Free songs
Home / Mark's Corner / Mark’s Corner 5: ኪሣችንን ሳይጎዳ አበዳሪዎቻችንን እንዴት እናስተናግድ?

Mark’s Corner 5: ኪሣችንን ሳይጎዳ አበዳሪዎቻችንን እንዴት እናስተናግድ?

Mekuria-M-Negia

Mekuria M. Negia

ኪሣችንን ሳይጎዳ አበዳሪዎቻችንን እንዴት እናስተናግድ?

በምንኖርበት የአሜሪካ ምድር ላይ ከልምድ አልፎ ወደ ባሕልነት የተቀየረው የዘመኑ የመገበያያ መንገድ በቀላሉ ተመዞ በሚጫር ካርድ መጠቀምን ያስለመደ እና ያስገድደ ሆኖ እናገኘዋለን። የኑሮውም ውጣ ውረድ የኛን ኃላፊነት መመጠን ባለመቻሉ ይመስላል ብዙውም የአሜሪካን ነዋሪ በዕዳ የተዘፈቀ እና ከአንዱ ዕዳ ወደ ሌላው ዕዳ የሚዘል ሆኖ እናገኘዋለን።

ሁላችንም እንደምናውቀው የብድር አገልግሎት ባይኖር ኖሮ አብዘኛው ሰው በተስፋ እና በሞራል ዛሬን አድሮ የነገውን ለመቀበል ይቸገር ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም።

ለመነሻ እንዲሆን የራሴን የግል ተሞክሮ እንደምሳሌ ማቅረቡን ፈለኩ።

ለመጀመሪያ ጊዜ እኔና ባለቤቴ የመኖሪያ ቤት ለመግዛት አሜሪካን በገባን በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያውን የባንክ ብድር ስንፈርም የገጠመንን አስታውሳለሁ። በአሜሪካ ምድር በነበረን የአጭር ጊዜ ቆይታ ቀደምት የብድር ታሪክ ስላልነበረን እንደ አሁኑ ጠንከር ያለ ብድር ለማግኘት የሚያስችል መመዘኛ አልገጠመንም ነበር። በወቅቱ የብድር ታሪክ ብዙ የማያስቸግርበትና የማይታይበት በመሆኑ አበዳሪዎች በወቅቱ የነበራቸው መለኪያ ከወንጀል ነፃ መሆን እና ቋሚ ገቢ መኖሩን ብቻ ከማረጋገጥ ያለፈ ባለመሆኑ ብድሩን በማግኘት የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የበቃነው ቀልጠፍ እና አጭር በሆነ ጊዜ ነበር። አሁን ግን በአገሪቱ ኢኮኖሚና የቤት ዋጋ መውደቅን አስከትሎ ብዙ መመዘኛ አውጥተዋል።

ስለዚህ ብድር መበደር እናም በግዜ መክፈል ለወደፊት ለሚፈልጉት የኑሮ ማሻሻል እና ብድር ለማግኘት በእጅጉ ጠቃሚ ስለሆነ የሚጠበቅብዎትን በቅድሚያ ለማዘጋጀት የሚከተሉትን ማወቁ ተገቢ ይሆናል።

አበዳሪዎችምንይጠይቃሉ?

  • ቋሚ አድራሻ አለህ? በአለህበት አድራሻ ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ ኖረሃል?
  • በምትሰራው ሥራ ለሁለት ዓመት ያህል ቆይተሃል?
  • ተበድረህ ታውቃለህ? በወቅቱም ትመልሳለህ?
  • አሁን መበደር ለምትፈልገው ብድር ወርሃዊ ክፍያ ለመክፈል የሚያስችል አቅም ወይም ገቢ አለህ?
  • በወንጀል ተከሰህ ታውቃለህ? አሁንስ በክስ ላይ ነህ?
  • የሃገር ውስጥ ገቢ (IRS} ታሪክ ያልተከፈለ ዕዳ አለብህ? የሆስፒታል /የሕክምና/ ያልተከፈለ ዕዳ አለብህ?

ከብድርጠያቂውየሚጠበቅቀድመ-ዝግጅት

  • ከላይ የተጠቀሱትን አበዳሪ ሊጠይቃቸው የሚችለውን ሁሉ በጥንቃቄ ተራ በተራ ማስተካከል ለመልሱም መዘጋጀት።
  • የብድር ሪፖርቱን ለማውጣት ትንሽ ጊዜ ያስፈልጋቸዋልና ዛሬ ያለብንን ከፍለን ነገ ብድር እንደማንጠይቅ መረዳት።
  • አበዳሪው የብድር ታሪካችንን ፈልጎ ሲያገኝ ያልተከፈለ ነው ብሎ ጥያቄያችንን ውድቅ እንደሚያደርገው ከወዲሁ መረዳት።
  • በተለይ የብድር ካርድ «Credit Card) የተፈቀደልንን ከግማሽ በላይ ተጠቅመን ከሆነ ቶሎ መቀነስ ያስፈልጋል። ታዲያ ብዙ ካርድ ካለን ሁሉንም የመጨረሻውን ሪፖርት ተራ በተራ ብዙ አራጣ (Interest) ያለውን በቅድሚያ ብዙ በመክፈል ወደ ዜሮ እንዲመጣ ማድረግ ብልህነት ነው።

መቼም ወጪ ሳናወጣ አንኖርም። ዕድሉ ኖሮ የብድር ካርድ ካገኘን በአግባቡ ተጠቅመን ቀድሞ በጥሬ ገንዘብ እንገዛ የነበረውን በቼክ ላበዳሪው በየወሩ መክፈል ማለት ነው። ይኽም ሆኖ ያለንን ካርድ ሁሉንም በማንቀሳቀስ በወሩ መጨረሻ ምንም ተጨማሪ ሳይኖርብን ከከፈልን በአበዳሪዎች ገንዘብ ተጠቅመን በወሩ መጨረሻ ከመለስን ታማኝነታችንን ማስመዝገብ ማለት እና ለወደፊቱም ለምንጠይቀው ማንኛውም ዓይነት ብድር  ለማግኘት በር ከፈትን ማለት ነው።  እኔ የሰው ገንዘብ አልፈልግም ብሎ (Credit Card) የብድር ካርድ ሳይጠይቁ መቅረት ደግሞ የዋኅነት እና ለሚቀጥለው የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ራስን ያለማዘጋጀት ይሆናል።

ለምሳሌ በግል የምንሰራ ሰዎች ታክሲ፣ ሊሞዚን….የመሳሰሉትን የምንሰራ ከሆነ የወጪያችንን ደረሰኝ መሰብሰብ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ለምናዘጋጀው ለታክስ መረጃ ለማቅረብ ከመቸገር ያድነናል። በዚህና በተመሳስለ የግል ሥራ ላይ የተሰማራን ሁሉ ለዕለታዊ የሥራ እንቅስቃሴያችን አንድ ካርድ ለዚህ ሥራ መድበን ጋዝም ስንቀዳ ፣ ጥገና ስናደርግ ከሥራው ጋር የተገኛኘ ማንኛውንም ወጪ ስናወጣ ለይተን ከአንድ ካርድ ብንጠቀም በወሩ የዱቤ ካርድ ላይ በምናገኘው ሪፖርት ሁሉንም ወጪያችንን ልናገኝ እንችላለን። እንደመረጃም ልንጠቀምበት  ስለምንችል አንድ የዱቤ ካርድ መመደቡ ብልህነት ነው።

መቼም በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ አበዳሪዎች ጋር የተዋዋለ ሰው ጥሩ ትምህርት አግኝቶ ያለፈ ይመስለኛል፤ ይኽ ምክር የሚያገለግለው ግን በቅርቡ ወደዚህ ባሕል የተቀላቀሉና ቆይተውም ቢሆን ሁሌ ከየት መጀመር እንዳለባቸው ከራሳቸው ጋር የሚነጋገሩትን ነው።

አንዳንድ ጊዜ ደካማ ወይም የተበላሸ የብድር ታሪክ ይዘንም ቢሆን ብድር ልናገኝ የምንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆናል።  ነገር ግን በምላሹ የምንከፍለው የወር ክፍያ መጠን በጣም የተለየ ይሆናል።። ጥሩ የብድር ታሪክ ያለው ከ3% እስከ 5% ሲከፍል መጥፎ የብድር ታሪክ ደግሞ 30% ወይም ከዚያ በላይ የሆነ አራጣ እንዲከፍል ሊጠየቅ ይችላል። ይኽን ሰፊ ልዩነት ልብ ይበሉ!

ተበድረው የማያልቅ ዕዳ ውስጥ ገብተው ያሉ ከመሰልዎት ለሁሉም ዘዴ አለውና ስጋት አይግባዎ! በመጀመሪያ ቅደም ተከተል አስይዘው ተራ በተራ ቢከፈል ብለው ያስቡ፣ ካልሆነ ግን እኛን ያማክሩን እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደሚያስተካክሉ በሚያውቁትና በሚገባዎት ቋንቋ ግልጽ አድረግን ልናስረዳዎት ዝግጁ ነን።

በመጨረሻም አንድ የምወደው አጎቴ በልጅነት ጊዜዬ ያስጠነቀቀኝ እና የሰጠኝን ምክር እንደምሳሌ እና በትምሕርት ሰጪነነቱ ላቅርብና ልሰናበት።

«ለወዳጅ፣ ለዘመድ፣ ለሥራ ጓደኛ በምንም መልኩ የገንዘብ ብድር አትስጥ፣ ችግሩን መጥቶ ሲነግርህና ብድር ሲጠይቅህ ይመልስልኛል ብለህ ከማትጠብቀው ብድር ይልቅ ያቅምህን ያህል ስጦታ ስጥ። ያለበለዚያ ግን ብድር ብለህ ሰጥተህ ሳይሞላለት ከቀረ ገንዘቡንም ወዳጅነቱም አብረው ይቀራሉና ተጠንቀቅ» ያለኝ ትዝ ይለኛል። በእውነትነቱና እስካሁን ድረስ በመልካም  ምክርነቱ  እጠቀምበታለሁ።

– Mekuria M. Negia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top