Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 4

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 4

የሸገር ወጎች 4

አጩሌ –  ከሸገር

Tales Of Sheger

Tales Of Sheger

ዲያስፖራው ወዳጄ እንዴት ሰነበትክልኝ? እኔ የሸገሩ አጩሌ ካንተ ከዲያስፖራው ወዳጄ ሃሳብ እና ቀን በእውኔ፣ ሌት በህልሜ ውልብ አያለችብኝ ከምትናፍቀኝ ያቺ ሀገራችሁ አሜሪካ ናፍቆት በቀር ሠላም ነኝ ከተባለ ሰላም ነኝ! ወዳጄ ኢትዮጵያ ምድር ላይ እየኖሩ ሠላም ነኝ የሚሉ ሰዎች በተመናመኑበት በዚህ ወቅት ሰላም ማለት ትርጉሙን እንዴት ብዬ ላስረዳህ እንደምችል ቢጨንቀኝ ዝምታን መረጥኩ (አንቺ ምን አለብሽ… አይቆምብሽ…) አሉ እትዬ አለሚቱ፡፡ እንዲህም ሆኖ ወደ ወጋችን እንለፍማ እኔ የምለው ይኼ 100 ዶላር ላይ ያለው ሰውዬ ግን ደህና ነው? ምነው እንዲህ ድምፁ ጠፋ ባክህ? እኛ ጋርማ እንኳን ግለሰብ እጅ ሊገኝ ቀርቶ ባንኮች እንኳን ሲጠየቁ ‹‹ እንኳን መልኩን ድምፁንም ከሰማን ቆየን›› እያሉ መመለስ ከጀመሩ ሰነባበቱ ምድረ የሸገር ነጋዴ ደግሞ እንኳን እንዲህ ዓይነት ወሬ ሰምቶ እንዲሁም ሰበብ ፈላጊ ነውና ከሰልም ልትገዛ ሆነ ሳሙና ልትሸምት ገበያ ብቅ ስትል ትላንት በሁለት እና በሶስት ብር የገዛኸው ሣሙናን አስራ አምስት ብር ይልሀል፡፡

ምነው? ወዳጄ በሀገር ሠላም? ስትለው አልሰማህም እንዴ ዶላር ተወዷል… ዶላር ጠፍቷል ብሎ ይመልስልሃል ፈጣሪ ያሳይህ እስኪ አሁን ሌላውስ ይጨምር ከሰልን ከዶላር ጋር ምን አገናኘው? እኛ እኮ ግራ ገባን ኑሮአችንን እናስታም ወይስ ቄሶቹን እናስማማ? በአንድ ወቅት ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም አሉ ተብላ ሸገር ላይ መሣቂያ የነበረች አንዲት ነገር ትዝ አለችኝማ ምን መሰለችህ ወዳጄ መቼም ከዚህ ቀደም ሰምተሃት ከሆነ በሞቴ ደግመህ ስማኝማ…ወቅቱ ኮረኔል መንግስቱ ሊቀመንበርነቱንም ለሰፊው ህዝብ ሲባል.. የጦር አዛዥነቱንም ለሰፊው ህዝብ ሲባል … የኢሠፓአኮ ፀሐፊነቱንም ለሰፊው ህዝብ ሲባል… የኢህድሪ ቀዳሚ ፕሬዝዳንቱንም ለሰፊው ህዝብ ሲባል እያሉ ስልጣኑን በሙሉ ጥርግርግ አድርገው በያዙበት ወቅት ነው አሉ፡፡
ታዲህ እዚህ ቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉ አባቶች እንደ አሁኑ ጳጳስ ማንን እናድርግ? እያሉ አንዴ ወደ ላይ አንዴ ወደታች ሲሉ ጉዳዩ በፍጥነት ‹‹ቆራጡ መሪ››መንግስቱ ኃ/ማርያም ጆሮ ትደርሳለች መንጌ አራዳው በፍጥነት የቤተክርስቲያን አባቶችን ሰብስቦ በመጥራት ትንሽ… ‹‹ቂጣቸውን በሳንጃ ወጋን!… እንዴት ነው ነገሩ? ንገሩኝ እንጂ… ልብ ልንገዛ እንችላለን እንዴ?›› ብሎ ካደነባበራቸው እና ከፎከረባቸው በኋላ ችግራችሁ ምንድ ነው? ሲል ይጠይቃል የሃይማኖት አባቶቹም ጳጳስ የሚሆን ሰው ለመምረጥ እንደተቸገሩ ይነግሩታል ታዲያ ይሄኔ መንጌ እንዲህ አለ አሉ ‹‹ችግር የለም!!! ለሰፊው ህዝብ ጥቅም እስከሆነ ድረስ የጳጳሱንም ቦታ እኔ ደርቤ እይዘዋለሁ!!›› ብሎላችሁ እርፍ አሪፍ ቆረጣ አይደለች? ታዲያ ሰሞንኛው ግርግርም የሚፈጥረው ክፍተት ‹‹ደርቤ እይዘዋለሁ!››የሚል እንዳያስነሳብን አባቶች ተስማሙ እላለሁ፡፡

‹‹ብልህ ሰው ከታናሹ ይማራል›› እንዲል ቅዱሱ መፅሐፍ፡፡ ታዲያ ሰሞኑን የሸገር ወሬ ሁሉ ስለዶላር ሆኖልህ ሰነበተ ዲያስፖራው ወዳጄ እባክህ አንተ አታጣውምና የሸገሩ አጩሌ እና ድፍን የሸገር ሰው ባንተ የተነሳ አበሳ እያየን ነውና እስኪ ባክህ ብቅ ብለህ ታየን ይሉሀል የሚል መልእክቴን አስተላልፍልኝማ (ለኔ ግን እቅፍ አድርገህ ሳምልኝ) ወዳጄ ባለፈው ጨዋታችን ስለነዚያ የሃይማኖት አባቶች አንዳንድ ነገር አውግቼህም አልነበር? ቃሌ መች መሬት ጠብ አለች ለአገር ለምድር የከበዱት እነዚያ አባቶች ጉዳይ በቃ እንደ ልጅነታችን ‹‹ጨዋታው ፈረሰ … ዳቦ ተቆረሠ›› አይነት መሆኑ አሳዘነኝ፡፡ አሀ! ለስንት ነገር ይበቃሉ አገር ይመክራሉ የተባሉት እራሳቸው ተመካሪ ሆነው በሜዳ ሲቀሩ እኔ አጩሌ ሀዘኔ ቅጥ አጣ፡፡ ወይኔ ሰውየው! አሉ የእድራችን ሊቀመንበር፡፡
ወደሌላው የሸገር ወግ ልውሰድህማ… ይኼ የከተማችን በየቦታው መቆፋፈር እና ተጀምረው በማያልቁ መንገዶች በቁፋሮ በአርኪኦሎጂስቶች የተገኘች መምሰል ያበሳጫቸው ነዋሪዎች ኡኡታን ያዳመጡት ከንቲባ ባለፈው በየመንደሩ እየዞሩ የተጀመሩትን መንገዶች ተመልክተው በድንጋጤ ክው ብለው ነበር አሉ፡፡ ለካ የተጀመረውን ሁሉ ተጨርሶ ስራ ጀምሯል እያሉ ሪፖርት በሚያደርጉላቸው የበታቾቻቸው የተጨረሰ መንገድ ሊያዩ ቢሄዱ ገና ያልተጀመረ ሆኖ ቁጭ፡፡ ታዲያ ምናሉ አሉ መሰላችሁ ‹‹በ6 ወር ነው እንጨርሳለን ያላችሁት? እንኳን በ6 ወር በ16 ዓመትም አታጠናቅቁትም ብለው ቻይናዎቹን ኩም አደረጓቸው ሲባል ሠማሁ፡፡

እናንተዬ መንገድ ሰሪዎቹ ቻይናዎች ሁሉ ሥራቸውን ሁሉ ትተው እንደ አገሬው ሰው ውሎአቸው ሁሉ ጫት በመቃም መሆኑን የሸገር ሰው ሲያወራ ሃሜት ነው አልሰማም ያልኩት ተሸውጄ ኖሮአል፡፡ እውነት እኮ ነው የሰለጠኑት ሀገራት በ6 ዓመት ሠርተው የማይጨርሱትን መንገድ በ6 ወር ሠርተን እናስረክባለን የሚሉት ለካ በምርቃና ብው እያሉ ነው! አንዴ ጫት ይዘው ከተቀመጡ መነሳት አያውቁም ለነገሩ እሱንስ የተማሩት ከማን ሆነና? ከቱባ ቱባ ባለስልጣኖቻችን አይደል? ደግሞስ ነፍሳቸውን ይማርና ሟቹ ሰውዬ ከስልጣኖት ይነሱ ተብለው ሲጠየቁ ‹‹እንኳን ከስልጣን ከጫትም ላይ መነሳት ይከብዳል›› ብለው መለሱ እየተባለ ሸገር ላይ የሚፎገረው እኮ እውነትነት አለው የስልጣኑ ባይብስ ብለህ ነው ወዳጄ? እንዲህም ሆነ እንዲያ እንኳን በ6 ወር በ6 ቀንም እንጨርሰዋለን ካሉ ያለን አማራጭ ማመን እና ማመን ብቻ ነው እነሱ ባይታመኑም፡፡

እዚህ ላይ በአንድ ወቅት አቤቶክቻው ያላትን ነገር ልበደረውማ‹‹እኛ ስናምነው እሱ ያሳምመናል እንጂ ማመኑንስ እናምነው ነበር፡፡ ለምሳሌ በ97 ምርጫ የምርጫውን ውጤት ተቀብሎ ‹‹ላጥ›› ይላል ብለን አምነን ነበር፡፡ ግን አልታመነም በጥይት አሳመመን እንጂ›› ድንቅ አባባል አይደለች አቦ ታምኖ ካለመታመን ይሰውረንማ…ቆይ ታዲያ ማንን እንመን? ወዳጄ ሙት ከተማ ላይ የሚሠሩትን ፎቆችና ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች በኢቲቪ ስትመለከት ሀገሬ አደገች ማለትህ አይቀርም እኛስ ብታድግ ምን ከፍቶን? ግን ፎቆቹ የማን ናቸው?… በል ተወኝ ቦተሊካ አታስወራኝ… ግን..ግን.. በመንግስት ሲሚንቶ፣ በመንግስት ብር፣ በመንግስት መሬት በሙስና በተገኘ ገንዘብ የተገነቡ እኮ ናቸው፡፡

ታዲያ በኢቲቪ ሲያሳዩህ አምነህ ከሆነ አትሸወድ፡፡ እስቲ ልብ ካላቸው ባለስልጣኖቹ የእውነት…የእውነት ሃብታቸውን ያስቆጥሩ?… ታዲያ እንደባለፈው ደሞዜ ሶስትሺ ብር ናት የምኖረው በኪራይ ቤት ነው የሚል ሚኒስቴር አንፈልግም እኛ ያልነው የእውነቷን! ነውና፡፡ ‹‹እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን›› አለች ሴትዮዋ ስትተርት፡፡ እኛም እንዲያ ሆኖብን ነው እንጂ እንዲህ አይነቱን ሲኤምሲ ያለህ ፎቅስ?.. ቦሌ በአጐትህ ስም የያዝከው መሬትስ (ፈረስ ልታረባበት ነው ስታዲየም ልትገነባበት) ብለን መጠየቅ እንችል ነበር ግን ምን ያደርጋል? ወይኔ ሰውየው! አይደል ያሉት የእድሩ ዳኛ? ወዳጄ ባለፈው ከወደ እናንተ ሀገር የሰማሁት ነገር በጣም ነው ያስደነገጠኝ፡፡

እንዴ ይሕን ያህል ‹‹ፀሐዩ መንግስታችን›› ፋራ ሆነ እንዴ? በቃ አበበ ገላው፣ አበበ በለው፣ አበበ ቶክቻው (አቤ ቶክቻው) በቃ የአባቱ ስም ማንም ይሁን ማን አበበ የሚባል ሰው አልይ አለ እንዴ? በእውነት በእውነት አሜሪካ ድረስ ሄደው ይህን ያደረጉት ሰዎች መንግስታችን የላካቸው ሰዎች ከሆኑ በእውነት ሼም ነው!!! እንዲህም ሆኖ ድሮ ድሮ ያገሬ ሰው ሲተረት ‹‹የወደቀ ዛፍ አያድርግህ›› ይል ነበር ታዲያ ዘንድሮ ምን ቢል ደስ ይልሃል? ‹‹‹ስምህን አበበ አያድርገው›› ኧረ እንኳን በደህና ጊዜ አጩሌ ሆንኩኝ ወዳጄ በል ደህና ክረምልኝ የወር ሰው ይበለን!!!

ኢትዮጵያን እግዚአብሔርን ይባርክ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top