Free songs
Home / Selayu / Selayu 8: የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ወጎች

Selayu 8: የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ወጎች

Selayu

Selayu

የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ወጎች

ዛሬ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድናችንን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን እንሰልላለን፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቀልድ አዋቂ እና አንዳንዴ የሚናገሩት ሁሉ የሚያስቅ ላመኑበት ነገር ወደ ኋላ የማይሉ ቆራጥ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ አንድ ስሙን የማስታውሰው ጸሐፊ ስሙን ባልዘነጋሁት መጽሔት ላይ አሰልጣኙ የፈጠሯቸውን ሳቅ የሚያጭሩ አጋጣሚዎች ሰብስቦ እንደሚከተለው አስነብቧል፡፡

“እዚህም አይያዝም እኮ”

  አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች በተለየ ለሙሉዓለም ረጋሳ ክብር አላቸው ይባልላቸዋል፡፡ ይሄንን ተጫዋች በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እንጂ በክለብ ላይ አሰልጥነውት አያውቁም፡፡ ለብሔራዊ ቡድን ሲያሰለጥኑት ምን መስራት እንደሚችል ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ተቃራኒ ሆነው ሲገጥሙት ይፈራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ኒያላን እየሰለጠኑ ሳለ የሙሉዓለም ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመግጠም ይገደዳሉ፡፡

ከጨዋታው በፊት ምን ማድረግ እንዳለባቸው “ቦርድ” (ነጭ ሰሌዳ) ላይ በማርከር እያስረዱ ነው፡፡ ስለ ሁሉም ተጫዋቾች ሚና በደንብ አስረዱ፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሳወቁ፡፡ ልክ ሙሉዓለም ላይ ሲደርሱ ተጫዋቹ ቁልፍ እንደሆነ ለማሳወቅ ለማክበብ ጣሩ፡፡ ማርከሩ ከእጃቸው ላይ ወደቀ፡፡ “ይሄውላችሁ ተጫዋቾቼ ይሄ ልጅ እዚህም እኮ አይያዝም” በማለት ኮስተር ብለው ተናገሩ ተጫዋቾቹን፡፡ እንደሚፈሩት ያወቁት የእርሳቸው ተጫዋቾች ግን ከመሳቅ ወደ ኋላ አላሉም፡፡

“እንኳን ናይጄሪያን መቼ እርሻ ሰብልን ሰራሁ”

ሰውነታቸው ደልደል ያለና ረጃጅም ተጫዋቾችን መርጠው አዲስ ቡድን አዋቀሩ፡፡ የቡድኑ ተጫዋቾችን መርጠው አዲስ ቡድን አዋቀሩ፡፡ የቡድኑ ኮሚቴዎች መጥተው ስለ ቡድኑ ሲጠይቋቸው “ናይጄሪያን የመሰለ ቡድን ሰርቻለሁ” ብለው አስረዱ፡፡

ሆኖም ግን ቡድኑ በመጀመሪያ ጨዋታ በበርካታ የጎሎች ልዩነት ሲሸነፍ  መታለላቸው የገባቸው ሰውነት ተጨዋቾቻቸውንና ኮሚቴውን ሰብስበው እንኳን ናይጄሪያን መቼ እርሻ ሰብልን ሰራሁ?” ብለው መሻሻል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

“ጦሩ ሲወረወር…ደረቴ ላይ ሲሰካ”

  በሚሰራው ቡድን ከፍተኛ እምነት ያለው ሰው ታውቃላችሁ? በቃ አሰልጣኝ ሰውነት በሚሰሩት ቡድን በጣም እምነትን ያሳድራሉ፡፡ በኒያላ የገጠማቸውም ይሄው ነው፡፡ በሰሩት ቡድን ከፍተኛ እምነት ስለነበራቸው እየተሸነፉ እንኳን ተጫዋቾችን መቀነስ አልፈለጉም፡፡ በስተመጨረሻ ተጫዋቾች የግድ መቀነስ እንዳለባቸው ይሄንን ማድረግ ካልቻሉ የስንብቱ ዕጣ ፈንታ ለእርሳቸው እንደሚደርሳቸው ሲነገራቸው ተጫዋቾቻቸውን ለስብሰባ በመጥራት “ጦሩ ሲወረወር ደረቴ ላይ ሲሰካ…ጦሩ ሲወረወር ደረቴ ላይ ሲሰካ…አሁን ደረቴም ሳስቷል…ጦሩንም የምቀበልበት ቦታ አጥቷል፡፡ በቅርቡ ሶስት ጦሮች ይወረወራሉ…እኔ አጎንብሼ “ሽል” ብያለሁ…ሦስት ተጫዋቾች ላይ ያርፋል” በማለት ሦስቱ ተጫዋቾች ተቀናሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ እግረ መንገዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

“ፎቶ ልታነሳ …ወይስ ብፌ?”

  በቅርቡ የተፈጠረ ነው፡፡ ሱዳንን ረትተው ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፉ በኋላ በሸራተን አዲስ የራት ግብዣ ነበር፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ምግብ ሊያነሱ ሲንቀሳቀሱ   አንድ ጋዜጠኛ እየተከታተለ ፎቶ እያነሳ አስጨነቃቸው፡፤ ይሄኔ ሰውነት “አንተ ሰው ዛሬ የመጣኸው ቡፌ ልታነሳ ወይስ እኔን ፎቶ ልታነሳ?” ብለው ምግብ ያነሱትን እና መጉረስ የጀመሩ ተጫዋቾቻቸውን ሁላ በሳቅ ትን ሊያስብሏቸው ነበር፡፡

“እኔም ሱፍ አድርጌ ልዙር እንጂ”

  ቡድናቸው በተከታታይ እየተሸነፈ ሰውነት ተቸገሩ፡፡ የአሰልጣኝ አቻዎቻቸው እና ጓደኞቻቸው ደግሞ ድል ይቀናቸው ጀመር፡፡ ይሄኔ ሰውነት ልምምድ ላይ ለተጫዋቾቻቸው “እባካችሁ..እባካችሁ..አንዴ አሸንፉና እኔም እንደ ተጫዋቾቼ ሱፍ አድርጌ አዲስ አበባ ስታዲየምን ልዙር” ብለው በሽንፈት ባዘነው ቡድን ላይ ሳቅን ፈጥረዋል፡፡

ሰውነትና ቅፅል ስሞች

  መንግስቱ አሰፋ የአባቱ ስም እስኪረሳ ድረስ “መንግስቱ ማሲንቆ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህን ቅፅል ስም የሰጡት ሰውነት ናቸው፡፡ አሰልጣኙ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው የሰጧውን ቅፅል ስሞች ዘርዝሮ መጨረስ በጣም ይከብዳል፡፡ በአሁኑ ብሔራዊ ቡድን እንኳን   ለተለያዩ ተጫዋቾ የተለያዩ ስያሜዎች ሰጥተዋል፡፤ ከስዊድን መጥቶ በቶሎ አማርኛ የለመደውን የሱፍ ሳላህን “ጎንደሬው” ሲሉት፣ የውትድርና ማዕረግ ያለውን ዓይናለምን “ሳጅን” ብለው ይጠሩታል፡፡ በሁሉ ነገር ላይ ተሳትፎ የሚያደርገውን በኃይሉ አሰፋን “ጎግል” ሲሉት ደጉ ደበበን “ጠንቃቃው” በማለት ሰይመዋቸዋል፡፡

“ፆም ሲፈታ ሥጋ መግዣ አላጣ…”

  ይሄም በቅርቡ የተከናወነ ነው፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ይሄንን ብሔራዊ ቡድን ሲረከቡ “ጊዜያዊ” ነበሩ፡፡ የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ይመጣል ተብሎ ይጠበቅ ስለነበር “ጊዜያዊ” የሚለው ስያሜ አለቅ  አላቸው፡፡ በዚህ ላይ ጋዜጠኞች በተለያዩ ጊዜ ስንብታቸው የማይቀር መሆኑን ያስታውሷቸው ጀመር፡፡ አንድ ወጣት ጋዜጠኛ ይሄንን ጉዳይ ሲያነሳባቸው “ሰውነት የሚፈራ መሰለህ እንዴ…ፆም ሲፈታ እንደሆነ አንድ ኪሎ ሥጋ መግዣ አላጣ…ምን ታስፈራራኛለህ?” ብለውታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top