Free songs
Home / Mark's Corner / Mark’s Corner 7: ታክስ ከፋይ እና ታክስ ተቀባይ

Mark’s Corner 7: ታክስ ከፋይ እና ታክስ ተቀባይ

Mekuria-M-Negia

Mekuria M. Negia

ታክስ ከፋይ እና ታክስ ተቀባይ

መስጠት እና መቀበል የራሱ የሆነ ጥቅም እና ጉዳት ቢኖረውም፣ ለመንግሥት የምንከፍለውን ታክስ(ቀረጥ) የመሳሰለውን ስንከፍል ግን፣ ጠላት አስገድዶ የሚነጥቀን ሳይመስለን የምንቀር ቁጥራችን ቀላል አይደለም ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም።

በእኔ አመለካከት ነገ ተጠያቂነት ሳያመጣብን ወጪ እና ገቢያችንን በመረጃ አስደግፈን በሥርአቱ መለየት ከቻልን ካለአግባብ የሚወሰድብንም ሆነ ያለአግባብ ወስደን ነገ ተጠያቂነት ውስጥ ከሚከተን ደካማ የታክስ አሰራር ለመዳን ከመቻላችንም በላይ የ«ቄሳርን ለቄሳር…የእኛን ለእኛ» በአግባቡ በመውሰድ ስጋት ውስጥ የማይከተንን እፎይታ ማግኘት እንችላለን።

ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወር  ጃንዋሪ ጀምሮ ሀገር ውስጥ ገቢ /IRS/ እያጣራ ያለውን ብናይ፣ የ2009 ዓመት ኦዲት ለጠያቃችሁት ወጪ በትክክል መውጣቱን መረጃ አቅርቡ በማለት ለብዙ ታክስ ከፋዮችን የተጠያቂነት ደብዳቤ ልኳል። አጠያየቁም እንደተለመደው አልፎ አልፎ ሳይሆን በጅምላ መሆኑ ከራሱ IRS ድረ-ገጽ ላይ አንብቦ መረዳት ይቻላል። የ2009 ዓመት ታክስ ፋይል ካደረጉ ታክስ ከፋዮች ውስጥ ባለፈው ሰባት ወራት ብቻ እስካሁን 205 ሚሊዮን ታክስ ፋይል ያደረጉ እና ኦዲት ከተደረጉት በአብዝናው መረጃ የተጠየቁ ሲሆን፣ ይኽ ካለፈው ለምሳሌ ከ2001 ዓ.ም. ኦዲት ጋር ሲነፃፀር 670% ያደገ መሆኑን ያሳያል። ለዚህ ምክንያቱ ያው የኢኮኖሚ ሁኔታ እና በየስርቻው ካለእውቀት ታክስ እንሰራለን፣ ብዙ ገንዘብ እናስመልስላችኋለን እያሉ ታክስ ከፋዩ በማያውቀው ወይም በሥራው ጋር የማይገናኝና ቢጠየቅ መልስ መስጠት የማይችልበትን የወጪ ዓይነት አስገብቶ ተመላሽን በዛ በማድረግና ጥያቄ ሲመጣና ታክስ ከፋዩ የሰራለት ሰው ፈልጎ አለማግኘቱ ቀላል መፍትሄ ወይም መመካከር ያልቻሉና ባለማወቅ ነው የሚሉ በሃገር ውስጥ ገቢ IRS ተቀባይነት የማያገኝ ምክንያት የያዙ ብዙ ታክስ ከፋዮች በሃምሳው የአሜሪካ ስቴቶች ዳር እስከ ዳር የሚታይ ችግር ሆኖ ተገኝቷል።

በነገራችን ላይ በእኛ ቢሮ ታክስ ለተሰራላችሁ ከፋዮች ውስጥም ይኽ ማዕበል ያገኛቸው ግለሰቦች ነበሩ። ለዚያውም በጣም ጥቂት። እንዲያም ሆኖ ይኽን ችግር በአንድ የደብዳቤ ማስረጃ አያይዞ በመላክ ችግራቸውን ያቃለልንላቸውና የተጠያቂነት ፋይሉንም ያዘጋንላቸው ሲኖሩ፣ እስካሁን ውሳኔ ያላገኙትን ደግሞ የቅርብ ክትትል በማድረግ ላይ እንገኛለን። የአንድ ታክስ አዘጋጅ ሙያው ታክስ መሥራቱ ብቻ ሳይሆን የሚመጣውንም ችግር ተከታትሎ መፍትሄ ማሰጠት ነውና።

በIRS በመጠየቃቸው የተደሰቱም አልጠፉም። ምክንያቱም ያላቸውን የወጪ ደረሰኞች ሰብስበው ሳያመጡ የተረሳ ግን በሕጉ በወጪነት አቀናንሶ ተጨማሪ ተመላሽን የሚያስገኝ አግኝተው ከኦዲት ነፃ መሆን ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ተመላሽ ያገኙ ደንበኞቻችንን ስናስተናግድ እርካታው ለእነሱ ብቻ ሳይሆን እኛም የሥራችን ጥራት ደንበኞቻችንን በማስደሰቱ እርካታ  አግኝተንበታል።

ከዚህም የምንረዳው እና በሀገር ውስጥ ገቢ IRS እንደተደነገገው፣ እና ታክስ ፋይላችንን ለሦስት ዓመት መለወጥና ማስተካከል ስንችል IRS ደግሞ የአምስት ዓመት ጊዜ አለው ተመልሶ መጥቶ ወጪዎችህ ወይም ገቢዎችህ የተሟሉ አይደሉም፣ መረጃ እፈልጋለሁ ብሎ የመጠየቅ መብት አለው። እናም ጥያቄው ከመምጣቱ በፊት እና ጊዜ ገደቡ ሳያልፍ መልስ መስጠት ይጠበቅብናል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የተፈፀመ አንድ ገጠመኝ ላቅርብ፦ በጣም የማከብረው እና የምወደው የረጅም ጊዜ ደንበኛዬ፣ ባለፈው ዓመት በበጋው ዓርብ ማታ አመሻሽቶ ወደ ቤቱ ሲገባ ያው ልምድ ያደረገውን ፖስታ ሳጥኑን ከፍቶ ፖስታዎችን እንደታሸጉ፣ ከየት እና ከማን እንደተላኩ በማየት ላይ እንዳለ የማይወደውንና የማይፈልገውን የIRS ፖስታ ያገኝና በችኮላ ከፍቶ ያያዋል።  «የ2008 ዓ.ም. የ$13 ሽህ 755.00 የታክስ ዕዳ እንዳለብህ አረጋግጠናልና ባንክ ሪፖርት ባደረገልን ገቢህ መሠረት»…የሚለውን እንዳየ መደንገጥ ብቻ ሳይሆን በእለቱ በሥራ የደከመው ሰውነቱና የዛለው አካሉ ድካሙ ለቆት በድንጋጤ ሊወድቅ ምንም እንዳልቀረው ጊዜ ሳያጠፋ በእኩለ ለሌት ስልክ ደውሎ አጫወተኝ።

በአጋጣሚው የእጄ ስልክ አጠገቤ ነበርና አጠር ያለ የስልክ ውይይት አደረግሁ። እኔም የተቋማችንን የሥራ ጥራት ስለምተማመንበት፣ በእርግጠኛነት «ስህተት ሊሆን ስለሚችል የተላከልህን ደብዳቤ ይዘህ ጠዋት ብቅ በልና እንነጋገራለን» በማለት ካረጋጋሁት በኋላ የስልክ ውይይታችንን አብቅተን በማግስቱ ልንገናኝ ወሰንን።

በዚህ ጉዳይ በእጅጉ ሃሳብ ላይ መውደቁን እና መተኛት አለመቻሉን ያወቅሁት በማግስቱ ጠዋት ከሥራው ቀርቶ ቢሯችንን ከመክፈታችን በፊት ከደጃፉ ላይ ቆሞ ሲጠብቅ በማየቴ ነው።

ይኽ ደንበኛዬ ይኽንን የIRS አስደንጋጭ ደብዳቤ ሊያገኝ የቻለው በታክስ ዝግጅቱ ወቅት በማስረጃነት ያያዘው ስታክ የሸጠበትን ብቻ በመሆኑ ነበር። በደንበኛዬ ግንዛቤ ከዚያ ሂሳብ ገንዘብ ስላላወጣሁ ሪፖርት ማድረግ አይጠበቅብኝም ከሚልና ጥቅሙን ካለማወቅ የመነጨ ነበር። በዚህ የስታክ ሽያጭ ላይ ግን የሸጠበትን በማሳወቅ፣ ከዚያ ላይ ያገኘውን ትርፍ ወይም የገጠመውን ኪሳራ ካለ በየዓመቱ ሪፖርት ማድረግ እና ሠነዱን ማያያዝ ተገቢ ከመሆኑም ባሻገር ኪሳራ ቢኖር በተመላሽኘት የሚያገኘውን ጥቅም ማስቀረቱን ባለመገንዘቡ ነው።

ይኽን እንደምሳሌ የጠቀስኩትን የዚህን ደንበኛዬን $13 ሺህ 755.00 ተጠያቂነት በአግባቡ በማስተካከል እና ለIRS በመላክ በእዳ ከመጠየቅ ይልቅ የ$3,225.00 በተመላሸነት እንዲያገኝ አድርገናል። በዚያ ዓመት ስቶክ ልውውጥ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ስለነበረ ይኽንንም በማስረጃ ደግፎ በማቅረብ ነው።

ስለዚህ ውድ ወገኖቼ በIRS ያልተሰላ እና መረጃ ያልቀረረበት ጉዳይ ተጠያቂነት በሚያስከትልበት ወቅት ባለመደናገጥ ወደ ቤሯችን ብቅ ብላችሁ አነጋግሩን። መፍትሄውን እናፈላልጋለን።

– Mekuria M. Negia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top