Free songs
Home / Selayu / Selayu 11: ሜክሲኮ አደባባይ ላይ ቆሜ አዲስ አበባን በሰለልኩ ጊዜ አለቀስኩ

Selayu 11: ሜክሲኮ አደባባይ ላይ ቆሜ አዲስ አበባን በሰለልኩ ጊዜ አለቀስኩ

Selayu

Selayu

ሜክሲኮ አደባባይ ላይ ቆሜአለሁ፡፡ በእርግጥ አደባባይ አልኩ እንጂ አደባባዩ ላይ ልሁን አልሁን አላውቅም፡፡ እድሜ ለሚገነባው የባቡር ሀዲድ ይሁንና የሜክሲኮ አደባባይ የሚባል ነገር ለጊዜው በአዲስ አበባ የለም፡፡ የታክሲው ረዳት “መጨረሻ” ሲል የታክሲውን ወንበር ተደግፌ ለጥ ካልኩበት እንደነቃሁ እንጂ ምን ያህል ሰዓት እንደተጉአዝን እንኳን አላስታውስም፡፡ በየመንገዱ እንደ ቤተመንግሥት በር የሚዘጋጋው የአዲስ አበባ መንገድ እንኳን እንቅልፍ ወባም ያስይዛል፡፡ ታክሲዋ ከመገናኛ ሜክሲኮ ለመድረስ ምን ያህል ሰዓት እንደተራመደች የማላውቀው ለዚህ ነው፡፡

በከተማችን በር ብቻ አይደለም የሚዘጋው፡፡ መስኮትም ብቻ አይደለም፡፡ መንገድም ይዘጋል፡፡ ጥርቅም ተደርጎ ይዘጋል፡፡ አፍ ይዘጋል ብለው “አፍህን ዝጋ” አይበሉኝና ከሚከፈተው መንገድ የሚዘጋው እንደሚበልጥ ሰላዩ አረጋግጦአል፡፡ የኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳናም ይሁን የናይጄሪያ መንገድ፤ ካዛንቺስም ይሁን ፒያሳ ጥርቅም ካሉ ከልባቸው ነው፡፡ መዘጋት ብርቅ ነው እንዴ? እንዳይሉኝ ብቻ!

በአዲስ አበባችን የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ሲደረግ የማይዘጋ መንገድ የለም፡፡ በአንድ ወቅት መሪዎቹ መጡ ተብሎ የሚጓጓዙበት መንገድ እስኪያልፉ ድረስ ለሌላ መኪና ሲዘጋ በጊዜው የነበርኩበት የአቃቂ መንገድም ተዘጋ፡፡ የገባሁበት መኪና አልንቀሳቀስ ብሎ ተሳፋሪውን አበሳጨና አንዱ ተሳፋሪ ረዳቱን “አረ ባካችሁ እንሂድ” አለው፡፡ ረዳቱም ተበሳጭቶ “በየት በኩል እንሂድልህ? መንገዱ ተዘግቶ የለ እንዴ?” ከማለቱ ተሳፋሪው ነጠቀውና “ከፈለጋችሁ በአየር ላይም ብረሩና አድርሱን”አለ፡፡ የዚህን ጊዜ ሾፌሩ ዞር አለና “የምንነዳው እኮ ዴር 33ን ሳይሆን ታክሲ ነው” ብሎ ተሳፋሪውን ዝም አሰኘው፡፡ እኔም ረዳቱን “መንገዱ ምን ሆኖ ነው የተዘጋጋው?” አልኩት፡፡

“የአፍሪካ መሪዎች ስለሚያልፉ ነው፡፡”

“የአፍሪካ መሪዎች አቃቂ ይመጣሉ እንዴ?”

“አይመጡም”

“ታዲያ ለምን ይዘጋል?”

“አቃቂ ከቦሌና ከሜክሲኮ በምን አንሶ ነው የማይዘጋጋው?” ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡ አፍን መዝጋት አያስከፍልምና እኔም እንደመንገዱ አፌን ዘጋሁ፡፡ ይኸው ዛሬም ሜክሲኮ ሆኜ በአፍሪካ መሪዎች ምክንያት ቀጣዩን ታክሲ መሳፈር ሳልችል በባዶ መንገድ ላይ ቆሜአለሁ፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት አዲስ አበባ እንዲህ ነው የከረመችው፡፡ ድንገት መንገዱ ጭር ይልና ዳር ዳር ላይ ፖሊሶች ይቆማሉ፡፡ ከዚያም “ዊው ዊው” የምትል ዶቅዶቄን ተከትለው የአህጉራችን መሪዎች በጥቁር መስተዋት ውስጡዋ በተሸፈነ መኪና ያልፋሉ፡፡ ይህን ከለመድን እነሆ ብዙ ጊዜ ሆነን፡፡  ዞር ስል የፈረሰውን የሜክሲኮ አደባባይ ሀውልት ተጎሳቁሎ፤ ውሀ ቋጥሮና ተጋድሞ አየሁት፡፡ ምናለ ከሚጥሉት ሙዚየም ውስጥ ቢያስቀምጡት ብዬ አሰብኩ፡፡ ሰው ሜክሲኮ ብሎ ሠፈሩን ሲያስብ በአእምሮው የሚፈጠረው የሜክሲኮ ሀውልት እንዲህ ተጎሳቁሎ ባልሰልለው እደሰት ነበር፡፡

የስለላዬን ዐይኖች ወደ ጦር ኃይሎች መንገድ ወረወርኩት፡፡ መንገዱ እንደሌሎቹ መንገዶች በፈረደበት ባቡር ምክንያት ተቦርቡሮ ወደ ዋሻነት ተቀይሯል፡፡ ዐይኔን ወደ ስታዲየም መንገድ ወረወርኩ፤ ያው ነው፡፡ ወደ ብሔራዊ ቴአትር የሚወስደው መንገድም ጭር ብሎአል፡፡ የሣር ቤት መሄጃማ ባግዳድን መስሎአል፡፡ ወደ አውቶቡስ ተራ የሚወስደውም እንደዚያው፡፡ መንገድም ያኮርፋል እንዴ? በዜብራ እንኳን የሚሻገር የለም፡፡ ጭርርርር…..፡፡ ቆይ አኚህ የአፍሪካ መሪዎች አንሄድም ብለው  እዚሁ መሸጉ እንዴ?

የቀድሞው ባለ ራዕዩ ጠቅላይ ሚኒስትራችን (ሌጋሲያቸው እንደተከበረ ይቀጥልልንና) ለምን በስማቸው የአዲስ አበባ መንገድ ወይም ጎዳና እንዳልተሰየመ ታውቃላችሁ? እሳቸው ነቄ ስለሆኑ በመንፈስ መጥተው ሌጋሲያቸውን የሚያስቀጥሉትን ሰበሰቡና በስሜ መንገድ ትሰይሙና አጥንቴ ይወጋችሁአል፡፡ በሚሸት ጫማ ብቻ ሳይሆን በጎማና በእንስሳ የሚረገጥን መንገድ በስሜ ሰይማችሁ ሁሉም ዝቅ ብሎ እንዲያየኝ ታደርጉና ! የሌጋሲዬ ጠላቶች የራእዬ ባላንጣዎች መሆናችሁን ለሚወደኝና ለምወደው ሕዝብ እናገራለሁ፡፡ ይህን ብታደርጉ መቃብሬ ላይ እንዳትቀመጡ!” ብለዋቸው ይሆናል ይባላል፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ማን በሁሉ ይረገጣል! ቀላል ነቄ ናቸው እንዴ!? ከመሞታቸው በፊት ሁሉንም መንገዶች ሰየሙና ላሽ አሉ፡፡ አይ መሌ!

በቃ አዲስ አበባ አንዴ በአፍሪካ መሪዎች ሰበብ፤ አንዴ በባቡሩ ሐዲድ ግንባታ ሰበብ፤ አንዴ ቴሌና ኤልፓ ኬብል ለመቅበር በሚል ሰበብ፤ አንዴ በመኪና አደጋ መንገዶቿ በቀን ለ48 ሰዓታት ይዘጋሉ፡፡ የቴሌም ይሁን የኤልፓ ኬብልን የሚቀብሩ ሰዎች በ3 ቡድኖች የተዋቀሩ ናቸው ይባላል፡፡ የመጀመሪያው ለኬብል መቅበሪያ የሚሆን  ቦይ ቆፋሪ፤ ሁለተኛው ኬብል ቀባሪ፤ ሶስተኛው ቡድን ደግሞ ኬብል የተቀበረበትን ቦይ ደፋኝ ናቸው፡፡ ከአንድ ወዳጄ እንደሰማሁት በአንድ ወቅት ሥራቸውን ሲሠሩ ሁለተኛው ቡድን ይዘገያል፡፡ የመጀመሪያው  ቡድን እንደ ሁልጊዜው ከፊት ቀድሞ የኬብል መቅበሪያ/መዘርጊያ ቦይ እየቆፈረ ይሄዳል፡፡ ቆፍሮ እስኪጨርስ መንገዱ ተዘጋ፡፡ ሁለተኛው ኬብሉን በቦይ ውስጥ የሚዘረጋው ቡድን ይቀርና ሶስተኛው ቡድን ቦዩን እየደፈነ መጥቶ መንገዱ ተከፈተ ተባለ፡፡ (ድርጅቱም መቶ ፐርሰንት ሥራዬን አጠናቀቅኩ ብሎ ይሆናል፡፡) ሆኖም የመብራት/የስልክ መስመሩ አለመዘርጋቱ ሲረጋገጥ እንደገና ይቆፈር ይባላል፡፡ መንገዱም በድጋሚ ይዘጋል፡፡ ኢቲቪም ብዙ የተቆፈሩ መንገዶችን እያሳየ ልማታዊው መንግስታችንን ያስተዋውቃል፡፡

አንዳንዴ ትራፊክ ፖሊሶች ሲደብራቸው ወይም ሆድ ሲብሳቸው መንገድ ይዘጋል፡፡ መቼስ የደበረውን ሰው የባንክ አካውንትና መንገድ ክፈት አይባልምና ከቸኮሉ ትራፊክ ፖሊሱን ማዝናናት ግድ ይሎታል፡፡ በሀገራችን መምህራን ደሞዝ ሲያንሳቸው ሥራ ያቆማሉ፡፡ ተቃዋሚዎች ሰልፍ ይወጡና … ይገባሉ፡፡ ሐኪሞችና መሀንዲሶች ከሀገር ይወጡና … አሜሪካ ይገባሉ፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ካነሳቸው ከሥራ ይባረራሉ፡፡ ትራፊኮች ደግሞ ደሞዝ ካነሳቸው መንገድ ይዘጋሉ፡፡ እነሱ ጋ ቀልድ የለም፤ የማሪያም መንገድ እንኳን አይሰጡም፡፡

ብቻ ይሄ ባቡር ደርሶ ከዚህ ሁሉ ገላግሎን! እንደ ክርስቶስ መምጫ ቀን የራቀው በባቡር የምንሳፈርበት ዕለት ደርሶ ብቻ! ግዴለም ጥቂት መታገስ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ልደታ ሄጄ ልሳል አሰብኩ… ግን ደግሞ በምን ታክሲ? ከሜክሲኮ ወደ ልደታ ለመራመድ እስከ ስታዲየም የሚረዝም ሰልፍ መሰለፍ የለመደ ድኩም ሀበሻ እግሬ እንዴት ይንቀሳቀስ!? ብቻ ይሄ ባቡር ደርሶ…

ያደርሳል መንገድ ያመጣል መንገድ አለ ደራሲው፡፡ የመዲናችንን መንገዶች ቢያይ ኖሮ ያቆማል መንገድ  ያፈዛል መንገድ ባለ ነበር፡፡ ለመሰለል የመንገድ መዘጋት የማይከለክለው ሰላዩ ሜክሲኮ አደባባይ ላይ ቆሞ አዲስ አበባን በሰለለ ጊዜ አለቀሰ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top