Free songs
Home / Selayu / Selayu 14: አከራዬ አዩኝ

Selayu 14: አከራዬ አዩኝ

 

ከቅዳሜSelayuያት በአንዱ ስሰልል ውዬ ወደ ቤቴ ስገባ የአከራዬ ሕፃናት ልጆች በአንድነት “ሰላዩ… በቲቪ ዐየንህ” በማለት እየተቀባበሉ ጮኹ፡፡ ክው አልኩ፤ እንዴት ክው አልል? በቲቪ መታየትን ከአከራይ ወገን ከመስማት በላይ ለተከራይ ምን የሚያስደነግጥ ነገር አለ? ወዳጄ የዘንድሮ አከራይ እኮ እንኳን በቲቪ በባጃጅ ገቢና ካየህ አለቀልህ… በነጋታው “ኪራይ ጨምር” ነው፡፡ እንኳን ኢቢሲ አሳምሮህ ካልሲ አስውቦ ካሳየህ … በማግሥቱ “ጨምር” ነው፡፡

አይ EBC የሥራህን ይስጥህ፤ ምናለ እንደው እኔን ያሳየህበት ስክሪንህ ድርግም ባለ፡፡ እንደው ይሄ ተንኮል ነው እንጂ በተጣበበ ልማታዊ የአየር ሰዓት አከራዮቼ ቲቪ ሲከፍቱ ጠብቆ እኔን ምስኪኑን ተከራይ ማሳየት ምን ይባላል? አሁን የሚታይ ሰው ጠፍቶ ነው? እሺ ሰውስ ቢጠፋ የሚታይ ያልተመረቀ መንገድ ጠፍቶ ነው? መንገድስ ይጥፋ እሺ የሚታይ ለም እርሻ ጠፍቶ ነው? እርሻም አይኑር ተዉት… አባይን ገዳቢ ወይም አባይን (አባይ እዚህ ጋ ላልቶ ይነበብ) ዘጋቢ ጠፍቶ ነው? ዘጋቢው ቢጠፋንኳ ዘጋቢ ፊልም ጠፍቶ ነው? ዘጋቢ ፊልም ቢጠፋ ዘጋጊ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” ጠፍተው ነው? እነርሱም የሉም እንበል እሺ … ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበሮች ጠፍተው ነው? እነርሱ ባይኖሩ እንኳን ጥቃቅንና አነስተኛ ባለወንበሮች ጠፍተው ነው? እነዚህንም እንደ ከሰረ መደብር የሉም በሉ እሺ… ግን ጥቃቅንና አነስተኛ ሽብሮች ጠፍተው ነው? ቢያንስ ቢያንስ ጅምርና ክምር ፎቅ ጠፋ ልትሉ ነው? ይሄም ይጥፋ እሺ ጅምርና ክምር ባለሥልጣንስ የለም? ይሄ ሁሉ ባይኖር እንኳን የኢቢሲዋ ኢትዮጵያን ፍሎሪዳን መስላ አገኘኋት የሚል ዳያስጶራ አለያም ደንባራ ታጥቶ ነው?

የአንድ ተከራይን ምስል አከራይ ቲቪ በሚያዩበት ሰዓት ጠብቆ ማሳየት ኪራይ ሰብሳቢነት እንጂ ምን ይባላል?

በቲቪ ከመታየቴ በላይ ደግሞ መታየቴን የነገሩኝ የአከራዬ ልጆች መሆናቸውን ምን ይሉታል? ደግሞ አንዴ ነግረውኝ ዝም ቢሉስ? እንደ ወንድሜ ያዕቆብ መዝሙር ጆሮዬ ላይ አዜሙት እኮ፤

እንደምንም ተረጋግቼ ነገሩን ማንም ሳይሰማ ለማለባበስ “በቲቪ ዐያችሁኝ… ጎበዞች፣ አሁን ማነው በሬን የሚከፍትልኝ” ብዬ እንደነገሩ ሸውጄ ላልፍ ስል እየደጋገሙና ንግግራቸውን ዜማዊ እያደረጉ የኔን በቲቪ መታየት ማውራት ቀጠሉ፡፡ ጭራሽ ማነው ቀድሞ ያየው በሚል መጣላት ጀመሩ፡፡ በጣም ስላበሳጩኝ “ስታድጉ እግዜር በኢቢሲ ያሳያቹ” ብዬ ልረግማቸው አልኩና ነፍስ የማያውቁ ሕፃናትን መጪ ጊዜ ለምን አበላሻለሁ ብዬ በርኅራኄ ተውኩት፡፡ ለኔም ለወንድሙም ያልራራው ቱግ ያለው አንደኛው ሕፃን ግን ሌላውን በጥፊ አጮለው፤

“ሚአአአአአአአአአአ” የሚል ድምፅ አስተጋባ፤ ጉልቤውን ጩጬ ደግሞ እኔ አጩዬው ሌላ “ሚአአአአ” በመስማት ደስታዬ ሙሉ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አከራዬ መጥተው “በቲቪ ከመታየትህ ልጆቼን ማጣላትህ” ብለው ሌላ ጭማሪ እንዳያዙብኝ አልቃሹን ቶሎ አባበልኩት፡፡ እዚህች ጋ ግን አንድ ጥያቄ በሕሊናዬ ሽው አለች…. “በኢቢሲ የምንታይ ሰዎች ሰውን ለምንድነው የምናጣላውና የምናጮለው?”

ወዲያው ከአከራዬ መኖሪያ ውስጥ የበር ድምፅ ሰማሁ፤ ለብ ያለ ላብ ህብለሰረሰሬን ይዞ ሲወርድ ተሰማኝ፤ ቅንድቤ እንደከርዳዳ አፍሮ የቆመ መሰለኝ፤ ጉንጬ ወጣ ገባ እያለ ጊዜያዊ ዲምፕል መፍጠሩ ይታወቀኛል፡፡ ወደተከራየኋት ቤቴ ከመግባት ይልቅ አቅጣጫዬን ቀይሬ ወደ በሩ አመራሁ፡፡ በጣም መደንገጤ የታወቀኝ ወደ ውጭ ለመውጣት ከውስጥ ማንኳኳቴን ሳስተውል ነው፡፡

ለነገሩ ጥፋቱ የኢቢሲ ብቻ ሳይሆን የመብራት ኃይልም ነው፡፡ ሳምንቱን ሙሉ የሌለ መብራት እኔ በኢቢሲ ስታይ ጠብቆ መምጣቱ ምን ይባላል?

አውነት ለመናገር ባሳለፍነው ጨለማ ሳምንት ኢቢሲ እንኳን ናፍቆን ነበር፡፡ ውሃ ልማት ሲረሳን ውሃ ፣ መብራት ኃይል ሲረሳን ደግሞ የኢቢሲ ወሬ እንደሚጠማ ያወቅኩት ባለፈው ጨለማ ሳምንት ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው… መብራት ሲመጣ የአከራዬን ጥምና የኔን ወሽመጥ ቆረጠ፡፡ “ቶማስ ኤዲሰን በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ሥራ አጥ አደገኛ ቦዘኔ ይሆን ነበር” ብዬ ኤልፓ ላይ እንዳሾፍኩት ሁሉ ኤልፓም “በዚህ ዘመን በኢቢሲ ስትታይ ተባብሬ ቤት አጥ አደርግሃለሁ” ብሎ ያሽሟጠጠ መሰለኝ፡፡ እግዜር ይይልህ ኤልፓ… ኮረንቲህን በማይሆን ጊዜ ለቀህ ቤቴን ልታስለቅቀኝ ነው፡፡

ብቻ አለቃቀቄ በቤት ብቻ ይብቃ፤ ለኢቢሲ ኢንተርቪው ሰጥቶ እንኳን ቤት ሌላም የለቀቀ ብዙ ነው አሉ፡፡

ከሐሳቤና ወደ ውጪ ከማንኳኳቴ የባነንኩት “ሰላዩ” የሚለውን የአከራዬን ድምፅ ስሰማ ነበር፤

“ምን እያደረክ ነው?” አሉኝ በፈገግታ፡፡ ፈገ…ግ ብለዋል፡፡ ከታዋቂ ሰው ጋር እያወሩ እንዴት ፈገግ አይሉ፤ የሚያስጨምሩትን ገንዘብ እያሰቡ እንዴት ፈገግ አይሉ፡፡

ምላሼ ሲዘገይባቸው “እየወጣህ ነው?” አሉኝ፡፡

“ከርሶ ቤት? ኧረ ምን በወጣኝ? ምን ጎደለኝ ብዬ?” መርበትበቴ ግራ ገባቸው፤

“እየወጣህ ነው ወይስ እየገባህ? ነው ምልህ”

እየወጣሁ ነው እየገባሁ? የኔም ጥያቄ ነው፤ ጥያቄያችን እንዲህ የተመሳሰለው አከራይና ተከራይ ከአንድ ወንዝ የሚቀዱ ሆነው ይሆን? አይ ይሄስ አይሆንም … ከአንድ ወንዝ የሚቀዱ ሳይሆኑ ከአንድ ቧንቧ የሚቀዱ (ላልቶ ይነበብ) ናቸው፡፡

“እየገባሁ ነው እማማ”

“ጎሽ ና በል የምነግርህ ነገር አለ”

በህብለሰረሰሬ የሚወርደው ላብ ከመቀዝቀዜ የተነሣ እርጎ የሆነ መሰለኝ፤ አፍሮ ቅንድቤም ጠፍቶ ቅንድበ በራ ሆነ፤ የጉንጬ ዲምፕል ወደ ቦርጨ ጉንጭነት የተቀየረ ሆነብኝ፡፡ እንደምንም ቀረብኳቸው፡፡

“ይኸውልህ ሰላዩዬ … መቼስ እንደልጄ እንደማይህ አታጣውም” ብለው ጀመሩ፤ አከራዮች የብር ጭማሪ ቀዶ ጥገናን ሲያዙ የሚያስቀድሟት ማደንዘዣ ንግግር ነች፡፡ እንደእናት አደንዝዘው እንደ አከራይ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ ካለዚያማ ሕመሙ በየትኛው የተከራይ ዐቅም ይቻላል?

“እናም ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ እንዲሁ ሳስብህ ነው የዋልኩት…”

ኧረ ምን አይነት ጣጣ ነው… እኔ እንደው አውቄዋለሁ፣ ለምን ወደ ጉዳዩ ገብተው የጭማሪውን መጠን እንደማይነግሩኝ አላውቅም… መጨረሻውን ለማውቀው ድርሰት ሐተታ አበዙበት፡፡

“ደግሞስ በዚህን ጊዜ አንተን ካላሰብኩ ማንን ላስብ…”

አንጀት ተበልቶ ተሙቷል፡፡ እኔ የማይገባኝ በችግር ጊዜ ካላንተ ማን አለኝ የሚል ጠይም ፈሊጥ ነው፡፡

“ስለዚህ እንደ ተከራይ ሳይሆን እንደ ልጄም ላዝህ ነው”

ሆሆ የዛሬውስ ለየት ያለ ነው፤ ከዐቅሜ በላይ ጨምረው ስታዘዛቸው ታየኝ… ኪኪኪ

“ነገ ወደ ኢየሩሳሌም ለአንድ ወር መሔዴ ነው፤ እናም የተከራየሃትን ቤት ትተህ እዚሁ እኔ ቤት እያደርክ ግቢውን እያስተዳደርክ ጠብቀኝ፤ እንደኔ ሆነህ ሁሉን ተቆጣጠር፤ ሠራተኛዋ ምግብህን ታበስላለች፤ የዚህን ወር ኪራይም ተወው አትክፈል፤ ብቻ ቤቴን አደራ፡፡ ነገርኩህ እንደልጄ ስለማይህ ነው፡፡ ያቺ አጭሯ የአክስቴ ልጅ እየመጣች ታይሃለች፤ ያው እዚህ ያለችኝ ዘመዴ እሱዋ ብቻም አይደለች? በል አሁን ግባ ይሄን ልነግርህ ነው የጠራሁህ…”

ዝም ብዬ በፈገግታ አየኋቸው፡፡

“አንተን እኮ ነው… ሰላዩ”

“አ… አቤት”

“እንግዲህ እንዲህ ፈዘህ ቤቴን እንዳታዘርፍ…” አሉኝ በቀልድ መልክ፡፡

ከልቤ ስቄላቸው እንደ መሔድ አልኩና “ግን እማማ ቲቪ አይተው ነው ይሄን የወሰኑት?” አልኳቸው፡፡

“ያመዋል እንዴ ልጁ… ነገ እኮ መንገደኛ ነኝ፤ ስጣደፍ ዋልኩ እያልኩህ፤ በምን ጊዜዬ ነው ቲቪህን የማይልህ… ሆሆሆ”

እየሳቅኩ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ ቅንድቤ በራ ይሁን አፍሮ ፣ ጉንጬ ስርጉድ ይሁን ቦርጭ መልኬ ስለጠፋኝ ምናልባት ቲቪ ላይ ደግመው ካሳዩኝ ብዬ ቲቪዬን ልከፍት ስል መብራት አለመኖሩን ተረዳሁ፡፡

ወዲያው እኔን በማሞገስ ከረሜላ መሸለም የማይሰለቻቸው እኔ ባለሁበት ሁሉ ዕለቱን ቡሔ የሚያደርጉት የአከራዬ ልጆች

“መጥተናል በዕለቱ

ኧረ እንደምን ሰነበቱ” እያሉ ገቡ፡፡ ዛሬስ አብሬአቸው ልጨፍር ተነሣሁ፤ የቅድሙን የቲቪም ወሬ ስለረሱት ደስ አለኝ፤ “ሆ” ብሎ ማጀብ ቀላል አይደል? አንዱ ብልጣብልጥ ያወጣል እኔና ሌሎቹ “ሆ” እንላለን፡፡

“እዚህ ማዶ ……..ሆ

አንድ ነጭ ጨው …….ሆ

እዚያ ማዶ …………ሆ

አንድ ነጭ ጨው ……….ሆ

የኔማ ሰላዩን ……………ሆ

በቲቪ አየነው …………..”

…………..//………….

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top