Free songs
Home / Selayu / Selayu 12: ዘራፍ

Selayu 12: ዘራፍ

Selayu

Selayu

ሰላዩ አኩርፏል፣ ሰላዩ ተቆጥቷል፣ ሰላዩ አዝኗል፣ ጥቂት ይተክዝና በረጅሙ ይተነፍሳል፡፡ እንደገና መለስ ብሎ ነገር እንምትበላ ወይዘሮ ከተብሰለሰለ በኋላ ዘራፍ ይላል፡፡

“……የወገኑ ደም ጠርቶ ያነቃው

የዜግነት ክብር በል ተነስ ያለው

የት አለ ዘመድ ወገን ወዴት ነው?

የታል ስሜቱ የሃበሻነቱ?

የኢትዮጵያዊነቱ

የታለ ወዙ የጀግንነቱ

የቆራጥነት መራራ ሀሞቱ?

ቁጣው አስደንጋጭ እንደ አራስ ነብር

የደፈረውን የሚሰባብር

ጠላቱን ሚውጥ እንደዱር ዘንዶ

ከየገባበት ፈልጎ አሳዶ

እውነት የሆነ ሀቀኛ ፍርዱ

አድቅቆ የሚጥል በኃያል ክንዱ

አትንኩኝ አትንኩኝ አትንኩኝ ባይ ለጎንታዮቹ

ደርሰው ከነኩት ከጎነተሉት

እንኳን ለመርዶ ለወሬ አያመቹ

እምምምም…..

እትትት……”

•     •     •

….ያኔ ድሮ….እርሶ ወደ አሜሪካ ሳይሰደዱ በፊት

                ወይም ካናዳ ወይም አውሮፓ ሳይሰደዱ በፊት

                አሜሪካ የምትባል ምድር ሳትኖር በፊት

                ድሮ…ኢህአዴግ ከመኖሩም በፊት

                ከፌስቡክም በፊት

                ከኢቲቪም በፊት….

  ኢትዮጵያ የተባለች ታላቅ ምድር አድርአዝ የተባለ ታላቅ ንጉሥ ነበራት፡፡ ሳዑዲ አረቢያ በተባለች ደረቅ ምድር ደግሞ ቁሬይሾች የተባሉ የነቢዩ መሀመድ ደጋፊዎችን የሚያሳድዱ ነበሩ፡፡ እናማ አሳደዷቸው፡፡ አሳደው…አሳደው….አባረው…አባረው አሰቃዩአቸው፡፡ ታላቁ ነቢይም ተከታዮቻቸውን ከቁሬይሾች ለማዳን የመረጧት ኢትዮጵያን ነበር፡፡ ቃል በቃል በሃዲስ እንደተፃፈው  “ሂዱ ወደ ኢትዮጵያ በዚያችም ሀገር ፍትህን የሚያውቅ ንጉሥ አለ፡፡ እሱም ይጠብቃችኋል፡፡ የእውነትና የዕምነት  ሀገር ናት፣ በዚያም አላህ እስኪፈቅድ ድረስ ትቆያላችሁ” ብለዋቸዋል፡፡ በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው የሚባለውን ሄጂራ (ስደት) ያስተናገደችው ኢትዮጵያ ስደተኞቹን አሳልፋ እንድትሰጥ በቁሬይሾች  በርከት ያለ እጅ መንሻና ወርቅ ቀርቦላት ነበር፡፡ ንጉሡ ግን አልተቀበሉትም “በእነዚህ ሰዎች ላይ እንድፈርድ የሚያደርገኝ አንዳች ነገር አላገኘሁባቸውምና አሳልፌ አልሰጣቸውም፡፡ በምድሬ ይቀመጡ፡፡” አሉ እንጂ፡፡

    •     •     •

….ሰላዩ ተቆጥቷል፣ ቁጣው አልበረደም፣ የስለላ ሳይሆን የሽለላ እንጉርጉሮውን ቀጥሏል፡፡

ኧረ ጎራው……ኧረ ጎራው

ጎራው..ጎራው….ጎራው

አንተ ሀበሻ ያልከኝ ያንቆለጳጰስከኝ

በእንግድነት መጥተህ ያላበረርኩህ ነኝ፤

ጎራው…..ጎራው……ጎራው

በደረቅ መሬትህ ብታፈሰው ደሜን

ያንተም ደም አለብኝ ያንድ ደም ደሞች ነን

ጎራው.……ጎራው…..ጎራው

 እምቢ…..እምቢ

ርካሽ ጉልበቴን አንጠፍጥፈኻል

በመሬቴ ላይ የዘራኸውን ሩዝህን ቅመህ ፈንክተኸኛል

ይሄ ሳይበቃህ በንቀት ኃይልህ ደርሰህብኛል

አትንካኝ!

አትንካኝ ብልህ ነካክተኸኛል

ይኸው “እምቢ” በል ተነስ ይለኛል

ኢትዮጵያዊነት ጥቁሩ ወኔ እምቢ ያስብለኛል

እምቢ…..እምቢ……”

•     •     •

  ድሮ ያኔ….የሳውዲ ስደተኛ ዐረቦች በነፃይቱ ምድር ኢትዮጵያ በስደት ሳሉ በነፃነት ሱቅ ከፍተው ይነግዱ ነበር፡፡ ‘ሱቅ’ የሚለው ቃል ራሱ ዐረብኛ ነው፡፡ በዛሬዋ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚገኙት ስደተኞቻችን እንኳን ሱቅ ሊከፍቱ ይቅርና በሕይወት መኖር ብርቅ ሆኖባቸዋል፡፡ የሚደንቀው በኢንቨስትመንት ስም የሳዑዲ ሀብታሞች በለም መሬታችን ሩዝ እያመረቱ  ሀገራቸውን መመገባቸው  እኛን ከመደቆስ አላገዳቸውም፡፡ የተዳቀሉ ናቸው ለማለት ሐበሻ ብለው የሰየሙንም ወይ እነሱ ወይ ወገኖቻችን ከሚሰደዱባቸው የዐረብ ሀገራት መካከል ወደኛ ተሰድደው መጥተው በሀገራቸው ውስጥ ከሚኖሩበት ነፃነት በላይ የኖሩት ዐረቦች እንደሆኑ ይታመናል፡፡

…..ሰላዩ ግሏል፤ ሞቋል፤ ይፋጃል…

“ኢትዮጵያዊነት ዛሬም እሳት ነው

ንኩት ይፋጃል ገሞራ ፍም ነው

ምንም ቢዳፈን አመድ ቢያፍነው

እሳትነቱ ዛሬም ህያው ነው፡፡”

•     •     •

  “ጢርርር….ጢርርርር….ጢርር….” የሰላዩ ስልክ ጠራ፡፡ ከወጣበት ሳይወርድ ከሞቀበት ሳይበርድ “ሄሎ” አለ፡፡

“ጆፌ ነኝ ሰላዩ” በቃሊቲ እስር ቤት ‘ብዙ በማውራቱ’ ታስሮ የነበረ ወዳጁ ነው፡፡

“ተፈታህ እንዴ?” ሰላዩ እንደጋለ ነው፡፡

“በሀገራችን ከታሰሩ መፈታት የለም እኮ… አምልጬ ነው ባክህ”

“አምልጬ?”

“አዎ…አሁን ልሰናበትህ ነው የደወልኩት”

“ወዴት ልትሄድ?” ሰላዩ ይበልጥ ጋለ፡፡

“ወደ ሳውዲ ዐረቢያ ጠፍቼ ልሸበለል ነው”

“ምን… ሰሞኑን እየሆነ ያለውን አትሰማም እንዴ… ኢትዮጵያውያንን እኮ እያንገላቱ ነው…”

“አውቃለሁ” ጆፌ አቋረጠው “አውቃለሁ… እዚህ በነፃ ከምደበደብ እዛ ሄጄ በፌስቡክ እየተነገረልኝ፤ ሰላማዊ ሰልፍ እየተወጣልኝ፤ እየተሸለለልኝ፤ እየተፎከረልኝ ልንገላታ ብዬ ነው፡፡

በል ሰላም ግባ በለኝ” ድምፁ በተስፋ መቁረጥ የተጠቀለለ ተስፋ ያለው ይመስላል፡፡

“ሰላም ግባ” አለ ሰላዩ ቅዝቅዝ ባለ ድምጽ፡፡ ያ ሁሉ ሙቀት የት ገባ፡፡ ሰላዩ በረዶ ሆኗል አሁን፡፡ ቀዝቅዟል፡፡ ቅዝቅዝ… ብርድ….እትትት!

•     •     •

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top