Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 2

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 2

የሸገር ወጎች 2  

አጩሌ –  ከሸገር

Tales Of Sheger

Tales Of Sheger

ዲያስፖራው ወዳጄ እንዴት ከረምክልኝ?እኔ የሸገሩ አጩሌ ቃሌን ጠብቄ ይኸው በሰአቴ ተገኘሁ፡፡ እኔ የምለው ወዳጄ የምርጫው ነገር እንዴት ነበር?መቼም እንደ እኛ ተጭበርብሯል… ይደገም ምናምን ብላችሁ ድንጋይ እንደማታነሡ እርግጠኛ ነኝ ለነገሩ ተወው የሚወረወር ድንጋይስ ሲኖር አይደል? ዲያስፖራው ቢወረውር ወይ አንቁላል አልያም ቲማቲም ነው እያሉ እዚህ የሸገር ልጆች ይፎግራሉ፡፡ ቲማቲም ስል ምን ትዝ እንዳለኝ ታወቃለህ? እኚያ ጎረቤቴ ወይዘሮ ገላዬ የስፔኖቹን አመታዊ የቲማቲም መወራወር ዜናን ያ ልማታዊ ቴሌቪዥን ጣቢያችን ሲያቀርብ አይተው ‹‹አዬዬ … መድሃኒአለም እዚህ አንዲቷ ፍሬ ሶስት ብር ከሃምሳ ገብታለች እኒህ ጡር የማይፈሩ መወራወሪያ አደረጉት ምነው ሃገራቸው የኮብል ድንጋይ ጠፍቶ ነው?›› ብለው እርፍ፡፡ የለመዱት ሰው በድንጋይ ሲወራወር እንጂ በቲማቲም አይደለማ፡፡

ወዳጄ መቼም አንዳንድ ነገሮች ሣወራህ ከመሳቅ እና ከመጫወት ይልቅ ተቀይመኸኝ ከሆነ ይቅርታህን አትንፈገኝ ምክንያቱም እኔ ያለሁት ሸገር አንተ ደግሞ አሜሪካ ስለሆነ ይሆናል፡፡ ለነገሩ እናንተ አሜሪካ ያላችሁ ዲያስፖራዎች ለሣቅ ቅርብ ናችሁ ይባላል ‹‹ይሔ የቢል ስትረስ ያለበት ሐበሻ መስከረም የተሠኘው ኮሜዲያን Whats’ up DC ሲል ሳይሆን ሙዝ ተላጠ ብለው መሣቅ ይቀናቸዋል›› እያሉ እዚህ ሀገር ቤት ያሉ ሰዎች ያሙዋችሁዋል፡፡ ተዋቸው ወዳጄ አመል ሆኖባቸው ነው አመል! ያው አመል አይለቅ አይደል? ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለፉም በኋላ ሀበሻ አመሉን አልተወም እንዲያውም እኛ ቀበሌ አርባቸውን ካላወጣን ብለው አርባ አርባ ብር አምጡ ተበለናል ብለው ጎረቤቶቼ ሲያወሩ ሠምቼ በቀበሌያችን ኮራሁ ሆ…ሆ…ይ ወዳጄ እንዴት አልኮራ…? አርባ ብሩንስ ተበድረንም ይሁን የአንድ ሳምንት የሆድ ወጪያችን ቀንሰን እንከፍለዋለን… እኔ የፈራሁት ያላዋጣ አርባ አርባ ጅራፍ…! ቢሉንስ ብዬ እኮ ነው፡፡ ለማን አቤት ይባላል ወዳጄ? የአንዱን ታሪክ አልሠማህልኝም? በል ካልሠማህማ ላውጋህ ምን ሆነ መሰለህ፡- ሰውዬው አንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት ቀጭን ጉዳይ ኖራው ቀን ከሌት መመላለስ ነው፡፡ ዛሬ ሃላፊው አልገቡም… ነገ አልተፈረመበትም… ከነገ ወዲያ ኃላፊው ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡

በቃ ሰውዬው በቢሮክራሲው ምክንያት ጉዳዩ ቀናት ሳምንታትን ደግሞ ወራትን ወለዱ ቢል… ቢሠራ ጉዳዩ ሊፈፀምለት አልቻለም አንዲያውም በመጨረሻ ፋይልህ ጠፍቶአል ብለውት እርፍ! ታዲያ ሠውየው በንዴት ቀጥታ ወደ ዋናው ሃላፊ ቢሮ በርግዶ በመግባት ‹‹ወደላይ አቤት እላለሁ! ለበላይ አሳውቃለሁ›› ቢል ሃላፊው ከት ብሎ ስቆ «ከኔ በላይ ያለው ጣሪያው ነው›› ብሎት አረፈልህ ወደጣሪያው እየጠቆመው፡፡ በቃ ነገራችን ሁሉ በጣሪያ ተሸፍኖ ቁጭ! ከጣሪያው ስር ደግሞ ወደታች ወደኛ መንደር ብቅ ብትል ደግሞ ወይ የአየለ እናት አልያም የአጉቾ እናት የልጃቸውን አመዳም ፀጉር እየደባበሡ «ድስት የለንም እንጂ፣ ቅቤ ቢኖረን ኑሮ ዱቄት ተበድረን ገንፎ እንበላ ነበር፡፡» እያሉ ልጃቸው እንቅልፍ እስኪወስደው ሲያጫውቱ ትሠማለህ፡፡

እና እንግዲህ በዚህ ኑሮ ላይ የቀበሌ አርባ ብር ተጨምሮበት አለቅን!! አለች ያቺ አውቆአበድ? እንዴ ለሀዘኑም ልክ ይረው አንጂ እሣቸው ሞቱ ብለን እኛ ማለቅ አለብን እንዴ? አሉላችሁ ደግሞ ምክንያት አገኘን ብለው በየቦታው በመፈክር ጋጋታ እራሳቸው ተጨንቀው እኛን ያጨናነቁን… ወዳጄ ፈጣሪ ያሳይህ «የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ራዕይ ለማሳካት የመቃብር ጉድጓዶችን በስፋት እንቆፍራለን!!›› የእገሌ ቤተክርስቲያን ጉደጓድ ቆፋሪዎች ማህበር፡፡ የሚል ማስታወቂያ ከሠውዬው ራዕይ ጋር ምን አገናኘው? ሌላ ቦታ ደግሞ ስትሔዱ ደሳሳ ጎጆ በር ላይ የሠውዬውን ፎቶ ሠቅለው ‹‹ራዕያቸውን ለማሳካት ምርጥ የደብረብርሃን አረቄ አስመጥተናል›› ይላል ዲያስፖራው ወዳጄ ሙት ይሄን ለማየት ጎጃም በረንዳ አከባቢ እና ሠባተኛ ዝለቅ ጉድ ታያለህ፡፡

ነገሩ «የእኛ ህዝብ እኮ ሣሙና የሆነ ህዝብ ነው!›› ያለውን ሠውዬ አስታወሠኝ አ…ሐ ያን ሰሞን የሠውዬውን ፎቶ የሚሸጡ ምላጭ የሆኑ ልጆች «ኑረውም የጠቀሙን ሞተውም የጠቀሙን ጀግና ፎቶቸውን በአምስት …በአምስት ብር» እያሉ እዛው! እዛው! በራቸው ላይ ቸበቸቡታ እውነትም ሣሙናዎች!

መንገድ የሚሠሩት ቻይናዎች እንኳን በአቅማቸው የሠውዬውን ፎቶ ለጥፈው ‹‹ጁንታኦ ሺሺ ያታኦ ሲንታሶል!›› ብለው ለጥፈውታል ትርጉሙ ምን እንደሆነ ባይገኝም ስገምት… ስገምት ግን «እነሆ አሁንስ ተስፋችን ማን ነው? እርስዎ አልነበሩምን?» አይነት መሠለኝ፡፡ እንዴ እሣቸው ለሠፊው የኢትዮጵያ ህዝብና ለቻይናዎች ምን ያልሆኑት አለ?እንዳለኝ ካድሬው ወዳጄ፡፡

በነገራችን ላይ ቻይናዎች አስመስለው በመስራት የሚወዳደራቸው አንደሌለ ለአንተ መንገር ለቀባሪ እንደማርዳትቢሆንብኝ በቀጥታ ወደ ጉዳዬ ልግባልህ ቻይኖቹ አስመስሎ በመስራት ከመራቀቃቸው የተነሣ እንዲህ አሉ ሲባል ሰማሁ ‹‹ የምን ሀዘን ማብዛት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በጣም የምትፈልጓቸው ከሆነ አንድ ሁለት ሳምንት ስጡንና እንስራላችሁ!»ወይ ቻይና! አያደርጉትም ብለህ አትሞኝ፡፡ በነገርህ ላይ ፎቶአቸው ‹መብረቅ መከላከያ› ተብሎ እንደ ተሠየመ ሠምተህልኛል? ው…ይ አልሠማህም እንዴ? የመቼህን!ነገሩ ምን መሠለህ እነዚህ ቀበሌ…ወረዳ ምናምን የሚባሉት ‹‹ንግድ ፈቃድ አድስ!… ግብር ክፈል!» እያሉ ህዝቡን የሚያጨናንቁበት ጊዜ አላቸው።

ታዲያ ምድረ ነጋዴ የሠውዬውን ፎቶ‹‹ራዕይህን እናሳካለን!›› ከሚል ጽሑፍ ጋር ንግድ ቤቱ በር ላይ ልጥፍ! ታዲያ ሰውዬው ያሉበት ፖስተር ካለ ቀበሌዎች ‹‹ይሔ ሐቀኛ ነጋዴ ነው›› በማለት ያልፋታል አሉ (ይሔም የሠውዬውን ራዕይ ማሳከት ይሆን እንዴ?)

እንዲህም ሆኖ ይሔ ሣሙና የሆነ ነጋዴ ምስላቸውን ‹‹መብረቅ መከላከያ›› የሚል ስም አውጥቶለት አረፈው ውይ ሕዝቢ ሃበሻ! ነው ያለቺኝ ያቺ ወዳጄ? (አትሣቅ ወዳጄ!)ሌላው ግርም የሚለኝ ነገር ምን መሠለህ በሬድዮም ይሁን በብቸኛው የቴሌቭዥን ጣቢያችን ላይ በእያንዳንዱ ፕሮግራም ላይ የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስቴር ስም ካላነሡ የማይሆንላቸው እበላ ባይ ጋዜጠኞች መበራከት ነው።

እኔማ ግርም ቢለኝ አንዱ ጋዜጠኛ ወዳጄን   «እንዴት ነው ነገሩ የሣቸውን ስም ካልጠራችሁ ከደሞዛችሁ እንቆርጣለን፡፡» የሚል መመሪያ ወጣ እንዴ? ብዬ እስከ መጠየቅ ሁሉ ደርሻለሁ ወዳጄ ሙት አሁን በቀደም ዕለት አንዱ የሜትዎሮሎጂ አቅራቢ በቴሌቭዥን እንዲህ ሲል ሠማሁት ‹‹ውድ ተመልካቾቻችን በጎዴ ከፊል ደመናማ፣ በአፋር ፀሐያማ ፣በትግራይም ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ሲኖር በኦሮሚያና አጎራባች ክልሎች ላይ ልክ እንደጠቅላይ ሚኒስትራችን የቀብር ቀን ዝናባማ ሆኖ ይውላል!›› በቃ የሆነ ነገሩን ስታየው ከሠውዬው ሞት በፊት ዝናብ ዘንቦ የማያውቅ አስመሠለው፡፡

ዲያስፖራው ወዳጄ አትፍረድብኝ የዘይት ፋብሪካ ሳይሆን የቀለም ፋብሪካ በበዛበት ሀገር ላይ ሆኜ እንዲህ ብብከነከን አትዘንብኝ፡፡ የኑሮ ልዩነታችን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሠፍቷል እንደማህተመ ጋንዲ ምድር፡፡ አይገረምህና ለመኝታ ቤቱ በር እጄታ ወርቅ ያስገጠመ ደፋር ሐበሻ ሁሉ አንደተፈጠረ ስነግርህ እያዘንኩ ነው፡፡(ምን ማዘን ብቻ ሆዴ ቦጭ…ቦጭ እያለ ጭምር)

ለዚህ አይደለ እንዴ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን እስካሌድ እና ሀመርበል ፓርሽና ፌራሪ የታዘቡት ጅቡቲያውያን ‹‹እነዚህ ሠዎች መኪና ነው እንዴ የሚበሉት?›› አሉ እየተባለ የሚወራው፡፡ለምንኛውም የእድገቱ ፍጥነት፡- የነዳጅ ዋጋ እንደ አቦ ሸማኔ፤ የወርቅ ዋጋ እንደካንጋሮ፤ የምግብ ዋጋ እነደሚዳቆ፤ የመብራት ስልክ እና የውክፍያ ዋጋ እንደ ጥንቸል የኔ ደሞዝ እንደ ኤሊ እየተጓዙ ነው (በል ወዳጄ ደግሞ ቦተሊካ ተናገርክ ብለው ኤሊዋንም እንዳይቀሙኝ፡፡ ደህና ሠንብትልኝማ የወር ሠው ይበለን እንጂ ገና አወጋሀለሁ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top