣው ልክ የለው እንዳሉት እኚያ ሰውዬ ይሄ ነገር ስር ሰዶ የማምለኪያ ቦታ እስከ መዘጋት ከደረሰ በእውነት ሼም ነው ብያለሁ በራሳችሁ በአገራችሁ ቋንቋ፡፡ ምን አልክ? ሰምተኻል፡፡

ወዳጄ ሰሞኑንማ እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የተኩት ሰውዬ አቶ ኃይለማርያም ወይ (ውይ በሞቴ ለካ ጠቅላይ ሚኒስቴር ማለት ነበረብኝ)ምን እንዳጠፉ… ምን እንደበደሉ እንጃ ሰኞ የደኢህዴን ፕሬዝዳንት ማክሰኞ የፓርቲው ሊቀመንብር ዕሮብ የኢህአዴግ ፀሐፊ ሐሙስ እያደረጉ በስልጣን ላይ ስልጣን (ቂቂ…ቂቂ… ወይ ስልጣን?) ሲጨምሩባቸው ምን ሲጨምሩባቸው ሲከምሩባቸው ሳይ በእውነት አሳዘኑኝ፡፡ አንጀቴን በሉኝ ምን አለ እኚህ ሰውዬ ኧረ ይህ ነገር በዛብኝ አይሉም እንዴ? አንድ ወዳጄን ብጠይቀው ማረፊያቸው ደርሶ ይሆናል ቢለኝ ደንግጨ የት? ብለው ቅዱስ ሉቃስ ሆስፒታል (ሲውዘር ላንድ) አይለኝ መሠለህ የአቶ መለስ የመጨረሺያ ማረፊያን በማስታወስ ግን ከምሳሌ ፀጉር ይነቀል አንድ ነገር ጠረጠርኩ…ልነግርህ አስቤ ነበር ይቅርብኝ ተውኩት ክፉ አታናግረኝ ደህና ክረምልኝማ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top