Free songs
Home / Selayu / Selayu 16: የልማት ሠራዊት ግንባታ

Selayu 16: የልማት ሠራዊት ግንባታ

Selayu“ልማታዊ መንግሥታችን ”ሰሞኑን… ምን ሰሞኑን ብቻ ካለፈው ዓመት ማለቂያ ጀምሮ የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎችን፣ ካድሬዎችንና የመንግሥት ሠራተኞችን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር በመመደብ “ልማታዊ የትምህርትና የሥራ ሠራዊት”ን ለማፍራት እያሠለጠነ መሆኑን ሀገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው፣ ተቃዋሚ ያሽሟጠጠው ሐቅ ነው፡፡ ኢቲቪ/ኢቢሲ አልዘገበውም እንጂ ተቃዋሚዎች ጉዳዩን “የምርጫ ሠራዊት ግንባታ ነው” እያሉ ነው አሉ፡፡ (…እናቅሻለን እናቅሻለን እናቅሻለን…መሆኑ ነው ነገሩ፤)

በነዚህ ሥልጠናዎች በተሳታፊዎች በድብቅም ሆነ በግልጥ የተነሡ ሐሳቦችን በስለላ መረባችን ቃርመናል…

በመጀመሪያው ዙር አንዲህ ተባለ…

…ምርጫውን ምክንያት በማድረግ ነፍ ተቃዋሚዎች ከየሥርቻው በመፈልፈል የልማታዊ መንግሥታችንን ዲሞክራሲያዊነት አረጋግጠዋል፡፡ ኧረ እንደውም አሁን አሁን ፓርቲ አቋቁሞ መቃወም ምርጥ የሥራ ዕድል ሆኗል፡፡ በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ነፍ ናቸው፡፡ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ለመቃወም የተቋቋሙም ነፍ ናቸው፡፡ ኢህአዴግንም፣ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎችንም፣ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎቹን የሚቃወሙትንም፣ ራሳቸውንም ለመቃወም የተቋቋሙም ነፍ ናቸው፡፡ ብቻ ከሰሞኑ የሚያበላ ፊልድ መቃወም ነው አሉ፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ምርጫ የሚመጣው በጣም ዘግይቶ በመሆኑና በጣም ከመዘግየቱም የተነሣ ሥራ እየፈቱ ስለሆነ ምርጫው ቶሎ ቶሎ እንዲደረግ በሚል በየአምስት ዓመቱ መሆኑን ተቃውመው የተቃውሞ ሰልፍ ሊወጡ መሆኑን የስለላ መረባችን ደርሶበታል፡፡ (እዚህ ጋ የለንበትም ኢህአዴጋችን ሰልፍና ዘራፍ አይወድም አሉ፤…ሞኞች! በሀገራችን ሰልፍ እንደመቃወም ቀላል መስሏቸዋል፡፡ በርግጥ እንደ የዳቦ ቤት ሰልፎችና የታክሲ ሰልፎች አይነቶቹ ብዙ ሰልፎች ቀላል ብቻ ሳይሆኑ ግዴታ ቢሆኑም ሰላማዊ ሰልፍ ግን ውጉዝ ከመአሪዎስ ነው፡፡)

ተቃዋሚዎች በኢቲቪ መቅረብን ይቃወማሉ፣ በኢቲቪ አለመቅረብንም ይቃወማሉ፡፡  አንዱ ተቃዋሚ አውቆ በስህተትም ሆነ ሳያውቅ በድፍረት በመንገድ ሲያልፍ እንኳን በኢቲቪ ከታየ “ተቃዋሚ” የተሰኘውን የክብር ማዕረጉን በተቃዋሚዎች ይነጠቃል፡፡  የነጠቁትን መልሶ በመቃወም ግን ምርጥ ኢንተርፕሩነር መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ የነካው ሁሉ የረከሰ ነውና ፀበል ይረጭ ይላሉ፡፡ ነገር ግን ፀበል ለመርጨት ፀበሉም ቄሱም የላቸውም፡፡ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ በፊት የነበረው ዘመን ሁሉ ወርቃማ ዘመን ነው፤ ከኢህአዴግ በፊት የነበረ መሪ ሁሉ ጻድቅ ነው ይላሉ፡፡

ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ን ይቃወማል፡፡ (ከኢህአዴግስ መቀየምና መቃወም ይሠውረን)፡፡ የግሉን ፕሬስ ይቃወማል፡፡ እነሆ በሀገራችን ሁለት ዐይነት ኢትዮጵያዎች አሉ፤ የኢቲቪዋ ኢትዮጵያና የግሉ ፕሬስ ኢትዮጵያ፡፡ (የኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ የት ይሆን ያለችው?) ኢህአዴግ የኖረበት ዘመን ወርቃማ መሆኑን ለማብሠር የሕዳሴው ዘመን ይለዋል፡፡ በሕዳሴውም ዘመን ለመመረጥ ራሱን ብቸኛው እጩ ያደርጋል፡፡

የተቃዋሚዎችን ነፍስም ከመሸምደድ ኢህአዴግዬን ምረጥ!

አክተር አይሞትም ባክህ… ተዋናይ ቢበዛ ለድምቀት ነው፡፡

በሁለተኛው ዙር እንዲህ ተባለ…

ኪራይ ሰብሳቢነት መውደም አለበት፡፡ መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማውደም ብርቱ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡

እዚህ  ጋ  ጣፋጭ ወግ ተነሳች… እውነተኛ ታሪክ ናት ተብላለች፡፡

…በአንዱ ክልል ነው አሉ፡፡ መንግሥት ትምህርት ቤት እንዲሠራ ዳጎስ ያለ በጀት ይመድባል፡፡  የክልሉ ሰዎች በጀቱን እንደተቀበሉ ሥራውን አንደጀመሩ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ በየዓመቱ እየተሠራ እንደሆነ በተቀናጀ ሁኔታ ሪፖርት ይደረጋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ያረፈበት ካሬሜትር፣ የኮንትራክተሩ ዐይነትና ልምድ፣ የቁፋሮው አድካሚነትና የመሠረቱ ብዙ ማስወጣት፣ የሲሚንቶ መወደድ… ሁሉም በተራ ተገለፀ፡፡ በመጨረሻም ትምህርት ቤቱ ያልቅና ይመረቃል፡፡ ተማሪዎች እየተማሩበት ነው፡፡ በክልሉ ትምህርት ቤት በመሠራቱ ሁሉም መደሰቱን ይገልጣል፡፡  ይሄ ሁሉ ታዲያ በሪፖርት ነው፡፡

አይደርስ የለም አንድ ቀን ደረሰችና የፌዴራሉ መንግሥት አካል የሆነ ኮሚቴ ትምህርት ቤቱን ሊጎበኝና የክልሉን ባለሙያዎች ሊያመሰግን ወደክልሉ ይሄዳል፡፡ ለኮሚቴው ጥሩ አቀባበል ተደርጎ ትምህርት ቤቱን ካሠሩት መካከል አንዱ ሊያስጎበኛቸው ይዟቸው ይወጣል፡፡

ቢሄዱ ቢሄዱ መንገዱ አያልቅም፡፡ “ብዙ ሩቅ ነው እንዴ አቶ…”

“ደርሰናል እዚች  ጋ  ነው”

አሁንም ይሄዳሉ… ይሄዳሉ፡፡

አስጎብኚው ተናገረ “ይሄ ጤና ጣቢያ ነው… ያኛው ደግሞ ኳስ ሜዳ ነው…እ… ይሄ ደግሞ የእርሻ መሬት ነው”  አሁንም ይሄዳሉ፡፡

“እዛ ጋ ከነ ግርማ ሞገሱ የምታዩት ደግሞ የምንኮራበት ተራራችን ነው… ይሄ ሁሉ የመልካም አስተዳደራችን ውጤት ነው”

“ትምህርት ቤቱ ከዛ ጀርባ ነው?” ከኮሚቴው አባላት መካከል አንድ የተሰላቸ ድምጽ በጉጉት ጠየቀ፡፡

“ደርሰናል… ” አሁንም ይሄዳሉ፡፡ “እዛ ጋ እንደ አዞ ተጠማዞ የምታዩት አብረቅራቂ  መንገድ ዋናው አውራ ጎዳና ነው…ባሻገር ያለው ኩሬ…”

የኮሚቴው ኃላፊ በቁጣ አቋረጡት  “አቶ እገሌ እኛ የመጣነው ትምህርት ቤቱን ለማየት እንጂ መልክዓ ምድር ለማድነቅ አይደለም…አሁን ትምህርት ቤቱን ታሳየናለህ አታሳየንም?”

“ኧረ አሳያለሁ”

“የታል ታዲያ”

“አባቴ ይሙት አሁን እዚህ ጋ ነበር…የት እንደሄደ አላውቅም”

በሦስተኛው ቀን እንዲህ ተባለ…

መልካም አስተዳደር የአገልግሎታችን መሠረት መሆን አለበት፡፡ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ያለው ደንበኛን የማስተናገድ ባሕል ያሳፍራል፡፡ አንዳንዶቹ መሳደብ ነው የሚቀራቸው፡፡

የሥራ መመሪያው ራሱ የመልካም አስተዳደር ማነቆ ነው፤ ብዙዎቹ አገልጋዮች መመሪያው አይፈቅድም በማለት ካለቅንነት የሚያጉላሉትን ሕዝብ ብዛቱን ቀበሌ ይቁጠረው…

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top