Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 3

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 3

የሸገር ወጎች 3  

አጩሌ –  ከሸገር

Tales Of Sheger

Tales Of Sheger

ዲያስፖራዉ ወዳጄ ሰላምህ ይብዛ! እንዴት ከረምክልኝ? እኔ የሸገሩ አጩሌ ካንተ ከወዳጄ ናፍቆት በቀር ‹ሰላም ነኝ› ከተባለ ሰላም ነኝ፡፡ መቼም ጀግናው በላይ ዘለቀ ‹‹ወንድ አይብቀልብሽ›› ብሎ በረገማት የጉድ ምድር እየኖርኩ ሠላም ነኝ ከማለት ውጪ ምን ልበል?

ወዳጄ ባለፈው ሠሞን እኛ ሀገር ቤት ያለነውንም ሆነ እናንተ ዲያስፖራዎችን አንድ ያደረገን (ተመስገን አምላኬ በዚህ እንኳን አንድ አንሁን እንጂ) ሠሞነኛ ወሬ የእነኚህ የጳጳሳቱ ጉዳይ ቢሆንም እኔ አጩሌ ዴንታም አልሰጠሁት፡፡ ለምን እንደሆነ ገባህ? በረዣዥም ወንበር ላይ የተቀመጡት የጌቶቻችን የቼዝ ጨዋታ እንደሆነች ጠንቅቄ ስለምረዳ ነዉ፡፡ እዚህ ጋ በኑሮ ውድነትና በታክስ የሚቃጠለውንና ሆድ የባሰዉን ምስኪን ሃሳቡን ለማስረሳት፣ አመለካከቱን ለማስቀየር የወሠዱት ስትራቴጂ ወይም በእራሳቸዉ ቋንቋ ‹ቆረጣ› እንደሆነች አዲስ አበቤ ያልነቃባቸዉ መስሎአቸዋል፡፡

ለፉገራዉና ለመሸወዱም ቢሆን የሸገር ሠዉ እንደሚቦንሳቸዉ አልተረዱም፡፡ አይ አለማወቅ!!! ዲያስፖራዉ ወዳጄ እረ እንደዉም ባለፈዉ እዚሁ ሸገር ላይ የተፈጠረች ነገር ላዉጋህማ ነገሩ እንደህ ነዉ… ምን እንደነካብን ሳይታወቅ ቡዳ ይብላዉ፣መጋኛ ይምታዉ፣ ክፉ መንፈስ ይፀናወተዉ ሣይታወቅ ‹‹መርጣቸችሁኛል! ዘጠና ዘጠኝ ፐርሠንት አሸንፌያለሁ! ያለሁም እኔ የሞኩትም እኔ!›› ያለዉ መንግስታቸን ‹‹ደሃ እንዳላይ! የታረዘ እንዳልመለከት!ደሃ ማለት ትርጉሙ የጨረቃ ቤት ያለዉ ነዉ›› ብሎ ዘመቻ በሚመስል ሁኔታ የስንቱን ደሃ ቤት በልተው በጠገቡ ካድሬዎቹ ፊት አውራሪነት ማፈራረስ ጀምሮልሃል፡፡

ታዲያልህ የሸገር ደሃ ፖለቲካዉን የኑሮ ዉድነቱን ሁሉ ረስቶልህ እንቅልፍ አጥቶ ሠነበተ፡፡ እና በቀደም ዕለት እንደለመዱት አንዱን ሠፈር ለማፍረስ ቢሄዱ የአከባቢዉ ሠዉ ሁሉ ተማክሮ እና አስቦበት ቆይቶ ነበርና ገና ለማፍረስ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ምስል ሁሉም ከየደበቀበት አዉጥቶ መሬት ላይ በማንጠፍ የእሳቸዉን ፎቶ ረገጣቸሁ እለፉ እንጂ ካለዚያ አታፍርሷትም›› ብለውልህ እርፍ! ቀበሌዎቹስ ምን ሞኝ ናቸዉ ‹በሉ ተዉት!!› ብለዉልህ ሄዱ፡፡

አየህ ሠዉየዉ በሕይወት ባይኖሩም እንዲህ ከጅርባ እየገዙ ነዉ! በመንፈሳቸዉ! እንደዉም እንደ ካድሬው ወደጄ የእሳቸዉን ታዓምር እንደ ታዓምረ ማርያም እና ድርሣነ ሚካኤል ሲያዝጎደጎድልኝ እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች እናቶች ልጆቻቸዉን ቡዳ እንዳይበላቸዉ በክታብ መልክ የሠዉየዉን ምስል ልጆቻቸዉ እንገት ላይ እንዲታሠርላቸዉ ጥያቄ አቀርበዋል ብሎኝ አረፈልህ፡፡ ‹‹እረ እናንተ ሠዎች አንዳንዴም ፈጣሪን ፍሩ›› ልለዉ ፈልጌ ነበር፣ ነገር ግን ተዉኩት፡፡

አየህ የሠዎቻችንን ሙድ የመብት፣ የነፃነት፣ የዳቦና የእንጅራ ጥያቄ ለማንሣት ማሠብህን ካወቁ ሌላ ሃሳብህን የሚበታትን ነገር አምጥተዉ ይጭኑብሃል፡፡ እሡን አላምጠህ እስክትጨርስ ጊዜዉ ይነጉዳል፤ ለዛም እኮ ነዉ ይሄ የጳጳሳት ጨዋታ ያልደላኝ፡፡ እርግጥ ነዉ ሃይማኖት፣ እምነት፣ ምናምን.. ልትለኝ ትችላለህ፡፡ እኔ ግን ከሱ ጀርባ ያለዉን እያሰብኩ ፈገግ እለላሁ፡፡ እሰቲ ፈጣሪ ያሳይህ ወዳጄ ገና ያአዲስ አበባዉ ልዑክ ዳላስ ለስምምነት ከመድረሡ ከአዲስ አባባ ለቪ.ኦ.ኤ መግለጫ የሠጡትን አባት መልእክት አዳመጥከዉ? ‹‹በቃ አትልፉ የምትመጡ ከሆነ ኑ! ቤትና መኪና ይሰጣችኃል፡፡ አለበለዚያ የወንበሯን ነገር እንዳታስቧት እንቁልልጭ! እንዳማራችሁ ትቀሩዋታላችሁ›› እኮ ነዉ ያሉት፡፡ አረ ሼም ነዉ ወዳጄ!

ያ ካድሬ ወደጄ ስለ እነዚሁ አባቶች ስምምነትና ሰለ አሜሪካዉ ድርድር ብጠይቀዉ ‹‹እባክህ አትቀልድ እንኳን ቀድሞ የነበሩት ሊመጡ አሁን የሄዱትም የሚመለሡ አይመስለኝም! ምን ነክቶሀል አገሩ አሜሪካ እኮ ነዉ!›› ብሎኝ ቁጭ፡፡ ካድሬዉ ወዳጄን በእውነት ታዘብኩት፡፡ ለካ ለአፍ ያህል ነዉ ‹መንግስታችን! ፀሃዩ መሪያችን! ባለ ራዕዩ!…› ምናምን የሚለዉ እንጂ ለአንድ ሳምንት ኮርስ እዚህች ጎረቤት ኬንያም ቢልኩት የሚመለስ አይመስለኝም፡፡ እንዲያዉም እኚህ አዲሡ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈዉ ከአልጀዚራ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ካየሁ በኃላ እሣቸዉንም ክፉኛ መጠራጠር ጀምረያለሁ፡፡

አንዴ ዲያስፖራው ወዳጄ ምን እንዳሉ ሠምተህልኛል? ‹ኤርትራ ሄጄ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር መደራደር እፈልጋለሁ ሲሉ ሠምቼ በሣቅ ልፈነዳ…› ይቀልዳሉ እንዴ? አልመለስም ብለዉ እዛዉ ጥገኝነት ቢጠይቁስ? ያልከኝ ወዳጄ ዋ! እንዳይሰሠሙህ (የቀድሞዉስ የዘመዶቻቸዉ አገር ነዉ.. እኚህኛዉ ምን ቤት ነኝ ብለዉ ይሆን?)አትሣቅ ወዳጄ የሚያስቅ ነገር የለምና፡፡

አ…. ረረ..ረረ..ረስቼዉ እኚህ ፕሬዘደንታችን ደግሞ ሃይለኛ ኮሜዲም መስራት ይችላሉ ለካ? ያ መስከረም ከምትሉት ደረቅ ኮሜድያን እኚህ አቶ ግርማ ቀልድ ይዋጣላችዋል ለካ፡፡ ባለፈዉ አሜሪካ ለሚገኙት ጳጳሣት ‹‹እባካችሁ ወደ ሀገራችሁ ግቡና በአንድነት ሀገራችሁን፣ ሕዝባችሁንና እግዚያብሄርን አገልግሉ› ብለዉ ደብዳቤ መፃፍ! ከዛስ አትልም ወዳጄ? ከዛማ ሀገሪቱን ከመጋረጃዉ ጀርባ ቁጭ ብሎ የሚመራት ሠውዩ እሣት ለብሶ እሣት ጎርሶ ወደ ቤተ መንግስት በማምራት ‹‹ከዛሬ ጀምሮ እንዲህ አይነት ቀልድ አልፈልግም! ለፕሬዘዳንትነት እንጂ ለኮሜዲያንነት አይደለም የቀጠርንዎት! ኮሜዲያን ብፈልግማ ኑሮ ክበበዉ ገዳን አስቀምጠዉ ነበር፡፡ ለዛሬ ጥፋቶት እጅ በጆሮ›› (እነደልጅነታችን ቅጣት) ቢላቸዉ… ‹‹አይ … ልጄ ልጄ ጆሮዬን እንዴት ብዬ? ባይሆን ጆሮዬን ከምይዝ ከዘራዬን አቀብለኝ… ከዘራዬን ልያዝና አጥፍቻለሁ ብዬ ደብዳቤ ልፃፍ›› አሉ ተብሎ ሲወራ ሰማዉ፡፡ ውይይ…. ሀበሻ ወሬ ሲፈትል እኮ ለብቻዉ ነዉ፡፡

ብቻ ጤና!!› አሉ ወይዘሮ ገላዬ… ዕድሜና ጤና ገና ስንቱን ያሣየናል፡፡ ወዳጄ ይኸዉ ለጉድ ፈጥሮን አይደል እንዴ በልማት ሠበብ የአቡነ ጴጥሮስና የምኒሊክ ሀዉልት ይነሣል ብለዉ በድፍረት ነገሩን፡፡ ወዳጄ ሙት አዲስ አበባን ብታያት እንደድሮ እንዳትመስልህ… በሚጀመሩ እንጂ በማይጨረሡ መንገዶቿ የተነሣ ፈራርሳ በቁፋሮ በአርኪሎጂስቶች የተገኘች ከተማ መስላልሃለች፡፡

እነሡ ምን ጨነቃቸዉ..በጀቱ እንደዉ ወደ ኪሣቸዉ ነዉ.. ተሠራ አልተሠራ፣ አለቀ አላለቀ ማን ቁብ ሠጥቶት!! ይባስ ብለዉ ይኸዉ ታሪካችንን ተራ በተራ ለማጥፋት ከፒያሣ ‹ሀ› ብለዉ ጀምረውልሀል፡፡ ማን ይናገራቸዉ.. ወጣቱ እንደሆነ ስለ ሀገሪቱ ትቶ በአርሴናልና በቼልሲ በድሮግባና በሜሲ እግር ኳስ ጥበብ እየተጣላ በጩቤ መተራረዱን እንደ ጀግንነት ቆጥሮልሀል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top