Free songs
Home / Mark's Corner / Mark’s Corner 4: አገልግሎት እና የአገልግሎት ክፍያ

Mark’s Corner 4: አገልግሎት እና የአገልግሎት ክፍያ

Mekuria-M-Negia

Mekuria M. Negia

አገልግሎት እና የአገልግሎት ክፍያ

በዚህ መልዕክቴ የማተኩርበት ዓቢይ ጉዳዩ በአገልግሎት ሰጪዎች እና ተቀባዮች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት እና እርስ በእርስ በመጠቃቀም አብረው ለረዥም ጊዜ እንዴት ሊቆዩ ይችላሉ የሚለውን ደረጃ በደረጃ በማገናዘብ ላይ ይሆናል።

አንድ ሰው ለመኖር የሚያስፈልጉትን አቅርቦቶች በምርትነት በጥሬው ሊገዛ ይችላል። ይኽን የገዛውን ምርት ጥቅም ላይ ለማዋል ካሰበ በቅድሚያ መጥኖ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ወይም ለዚሁ ዝግጅት ሙያ ያለው ሰው ማማከር ይጠበቅበታል።

ባለሙያ ሲባል ደግሞ በሁሉም ነገር የዳበረ፣ የተመጣጠነ እና የደረጀ እውቀት ላይኖረው ይችላል። ስለዚህ ባለሙያ ስንመርጥ ብቃት ያለው ባለሙያ፣ በየጊዜውም በሙያው ላይ ለሚደረጉ እድገቶችና አዲስ ግኝቶች በቂ እውቅና ያለው፣ እንዲሁም በየጊዜው ሙያውን ለማዳበር እና ባለው ላይ ለመጨመር የሚጥር መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። ታዲያ ይኽ ባለሙያ ለአገልግሎት በተፈለገ ጊዜ አገልግሎት ለመስጠት የሚያጠፋውን ጊዜ ጨምሮ ለሙያው የሚጠይቀው ወጪ እንዳለ ማወቅ ሲያስፈልግ ስራውም ዋስትና ያለውና አስተማማኝ መሆኑን በቅድመ ድርድሩ ላይ ማወቅ ተገቢ ነው።

ለምሳሌ አንድ ምግብ ቤት ገብተን የምግብ ዝርዝር እና ዋጋውን የያዘው ሜኑ ካነበብን እና ምግቡን አዘን ከተመገብን በኋላ በመጨረሻው ላይ የሚቀርብልንን የአገልግሎት ሂሳብ መቀበያውን የምንመለከተው ሂሳቡ ትክክለኛ እና ባዘዝነው ዓይነትና በትክክለኛው ዋጋ መሰላቱን እንጂ በዋጋው ላይ ለመከራከር አይደለም። ስፔሻል ክትፎ ተመግበን ስፔሻል ባልሆነው የክትፎ ተመን ይሁንልን ብለን መከራከሩ ተገቢ አይሆንም። ለተስተናገድንበትና ለተደረገልን አገልግሎት እንደምንደሰት ሁሉ በክፍያውም ላይ ልንከፋ አይገባም።

ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ለሚሰጠው አገልግሎት የክፍያውን ተመን የሚያወጣው በአካባቢው ያሉትን ተፎካካሪዎች ተመልክቶና ለሚሰጡት አገልግሎት የሚጠይቁትን ክፍያ አጥንቶ እንዲሁም ተጠቃሚውን በማይጎዳ መልኩ ሆኖ ሳለ የተለምዶ ጠባይ ሆኖ አንዳንድ ተጠቃሚዎች በዋጋው ላይ ሳይከራከሩ ከከፈሉ የተነጠቁ ያህል ይሰማቸዋል። ይህም አጉል ጠባይ የአገልግሎት ሰጪውን ስሜት በብርቱ እንደሚጎዳ አይረዱለትም።

እኔን እንደምሳሌ ባቀርብ እና ከልምድ ያገኘሁትን የስምምነት ልምድ ለማካፈል ያህል፦ ከአንድ የአገልግሎት ሰጪ ድርጅት ጋር ስምምነት ሳደርግ ሌላው ቢቀር መሠረታዊ በሆነው ጉዳይ ማለትም የመነሻውን እና የከፍተኛውን የአገልግሎት ዋጋ በመረዳት ስምምነቱን እፈጽማለሁ። ከራሴ ሙያ ውጪ የሆነን አገልግሎት የምፈልግ ከሆነ ቅድሚያውን ለምፈልገው አገልግሎት ብቁ ሙያ ላላቸው የሀገሬ ልጆች እሰጣለሁ። የምፈልገውን አገልግሎት ለወገኖቼ ከሰጠሁ የምጠቅመው የሀገሬን ልጆችና ራሴንም ጭምር ነው።

በግልጽ እንደምናየው ባሁኑ ወቅት በተላዩዩ የሙያ መስኮች ማለትም፦ የሕክምና፣ የሂሳብ ስራ፣ የቤት ግዢና ሽያጭ፣ የብድር አገልግሎት፣ የኮምፒውተር፣ የቪዲዮና የፎቶግራፍ ሥራዎች፣ የሕትመት፣ የቤት ግንባታ፣የቧንቧ እና የኤሌክትሪክ ሥራ፣ የግቢ ሣር መቁረጥ፣እና የቤት ጽዳት የመሳሰሉና ከፍተኛ ትምሕርት ከሚጠይቁ ሙያዎች ጀምሮ እስከ የጉልበት ሥራ ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ወገኖች በቅርብና በውስጣችን አሉን።

ስለዚህ ለምንፈልገው አገልግሎት በሀገር ልጅ ማሰራቱ እነሱንም ራሳችንንም ከመጥቀሙ ባሻገር ለአገልግሎት የምናወጣው ገንዘብ በእኛው ዙሪያ የሚሽከረከር ይሆናል።
ለእኔ ከሚገርሙኝ ጉዳዮች አንዱ በዚህ የአገልግሎት ስምምነት ዙሪያ የምናደርገውን ወጪ ለሌሎች ተመሳስይ ሙያ ላላቸው ባዕድ ለሆኑ ክፍሎች ከመስጠት ባለፈ ራሳችንንም «አይ! ከሐበሻ ጋር መዋዋል» እያልን እንሰድባለን። ራስን በራስ መዝለፍ ማለት ይኽ ነው።

ነገር ግን በማኅበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ለፀሎት የምንሰባሰበው፣ ሠልፍ ወጥተን ስለሃገር የምንከራከረው፣ ኃዘን ሲገጥም ቀድመን የ«ድረሱልኝ» ጥሪ የምናሰማው ይኼው የምንዘልፈውን ሃገር ልጅ ሐበሻውን ነው። ይኽን በአንዳንዶቻችን ላይ የሚታየውን ደካማ አቋም እርማት ብናደርግበት እና እርስ በእርስ መጠቃቀም ብንለምድ እንደ «እስራኤላውያኑ» በሌላው ዜጋ የምንከበርና እኛም ባለንበት ሀገር በጋራ ባለፀጋ የመሆን ዕድላችንን የሰፋ ይሆናል። «እነዚህ እርስ በእርስ የሚናቆሩ ሳይሆን ኅብረታቸው ይገርማል…ለሌላውም ትምሕርት የሚሆኑ ናቸው» እንባላለን።

በመጨረሻም በራሴው ላይ በደረሰው አጭር ገጠመኝ የዛሬውን ምክሬን ልቋጭ።

ግዜው የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ነው። በጊዜው በዋሺንግተን ዲ.ሲ. የግሮሰሪ መደብር ለመክፈት አስቤ የመደብሩን የክራይ ውል ከተፈራረምኩ በኋላ ባለሙያ ፈልጌ መደብሩን ለንግድ በሚያመች መልኩ በማደራጀት ለእድሳት የሚፈጀውን ጊዜ እና ዋጋ ተነጋገርኩ። ስምምነቱ በንግግር ብቻ ሳይሆን በወረቀት ላይ በሰፈረ ውል በሁለታችንም ክፍሎች በፊርማ የፀደቀ ነው። ነገር ግን በውላችን መሰረት በተስማማንበት የጊዜ ገደብ እና ዋጋ ሊፈጸም ስላልቻለ በሕጉ መሠረት አገልግሎት ሊሰጥ ተስማምቶ የነበረው ክፍል በገባነው ውል መሠረት የተቀበለውን ገንዘብ እስከነኪሳራው በመመለስ ካሳ ከፈለ።

በሌላ ጊዜም እንደዚሁ የማቀዝቀዣ ፍሪጅ የሚገጥም ባለሙያ ጋር ባደረኩት ውል መሠረት በስምምነቱ ዕለት ሥራውን ጨርሶ ካለስረከበ በየዕለቱ $300.00 ከመጨረሻው ክፍያ ላይ ይቀንሳል የሚል ስምምነት የነበረበት ውል በመፈራረም የቅድሚያ ክፍያ $2000.00 እከፍላለሁ። ይኽን ሥራ በወቅቱ ሰርቶ ለማስረከብ የተዋዋለው ባለሙያ በተወሰነው ጊዜና ሰዓት ባለማስረከቡ ከዋናው ሙሉ ዋጋ ማለትም ከ$6000.00 የቅድሚያ ክፍያው ተቀንሶ የአምስት ቀን ታሳቢ $300.00 በድምሩ $1500.00 ብቻ በመቀበል ሥራውን ላዘገየበት ቀናት በውሉ መሰረት ከፍሎ በዚሁ በሠላም ተለያየን። ይኽንን ጉዳይ ራሴን ምሳሌ አድርጌ ለማንሳት የፈለኩት አለምክንያት አይደለም። በጽሑፍ የሰፈረ ውል እና ስምምነት ምን ያህል ጉልበት እንዳለውና አስፈላጊነቱንም ለአንባብያን ለመግለጽ ፈልጌ ነው።

በመጨረሻም ለማስገንዘብ የምፈልገው ከሀገር ልጅ ጋር በግል ትውውቅ ላይ በተመሠረተ መተማመን ብቻ ላይ ተመስርቶ አንድን ውል በወረቅት ላይ በስምምነት ሳያሰፍሩ ሥራን ማሰራት ነገ ሊያመጣ የሚችለውን ውዝግብ መዘንጋት እና ከሚያውቁት ወገን ጋር መጋጨት ስለሚሆን ምንጊዜም ቢሆን በጽሑፍ ላይ የሰፈረ ውል መፈጸማችንን ማወቅ ይኖርብናል። ከዚህም ጋር የስምምነቱን ምንነት በደንብ አንብቦ መረዳት ነገ ከሚያመጣው ቁጭት እና (ከሐበሻ ጋር መዋዋል» ከሚል ወገንን ከመርገም ያድነናል። መፍትሄውም ይሄው ነው።

– Mekuria M. Negia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top