Free songs
Home / Tales of Sheger / Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 1

Tales of Sheger: የሸገር ወጎች 1

የሸገር ወጎች 1  

አጩሌ –  ከሸገር

Tales Of Sheger

Tales Of Sheger

ከወር በፊት… አዲስ አበባ ከተማ በሰሚ ሰሚ በሚናፈሱ ወሬዎች ከእግሯ እስከ ራስ ፀጉሯ ተወጥራለች፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት አዳዲስ ወሬዎች በታክሲ ውስጥ፣ በካፌዎች ውስጥ፣ በመንገድ ላይ ሌላው  ቀርቶ የሕዝብ ሽንት ቤት ውስጥ ሳቀይር እንደ ጉድ ይፈበረካሉ፡፡

ከወር በፊት… አዲስ አበባ በአንዳች ድብርት ተውጣለች አንዳች አዚም ተጫጭኖአታል፣ የሚወራው ወሬ ክንፍ ያለው ይመስል እንደጉድ ይበራል፣ ፒያሳ የተወራው በደቂቃ ልዩነት ቃሊቲ ወይም ኮተቤ ከሠማህ አትገረም ይሄ አዲስ አበባ ነው፡፡ ከተማዋ በወሬ የስንግ ተይዛለች አንዳንዱ በኢ.ቲ.ቪ (ልብ አርጉ ኢ.ቲቢ እንዳላልኩ) ሌላው ደግሞ በፌስቡክ እየማለ የሠማውንና ያየውን ጨምሮ ጨማምሮ ለወሬው ጅራትና ቀንድ አብቅሎለት ለሌላው ይናገራል፣ የሠማው ደግሞ ከታማኝ ምንጭ ያገኘሁት ነው በማለት ያሠማል (ፈጣሪ ያሳያችሁ ኢቲቪ ታማኝ ምንጭ ሲባል ድክም አያደርጋችሁም?)

አሁንም ከወር በፊት …‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮማ ውስጥ ናቸው አሉ እንዲያውም አሜሪካ አገር የሚገኝ ሆስፒታል ናቸው” ይላል አንዱ።

‹‹እረ ባክህ? በቀደም ዕለት ቤተ መንግስት ሆነው ስራቸውን እየሠሩ ነው አልተባለም እንዴ?  ይላል ሌላኛው የአንዱን ጋዜጣ ስም እየጠቀሰ፣  ተው ባክህ እኚያ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮቹ ሰውዬ ድርጅቱ ከትግል ጊዜ ጀምሮ አብሮት ያለ የድብቅነት ባህርይ ምናምን አለው ሲሉ አልተሠማህም አንዴ? ይጠይቃል፣

‹‹የትኛው ደርጅት?››

‹‹ሆሆይ ወንድሜ ያው ያለው አንድ ደርጅት ነው!››

‹‹ኢህአዴግን ማለትህ ነው?››

‹‹ሽሮዬን ልብላበት ምናለ ባትነካካኝ?›› በፍርሀት

ከፖለቲካው ወጣ ብለው ደግሞ ስለ ሰውዬው ጤንነት ይቀጥላሉ…

‹‹እኔ የምለው ቆይ አንተ ግን ከየት ሠማህ?››

‹‹ሙት!›› ለማንም አትናገር እንጂ ያቺ አሜሪካ ያለችው እህቴ የምትሠራበት ሆስፒታል ውስጥ ነው ያሉት አሉ… ኧረ እንዲያውም አይታቸዋለች…

‹‹ሂ ድ…ድ…ድ…ድ…››

በቃ ይኽን የሠማ ሠው ከመስሪያ ቤቱ ወጥቶ ቤቱ እስኪደርስ ደርዘን ለሚሞሉ ወዳጆቹ ‹‹ሠማህ ወይ? ለማንም አትናገር እንጂ ሠውዬው በጠና ታመዋል አሉ አረ… አንዲያውም ኮማ ውስጥ ናቸው አሉ! (ይህቺ የፈረደባት ኮማ በየቦታው በዝታ ጉድ አፈላችብን እኮ ወዳጆቼ!) ከዚያማ አትናገር የተባለው በተራው ለማንም አትናገር እያለ አዲስ አበባ እንዲሁ በወሬ ትናጥ ገባች፡፡

ከወር በፊት… ‹‹የመከላከያው ሠውዬ ኮማ ውስጥ ናቸው አሉ… ከቴሌቭዥን መስኮት ከጠፉ እኮ ሠነባበቱ ቴሌቭዥኑ የሚያሣየው ድሮ የተቀረፁትን ነው አሉ (አቤት ይህቺ አሉ የምትባል ነገር ባትኖር ምን አባታችን ይውጠን ነበር? ለነገሩ ከማን ተማርነው? አንደንድ የእንትን ነዋሪዎች… አንዳንድ የእንትን ማህበረሰብ አባላት የሚለን እውነት አንነጋገር ከተባለ ኢ-ቲቢ አይደለ? ይቅርታ ወዳጄ አ.ቲ.ቪ እና ኢ-ቲቢ እየተምታታብኝ የተቸገርኩት እኔ ብቻ መሰልኩህ? ድፍን የሀበሻ ዘር እኮ ነው ወ…ይ…ኔ ኢቲቪ እንዲህ ሙድ መያዣ ትሆኝ?) ኮማ ውስጥ ናቸው ስለ ተባለው ሰውዬ ጨዋታ ሳይዘጋ አንዱ ብድግ ብሎ ‹‹እንዴ ምን ሆናችሁ ነው?… ሰውዬው ሞተዋል አሉ… አንዲየውም በቀደም እለት ከአየር መንገድ አንድ አስክሬን  የወጣው የዕሳቸው ነው ሲባል ሰምቻለሁ ሊያውም ከታማኝ…

ታማኝ?…ታማኝ…ማ? በየነ? (ጉድ ፈላ)

‹‹ሆ…ሆ ሽሮዬን ልብላበት!›› ከተናግሮ አናጋሪ ይሰውረኝ እያለ

ዲያስፖራው ወዳጄ እኔ ግርም የሚለኝ ብቸኛው ብሔራዊ ቴሌቭዥኑም… ተቃዋሚውም፣ደጋፊውም፣መሀል ሰፋሪ ተብዬውም ይሄ ታማኝ ምንጭ የሚሉት ማንን ይሆን? እንደው አንድ የሆነች ነገር መደበቅ ሲፈልጉ ምንጮች እንደገለፁት ብለው ድፍን ያደርጉብናል ውይ ክፋት! እንዳናጣራ እኮ ነው፡፡ አሁን  በቀደም እለት እኚያ ጎረቤቴ ወ/ሮ አስካለችን ሌላኛዋ ጎረቤታችን ቀበሌ ዘይት መጥቷልና ይውሰዱ ብትላቸው ምን ቢሏት ደስ ይልሀል ‹‹ እኔ የምለው በቴሌቭዥን ነው የሠማሽው ወይስ ከታማኝ ምንጭ? ብለው እርፍ!!

ስለዚህ ጉዳይ በሁዋላ አጫውትሀለሁ አሁን ወደ ተነሳንበት ርዕስ የኋላ ማርሽ አስገበተን እንንዳ…

በቃ የወሬው ፍጥነት አንድ ፖስታ ከሚቀቀልበት ደቂቃ በፈጠነ ሁኔታ ተውልዶ አድጎ ለአቅመ ሀሜት ደርሶ ቁጭ! መንግስት በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህና ናቸው ይላል (መንግስትን ማመን ቀብሮ ነው! አንዴ ፓርቲው ድብቅ ነው ይለናል ሌላ ጊዜ ደግሞ… የሚሉ ባይጠፉም!) አንዳንዶቹ እንዲየውም ከተሜው የማያውቀውን የውጭ ሚዲያ ጠቅሰው እየማሉ አርፈዋል ብለው እርፍ! ይሔኔ ነው እንግዲህ ምደረ አዲስ አበቤ በሁለት ጎራ ተከፍሎ እውነት ነው!… አንዴት ተደርጎ? ሀሠት ነው! እየተባባለ የጦፈ ክርክሩን የያዘው ጠላቶቻቸው እርር ይበሉ ብሎ ነው መሠል ከመስከረም በፊት ወደ ቀደመ ስራቸው ይመለሣሉ የሚለውን በቴሌቭዥን ሠማን (አደግመዋለሁ! አሁንም አደግመዋለሁ ኢቲቪን ያመነና ጉም የጨበጠ አንድ ነው!!) እያሉ የሚፎትቱትን ወይም እንደጋዜጠኛና ደራሲ መሀመድ ሠልማን ኢቲቪን ‹‹ቁጩ›› እያሉ የሚጠርዋትን ትተን እኛ ግን እነሆ ኢቲቪን አመንን ያመነና የተጠመቀ … እንዲሉ (ለነገሩ ባናምንስ ምን እንመጣለን?)

ነገር ግን ተሸወድን! ወዳጄ ሙት እልሀለሁ ኢቲቪ ሸወደችን!! የጳጳሱን ሞት ስንሰማ እ…ን..ዴ ሞት አራዳው እንደ እግር ኳስ ጨዋታ አጠቃቀስኩ ብሎ ሸወደን ማለት ነው? እሱ ግን ለምንድነው እንዲህ የሚያጓጓን? እያልን ስናማው ከምታሙኝስ ይሄው አለ መሠል በማለዳ የሰውዬውን … የዋናውን ማለፍ በዛችው ይመጣሉ ብላ በነገረችን የቀበሌያችን ቴሌቭዥን በእንጉርጉሮ ታጅቦ ተመለከትን፡፡

ዲያስፖራው ወዳጄ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት በቴሌቭዥን የፉገራ ወሬ የተሸወደ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ሲነገረው ምን እንዳለ ሰምተኸል? ሲቀበሩ ካላየሁ አለምንም!! እውነቱን እኮ ነው በኢቲቪ ዘይት ተትረፍርፉዋል… ስኳር በየቀበሌው ተከማችቶልሀል ተብሎ ቀበሌ ቢሄድ ቀበሌዎች ፍርፍር ብለው ሳቁ አሉ፡፡ ስኳር የለችም ዘይትን ከፈለጉ የሚቀጥለው ዓመት ብቅ ይበሉ እየተባለ ቢነገረው እንዴት ነው ነገሩ… ማታ በኢቲቪ ተነግሮ? ቢል የሚያገኘው መልስ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ታዲያ እዚህ ምን ያስመጣሀል ሂድና ኢቲቪ ስኳርና ዘይት ይሽጥልህ ተብሎ መልስ ይሠጠዋል፡፡ ታዲያ ይሄ ህዝብ ሠውዬውን ሲቀብሩ ካላየን ወይም ካልቀበርን አናምንም ቢል ይፈረድበታል? በፍፁም! በፍፁም!!!

ወዳጄ ያው ቀብሩን በቲቪም ይሁን በሌላ መንገድ ተከታተለኸዋልና እሡን በመድገም ወጌን አላቆረፍድብህም እኚህ አዲሱ በሳቸው ተተክተዋል እየተባለ የሚነገርላቸው ሰውዬም ጠቅላይ ሚኒስትር የምሆን ከሆነ ብለው ሶስት ቅደመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል አሉ እነዚህ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ካልተሟሉልኝ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ፕሬዝዳንትም አልሆን ብለዋል፡፡(በፕሬዝዳንታችን ላይ የምታሾፉ ዲያስፖራዎች እረባካችሁ ቀልዱን ቀነስ አድርጉት) ከቀብሩ በሁዋላ አንዱ ምን አለኝ መሰላችሁ ‹‹ፕሬዝዳንቱ መለስ የት ጠፋ? ብለው እየጠየቁ ነው! አሉ ቢለኝ ተገርሜ ‹‹ አንዴ ምነው ወዳጄ? የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት በቴሌቭዥን ነገረውን ብለው ‹‹ ባክህ እሳቸው ካነበቡት በሁዋላ ወዲያው ረስተውት መቼ ነው የሚመጣው? ብለው ሲጠይቁ ነበር አሉ›› ብሎኝ አረፈው ምን ይሄ ብቻ እሳቸው ባሉበት የሚተከል ችግኝ ዘጠና ፐርሠንቱ አይፀድቅም! አለኝ ‹‹እንዴ ይሔ እንኳን የጠላት ወሬ ነው ብለው ከት…ከት…ከት ብሎ ስቆብኝ ‹‹አንድ ተክለው ስድስቱን ደፍጥጠው ስለሚሄዱ እኮ ነው፡፡ አይለኝ መሠለህ ጥርሱ ይርገፍና!!

እንዲህም ሆነ የናፍቆት ኢትዮጵያ መፅሄት ወዳጄ መሠናበቺዬን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቅድመ ሁኔታን በ«አሉ» የሠማሁትን ላካፍልህ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሆን ከተፈለገ እድሜዬ እንዲያጥር አልፈልግምና፡-

ዋልድባና ገዳም የሚባል ነገር አታምጡብኝ

መጅሊስና ምርጫ የሚሉ ርዕሶችን አታሠሙኝ

አበበ ገላው የሚባል ሠው ባለበት የትም ይሁን የትም እንዳትጠሩኝ፡፡ (አትሳቅ ወዳጄ የሚያስቅ ምንም የለምና)

እኔ ግን እላለሁ ላለነውም ላረፉትም ነፍስ ይማር! ወዳጄ ዘንድሮ በቁም እያሉ ተዘካር ማውጣትን የመሠለ ትልቅ ነገር የለም ለነገሩ የውሸት እየኖርን የእውነት እየሞትን ተዝካራችን ሰርጋችን ባይሆን ነው? ሰምተኸል! በል ወዳጄ ለዛሬ በዚህ ልሰናበትህ በሚቀጥለው በሌላ ወግ እጠብቅሀለሁ ሠላምህ ይብዛ!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top