Free songs
Home / Selayu / Selayu 10: የኢቲቪ ጋዜጠኛ የጻፈው የፍቅር ደብዳቤ

Selayu 10: የኢቲቪ ጋዜጠኛ የጻፈው የፍቅር ደብዳቤ

Selayu

Selayu

የኢቲቪ ጋዜጠኛ የጻፈው የፍቅር ደብዳቤ
(ክፍል አንድ)

“ውዴ!

እንዴት ከርመሽልኛል? መቼስ በዜና ሰዓት በኢቲቪ ቀርቤ እንደምን አመሻችሁ (የእለቱን ዜና ይዘን ቀርበናል፤ ከዜናዎቹ ጋር…) ስል ከመቀመጫሽ ተነስተሸ ደህና ነኝ የኔ ፍቅር አንተ እንዴት ነህ? ብለሽ ስትመልሽልኝ በፍቅር ሞገድ ስቱዲዮ ድረስ ይሰማኛል፡፡ ትዝ ይልሻል … ከኔ በፊት የነበረው አምባገነኑ የፍቅር ጓደኛሽ… እጅሽን በዛ ብረት መዳፉ ጨምድዶ ይዞ አባትና እናትሽን እየሰደበ ሲያሸማቅቅሽ፤ ኩምቢ የሚያክል ክንዱን ትከሻሽ ላይ ጭኖ ካለ ዕድሜሽ ሲያጎብጥሽ፤ ሴንጢውንና ክላሽንኮቩን በፊትሽ እያሳየና እየወለወለ ሲያሳቅቅሽ፤ በግቢሽ በረንዳ ላይ ተንከባክበሽ ያሳደግሽውን ጽጌረዳ በእምቡጥነቱ ፍሬ ሳያፈራ ቀጥፎ ሲያስለቅስሽ….ትዝ ይልሻል አይደል? ያኔ ነበር ብሶት የወለደው ልቤ አደፋፍሮኝ አድፍጬ የእናትሽ ጓሮ ዛፎች ሥር የተደበቅኩት፡፡ ማንም የሌለ መስሎት ያ ቀፋፊ እንደለመደው ገና ብቅ ሲል አፈር ድሜ አስጋጥኩት፡፡ ከዛማ የልብሽን የፍቅር ስቱዲዮ ከ198… በኋላ በቁጥጥሬ ሥር አዋልኩት፡፡ ያ ሕዝብ ሁሉ ያደነቀው ታይቶ የማይታወቅ ፍቅራችን ያኔ ነበር የተጀመረው፡፡ ዓለም ፍቅር አጥታ ዜናው ሁሉ ብጥብጥና ጥላቻ በሆነበት በዚህ ሰዓት የኔና ያንቺ ፍቅር በአሰገራሚ ሁኔታ ለተከታታይ ዘጠኝ አመታት 11 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ባለ ሁለት አሀዝ የፍቅር ዕድገትን ከሚያስመዘግቡት አራት ጥንዶች አንዱ መሆናችንን የዓለም የፍቅር ባንክ አረጋግጧል፡፡

“ውዴ!

ከዛ የጅብ ጥላ ተገላግለሽ ከኔ ጋር የተገናኘንባት የፍቅራችንን ህዳሴ በዓል ለማክበር 11 ቀናት ብቻ ቀርተውናል፡፡ የዛን ጊዜማ ብዙ ነገር ነው የማደርግልሽ፡፡ በመጀመሪያ የት እንደምወስድሽ ታውቂያለሽ? ቃሊቲ፡፡ ቃሊቲ ምን አለ እንዳትይኝ ደግሞ…! ልብሽ እንደ አንዳንድ አሸባሪዎች አንገት ከሚንጠለጠል ቃሊቲ ምን እንዳለ ልንገርሽ፤ ቃሊቲ ከርቸሌ አለ፡፡ በዚህ እሥር ቤት ውስጥ አንዳንድ አሸባሪዎች በጋዜጣ ላይ ተሳድበውና በፍቅራችን ላይ ተዘባብተው ተከርችሞባቸዋል፡፡ ታዲያ እነሱን እየጎበኘን ልማታዊ የፍቅር ወጎችን እያወጋን የፍቅራችንን ሕዳሴ ከማክበር በላይ ምን የሚያረካ ነገር አለ? ከዚያ ቀጥሎ የያዝኩት መርሐግብር የሞዴል አርሶ አደሮችን እርሻ እንድንጎበኝ ነው፡፡ በሞዴል ገበሬዎች እርሻ ውስጥ እየተንሸራሸሩ ልማታዊ አየርን እየተነፈሱ እርጥብ ፍቅርን ከመወያየት በላይ ምን ደስታ አለ?

በሦስተኛ ደረጃ ጊዜ ካለን በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ባለሀብት ወደሆኑ ወጣቶች ጎራ ብለን ፍቅራችንን ለማሳደግ እንዴት መሥራት እንዳለብን ልምድ እንወስዳለን፡፡ በመጨረሻም ጎተራ አካባቢ ወደሚገኘው የብሔር ብሔረሰብ አደባባይ እወስድሽና በፍቅራችን ዙሪያ ግልፅ ግምገማ እናደርጋለን፡፡ ከመሰነባበታችን በፊትም በሚያስደንቅ የፍቅር ድባብ … ከሥርሽ በርከክ ብዬ … እጅሽን እየሳምኩ… ዐይንሽ እየተስለመለመ ቁልቁል በፍቅር ሲያየኝ … ድንገት ሳታስቢው… የሕዳሴውን ግድብ ቦንድ በመስጠት ሰርፕራይዝ አደርግሻለሁ፡፡ መቼስ ቀኑ ደርሶ እንዲህ ዓይነቱን ውብ የፍቅር ጊዜ ለማሳለፍ እንደጓጓሽ አልጠራጠርም፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደገለፁት ከሆነ በኔና ባንቺ ፍቅር የማይቀና የለም፡፡ የፍቅራችንን ሕዳሴ ስናከብር ደግሞ እንዴት እንደሚሆኑ አስቢው፡፡

“ውዴ!

እኔ ባንቺ ፍቅር ከተያዝኩኝ ጀምሮ በቀን አንዴ ደጋግሜ ወደ ቤትሽ እንደምመጣ ሁሉም ያውቃል፡፡ አሁንማ የሠፈራችሁ ልማታዊ ወጣቶች በብርቱ የልማት ሠራዊትነት መንፈስ ኮብል ስቶን ስላነጠፉ መንገዱ አያስቸግርም፡፡ ደግሞም የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ ሲያልቅ በቀን 11 ጊዜ እንገናኛለን፡፡ አንቺማ በየቀኑ በኢቲቪ ስለምታዪኝ ናፍቆትሽን በዛ ትወጪያለሽ፡፡ ደግሞ አንቺን ሰርፕራይዝ ለማድረግ ትላንትና ዜና ሳነብ ፎቶሽን በኋላ ኪሴ ውስጥ ይዤው ነበር፡፡ ረስቼው እንዳይመስልሽ – ላንቺ ካለኝ ፍቅር የተነሳ ነው፡፡ የትኛው ፎቶሽ እንደሆነ እስኪ ገምቺ…..፤ ሱዳናዊቷ ጎረቤትሽ ከደቡብ ሱዳናዊ ባሏ ጋር ተጣልታ ካስታረቅናቸው በኋላ አራታችንም በአንድነት የተነሳነው ነው፡፡ ግብፃዊው ፎቶ አንሺ ጥሩ አርጎ ነበር ያነሳን፡፡ እንደውም ትዝ ካለሽ ይሄ ግብፃዊ ፎቶውን ካነሳን በኋላ ገንዘብ አልፈልግም ውሀ አጠጡኝና ልሂድ ነበር ያለን፡፡

“ውዴ!

እንዴት እንደናፈቅሽኝ ታውቂያለሽ? ታላቁ መሪያችን በነደፉት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የመጨረሻ የትግበራ ዘመን ኢትዮጵያን ለማየት የጓጓሁትን ያህል ነው የናፈቅሽኝ፡፡ ብቻ አንቺን ለማግኘት ጓጉቻለሁ፡፡ በጣም ነው የምወድሽ፡፡ በሚቀጥለው ደብዳቤ እስካገኝሽ ድረስ ለፍቅራችን ማጣፈጫ አባይ አባይ ብለው አንዳንድ የሀገራችን ዘፋኞች በጋራ የዘገቡትን ዘፈን ጋብዤሻለሁ፡፡

ያንቺው ልማታዊ ፍቅረኛ!!!”

ይቀጥላል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top