Free songs
Home / Selayu / Selayu 11: ሆያ ሆዬ እና መሪዎቻችን

Selayu 11: ሆያ ሆዬ እና መሪዎቻችን

Selayu

Selayu

ሆያ ሆዬ እና መሪዎቻችን

ሆያ ሆዬ … ሆ … ሆያ ሆዬ … ሆ

እዚያ ማዶ … ሆ … ጭስ ይጨሳል … ሆ

እዚህ ማዶ …  ሆ … ጭስ ይጨሳል … ሆ

አጋፋሪ ይደግሳል … ሆ …

ያችን ድግስ ውጬ ውጬ … ሆ

በስለላ ተገልብጬ … ሆ

መጣሁላችሁ … ሆ

ዓይኔን አፍጥጬ … ሆ

ጥሩ ሰላይ እንጂ ጥሩ ገጣሚ ባልሆንም ለዛሬ ግን የተዋጣልኝ ይመስለኛል። መቼስ ቡሄን ቢያንስ እንዳሰባችሁት አልጠራጠርም። ሠሞኑን ፈጣሪ ከመኪና ጎማ የጠበቃቸውና፣ ቁመታቸው ከመኪና ጎማ ያነሰ የአዲስ አበባ ልጆች ሰውን ሁሉ በሆያ ሆዬ ባለመኪና እያደረጉ ሲሸቅሉ ከረሙ። ታዲያ ሰላዩም ከልጆቹ ምላስ የሰለልኳቸውን ግጥሞች «እንዲህ ቢሆኑስ?» ልላቸው ነው።

አሁን ከላይ በመግቢያ የተጠቀምነው ግጥም እንዲህ ሰሞነኛ ቢሆኑስ።

ሆያ ሆዬ  …. ሆ …. ሆያ ሆዬ … ሆ

እዚያ ማዶ … ሆ … ዓባይ ይጨሳል … ሆ  (ጢስ ዓባይ ማለቴ ነው) ሆ

እዚህ ማዶ … ሆ … ሰው ይጨሳል  (የግብጽ ሰው ማለቴ ነው) …ሆ

የኢትዮጵያ መንግሥት … ሆ … ይደግሳል … ሆ

ያቺን ድግስ … ሆ … ውጬ ውጬ … ሆ

ደመወዜንም … ሆ … ተመጥጬ …. ሆ

(ከዚህ በኋላ ግጥሙን የሚጨርሱት ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ቢሆኑ)

ሣንጃዬን ይዤ … ሆ … ተቅበጥብጬ … ሆ

ከዙፋኔ ላይ … ሆ … ተገልብጬ … ሆ

ያቺ ዙፋን … ሆ … አመለኛ … ሆ

ኢሕአዴግን  … ሆ … አታስተኛ … ሆ

… መቼስ ኮሎኔሉ ዱላ ይዘው መሬት እየደበደቡ (የሚያዙት ዱላ ላይሆን ይችላል) ሟቹ አቶ መለሰ ፊት ሆያ ሆዬ አይጨፍሩም። ግን ቢጨፍሩ ምን ይሉ ነበር።

እንደሚመስለኝ ከሆነ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የቀድሞ ባለስልጣናትን ይዘው፣ እሳቸው «ሆያ ሆዬ» ብለው ግጥም እያወጡ፣ ከፊት ፊት የቀድሞ ባለሥልጣኖች «ሆ ባዮች» ሆ እያሉ፣ ከኋላ ደግሞ ሟቹ አቶ መለሰ ዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው «ነፍሳቸውን …..ና» ብቻ ተጀመረ እንበል።

ጓድ መንግሥቱ ቀጠሉ።

ሆያ ሆዬ … ሆ … ሆያ ሆዬ … ሆ

ቡሄ መጣ … ሆ … ያ መላጣ… ሆ  (መለስ መጣ ሊሆን ይችላል)

እኔን ጎትቶ … ሆ … ዙፋን ላይ ወጣ … ሆ

እኔ እንደሰማሁት እንግዲህ ሆያ ሆዬ ጨፋሪ ልጆች ጨፍረው ጨፍረው መስተጨረሻ ላይ የሚጨፈርለት ሰው ሽልማት ለመስጠት ሲዘገይ

ኧረ በቃ በቃ … ሆ … ጉሮሮአችን ነቃ … ሆ

ወይም ኧረ መሸ መሸ … ሆ … ጅብ አንኮሻኮሸ … ሆ

ወይም ድምጽህን ሰማና … ሆ … ተው ስጠን ምዘዝና … ሆ

ይላሉ።

ኮሎኔሉም የሚሸልሙት ሲዘገይ የሚከተለውን የሚሉ ይመስለኛል።

ኧረ በቃ በቃ ሰፊው ሕዝብ ነቃ

ኧረ መሸ መሸ ልቤ ተረበሸ

ወይም ድምጽህን ሰማና ተው ስጠን ምዘዝና

ከዚያም ሟቹ መለሰ ዜናዊ ወይ የከርቸሌ መግቢያ ቁልፍ ወይም የዚምባቡዌ መግቢያ ቪዛ መዘው ይሰጣሉ። በዓሉም በዚህ ይፈጸማል።

እስኪ ነገሩን እንገልብጠው … ኮሎኔሉ በዙፋናቸው ላይ ሆነው፣ ሟቹ ተጋዳይ መለሰ እየጨፈሩላቸውና ያው የእርሳቸውም ሆ ባዮች ሆ እያሉ በተገላቢጦሽ እንሳለው። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ድምፃቸውን ጠራርገው፣ መነፅራቸውን አስተካክለው ቀጠሉ። ሆ ባዮቹ እነ በረከት፣ እነ አዲሱ፣ እነ አባ ዱላ ገመዳን፣ ፕሬዚዳንቱንም ጨምሮ ሆ እያሉ ነው። (ፕሬዚዳንታችን ወትሮውንም ለመደገፊያ አንድ ዱላ ስለሚይዙ ለመጨፈሪያ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ዱላ ይዘዋል)

በሟቹ ጠ/ሚኒስትር አውጪነት ተጀመረ።

ሆያ ሆዬ … ሆ … ሆያ ሆዬ … ሆ

እዚህ ማዶ … ሆ … አንድ ካኪ … ሆ

እዚያ ማዶ … ሆ … አንድ ካኪ … ሆ

የኔማ መንጌ … ሆ … በሳንጃ ወጊ … ሆ

እነ በረከት እና ሌሎች ግጥም እየፃፉ ለተጋዳይ መለስ እያቀበሏቸው ነው።

ሆያ ሆዬ … ሆ … ሆያዬ … ሆ

እዚያ ማዶ … ሆ … አንድ ተጫዋች … ሆ

እዚህ ማዶ … ሆ … አንድ ተጫዋች … ሆ

የኔማ መንጌ … ሆ … ቀይ ሽብር መስራች … ሆ

ከዚህ በኋላ ተጋዳይ መለስ መጨፈሩን፣ እነ ፕሬዚዳንት ግርማ ማስጨፈሩ ሰለቻቸውና ሽልማቱ ቶሎ እንዲሰጣቸው የሚከተለውን አከሉ። በመጀመሪያ ሟቹ መለሰ ማውጣቱን ቀጠሉ።

ኧረ መንጌ ንቃ … አራት ነጥብ በቃ!

እዚህ ጋ ድንገት ፕሬዚዳንቱ ጣልቃ ገቡና …

ኧረ በቃኝ በቃኝ … ብዙ እንግዳ አለብኝ! አሉ።

ሟቹ መለሰም ፕሬዚዳንቱን ገላምጠው ሆያ ሆያቸውን ቀጠሉ።

ጭፈራችን ይገታ… ሃያ አንደኛው ዓመት መጣ!

ድምፅህን ሰማና … በል ስጠን ምዘዝና!

እዚህ ጋ ሟቹ መለሰ ዜናዊ ከባድ ስህተት ሰሩ።

በሉ ኮሎኔሉ ወይ ሣንጃቸውን አሊያም ሽጉጣቸውን ከመምዘዛቸው በፊት ልሰናበት።

የከርሞ ሰው ይበለንና እመለስበታለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top