Free songs
Home / Selayu / Selayu 15: አባት አገር ጀርመን

Selayu 15: አባት አገር ጀርመን

Selayu

ጀርመኖች ሀገራቸውን አንደኛ እናት ሀገር ብለው ሳይሆን አባት ሀገር ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ የእግር ኳስ ቡድኖቻቸው ሁሉ ታጋዮች፤ እጅ የማይሰጡና ውጤትን ብቻ ግብ ያደረጉ ነበሩ፡፡ እናታዊ ብልኃትን ሳይሆን አባታዊ ቆራጥነትን የተላበሱ ነበሩ፤ ናቸው፡፡

በመንፈሳዊ ትምህርት ሴት ለትውዝፍት፤ ለምንዝር ጌጥ ትሸነፋለች ይባላል፡፡ ከፈተናዎች ሁሉ በምን ላጊጥ፤ የቱን ባደርግ ውበቴ ጎልቶ ዐይን መሳብ እችላለሁ በማለት እና በመሳሰሉት ዲያቢሎስ በቀላሉ ይጥላታል፡፡ ሔዋንን ንግሥተ ንግሥት ሆይ እንዳንቺ ውብ የለም ብሎ ሰይጣን ያሳታት ለዚሁ ነው፡፡ እናም ውበት ለእናት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ወንድ ደግሞ ትልቁ ፈተናው ዝሙት ነው፡፡ ስለዚህ አባት ውበትን መመልከት እንጂ ውብ መሆን ብዙ አያሳስበውም፡፡

የአባት ሀገር ጀርመን ተጨዋቾች የእውነትም አባታዊ ናቸው፡፡ እንደ እናት ሀገር ብራዚልና እንደ እናት ሀገር አርጀንቲና ኳስን ይዞ መሽቀርቀር አይሆንላቸውም- አባት ሀገር ናቸዋ፡፡ እንደ ቆንጆ ኮረዳ የወንድን አንገት ሁሉ ማስዞር እና ውበትን ማሳየት ትዝ አይላቸውም- አባት ሀገር ናቸዋ፡፡

እንደ እናት ሀገር እንግሊዝ “እናት” ሆነው እንደ አባት መታገልና ሁሌም መውደቅ ያስቃቸዋል፡፡ ምንድነው መቀላወጥ ወይ እናት ወይ አባት መሆን! እያሉ ይቆጣሉ፡፡

እንደ አፍሪካውያን ሀገራት ተጨዋቾች እናት ሀገርን ወክለው ለ“እንጀራ እናት ሀገር” እንደ መጫወት ያህል መቀለድም ያሳዝናቸዋል፡፡ “ከእናት ሀገር ይልቅ ልጅነታቸው አብዝቶ የሚያሳስባቸው ጨቅሎች” በማለት ያሾፉባቸዋል፡፡ ተጨዋቾቹን ብቻ ሳይሆን የፌዴሬሽን መሪዎቸንም እንዲሁ ይሏቸዋል፡፡ “የእናንተ ሀገር ቆይ የክብሪት ቀፎ ናት አንዴ? እስከመቼ  ነው ከሆዷ ወጥታችሁ ጎኗን የምትረግጡት?” በማለትም ጎረቤታዊ የአባወራ ቁጣውን በምክር መልክ ያክላል- አባት ሀገር ጀርመን፡፡

እናት ሀገር ብራዚል በ1970ዎቹ “ከ3 በላይ ከገባባቹ ሀገራችሁ እንዳትመጡ” የተባሉ ተጨዋቾችን ያቀፈችው እናት ሀገር ዛየር ላይ 3 ብቻ አግብታ፤ የጎሉን መጠን ከፍ ሳታደርግ እናትነቷን አሳየች፡፡ አባት ሀገር ጀርመን ግን በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከ3 በላይ በሆነ ልዩነት ተሸንፋ የማታውቀውን ብራዚልን ያውም በሜዳዋ፤ ያውም በግማሽ ፍጻሜው 7 አከናነበቻት፡፡ አንድ ያጣላል፤ በሞቴ እያለች የአባት ጉርሻን ስቅ እስኪላት አጎረሰቻት፡፡ አባት ተቆጪ ነውና፤ ይፈራልና ብራዚልም ወዳ ሳይሆን በግዷ ከአፏ በላይ የሆነን ጉርሻ በሁለት እጇ አንከብክባ ጎረሰች፡፡ እየበላችም እንደ አዞ አለቀሰች፡፡ እንባው ግን የአዞ አልነበረም የእናት እንባ እንጂ፡፡

አባት እንዲህ ነው፡፡ ሲገርፍ አይጣል ነው፡፡ አባት ሀገር ጀርመን 6 የዓለም ዋንጫ ሀገራትን ገርፋ አባትነቷን አስመሰከረች፡፡

አንድ ኢትዮጵያዊ የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋች በአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅ ሲሰጥ ብራዚልንና ጀርመንን አነጻጽሮ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “አንድን ብራዚላዊ ሆዱን ብትቀደው ከሆዱ ኳስ ታገኛለህ፤ አንድን ጀርመናዊ ሆዱን ብትቀደው ግን የምታገኘው ባሌስትራ ነው”፡፡

ተጨዋቹ ይህን የተናገረው ብራዚልና ጀርመን ያላቸውን የእግር ኳስ ፍልስፍና ለመግለጽ በማሰብ ይመስላል፡፡ ጀርመን በዚህም ይሁን በዚያ ለዓለም ዋንጫ አንዴ ካለፈ ጠልዞም ይሁን ጠዝጥዞ፤ ቀጥቅጦም ይሁን አሯሩጦ ውጤት ያመጣል፡፡ ለዚህም ነው ከተሳተፈባቸው 18 የዓለም ዋንጫዎች በ17ቱ ለሩብ ፍጻሜ መብቃት የቻለው፡፡ ለዚህም ነው የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት አራት የዓለም ዋንጫዎች ለግማሽ ፍጻሜ የበቃው፡፡ ብራዚል ጋ ደግሞ መጠለዝ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ውብ እግር ኳስና አኩሪ ውጤት ለብዙ ጊዜያት ብራዚልን የገለጸ ውጤት ነው፡፡ ሁለቱ አገራት በየራሳቸው አካሄድ የዓለምን እግር ኳስ ተቆጣጥረዋል፡፡ ጀርመን 105 ጊዜ ብራዚል ደግሞ 103 ጊዜ በዓለም ዋንጫው በመጫወትም ከማንም ሀገር ይበልጣሉ፡፡

ከ2006ቱ የጀርመኑ የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ግን ጀርመን ባሌስትራነቷን ከኳስ ጋር ማቀናጀት ጀመረች፡፡ (ብራዚል ደግሞ ውብ እግር ኳስን አንቅራ ተፍታ ባለ ባሌስትራ ሆነች) የወቅቱ አሠልጣኝ ክሊንስማን የአሁኑን አሠልጣኝ ዮአኪም ሎውን ይዞ ጀርመን ጥሩ እግር ኳስን መጫወት እንደሚችል በጋራ አሳዩ፡፡ ሆኖም ጀርመን በሀገሯ ከግማሽ ፍጻሜ ማለፍ አልቻለም፡፡

በ2010 የደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ ጀርመን በዮአኪም ሎው እየተመራ በልጦ እየተጫወተ፤ ብዙ ጎልን እያገባ አሁንም ከግማሽ ፍጻሜው ተመለሰ፡፡ በ2008ትም ሆነ በ2012 የአውሮፓን ዋንጫም ማግኘት አልቻለም፡፡

በዚህን ጊዜ የቀድሞ ባለ ባሌስትራዎች እነ ቤከን ባወር ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ ውብ እግር ኳስ አይጠቅመንም፤ ዮአኪም ሎው ከሀገሩ ውጪ ከርሞ የመጣ ባለሙያ ነውና ለጀርመን አይሆንም፤ በባየር ሙኒክ በሻልከና በመሳሰሉት ታላላቅ የጀርመን ቡድኖች ያላሰለጠነና ያልተጫወተ ለጀርመን ውጤትን አያመጣም ተባለ፡፡ በተለይ ዮአኪም ሎውና ኦዚል ሁለቱም በሀገር ውስጥ ክለቦች ጉልህ ታሪክ የላቸውምና በጣም ተተቹ፡፡ በጀርመን የተከበሩ ባለሙያዎች ቡድኑን ተቹት፡፡ ዮአኪም ሎው ግን የሚሠሩትን ጠንቅቀው ያውቁ ነበርና ወይ ፍንክች አሉ፡፡ ይሄ የራስ መተማመናቸውም በደቡብ አሜሪካ ምድር ዋንጫን ያነሳ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ቡድን አሠልጣኝ አደረጋቸው፡፡ አባት ሀገር ጀርመን ለአራተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን አነሳ፡፡

እናት ሀገር አርጀንቲና የበኩር ልጇን ሜሲን ብትተማመንም አልሆነላትም፡፡ 90 ደቂቃው ሲያበቃ አርጀንቲናውያኑ ጉልበታቸውን እንደጨረሱ ያስታውቁ ነበር፡፡ አባታውያኑ ጀርመኖች ግን ተጨማሪ 90 ደቂቃ መጫወት የሚችሉ ይመስሉ ነበር፡፡ አርጀንቲናውያኑ ጎል ጋር እየደረሱ የሚስቱት በእናታዊ ርኅራኄ ይሁን በሌላ አልታወቀም፡፡

የሆነው ሆኖ አባት ሀገር ጀርመን ዋንጫን በላ፡፡ ለአራተኛ ጊዜ የዓለምን ዋንጫ በላ፡፡ ከጊዜው ጋር ተራምዶ፤ ብዙ ደጋፊን አፍርቶ፤ ባሌስትራውን ሳይሸጥ ኳስን አካብቶ የዓለም ቁንጮ ሆነ፡፡ ከ24 ዓመታት በኋላ ተሳካለት፡፡

ሕይወትም አንዲሁ ነች… ያለውን ይዞ ሌላ የሚያዳብረውን፤ ከሌሎች ጥሩ ጥሩውን የሚቀስመውን፤ ምንም እንኳን ብዙዎች ጠንክሮ ተስፋ ሳይቆርጥ በፅናት የሚታገለውን…. አንድ ቀን ውጤት ትሰጠዋለች- ከ24 ዓመታት በኋላም ቢሆን፡፡

የብብቱን እየጣለ የቆጡን የሚያወርደውን፤ የራሱን እየናቀ የሌሎቹን የሚያመልከውን፤ የተሳካለት ቢመስል እንኳን አወዳደቁን ታከፋዋለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top