Free songs
Home / Mark's Corner / Mark’s Corner 3: የንግድ ሥራን በጋራ አቋቁሞ መሥራት ጥቅም እና ጉዳቱ

Mark’s Corner 3: የንግድ ሥራን በጋራ አቋቁሞ መሥራት ጥቅም እና ጉዳቱ

Mekuria-M-Negia

Mekuria M. Negia

የንግድ ሥራን በጋራ አቋቁሞ መሥራት
ጥቅም እና ጉዳቱ

ባለፈው ወር እትም ላይ በዚሁ ገጽ ‹‹የንግድ ሥራን በግል አቋቁሞ መሥራት›› በሚል የንግዱ ዓይነት የሚኖረውን ጥቅምና ጉዳት በማነፃፀር ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ በዚህ ወር ደግሞ ‹‹በጋራ›› ለሚቋቋም የንግድ ዘርፍ ጥቅምና ጉዳቱን በተመለከተ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ምክሮችን ለማንሳት እሞክራሁ፡፡

የንግድ ሥራ በጋራ መስርቶ ለሚሠሩበት ስቴት ሕግ በመከተል መሥራት ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን አንዳንድ ጥቃቅን ጉዳትም ይኖረዋል፡፡ በመሠረቱ የተቀናጀ ጉልበት፣ ዕውቀት እና ገንዘብ ኃይል ፈጥሮ የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ የሚያጠያይቅ ባይሆንም፣ በአጋጣሚ የንግድ ዘርፉ ኪሣራ ውስጥ ቢገባ እንኳን ለአባሎቹ ኪሣራውን በጋራ ስለሚካፈሉት ጉዳቱ እንደግል የንግድ ዘርፍ አይከብድም፡፡ ግን ለማናቸውም የንግድ ዘርፍ ማቋቋም እና ሥራውን በተቃና መንገድ ለማከናወን በቅድሚያ ግልጽ የሆነና ሁሉም አባላት የተስማሙበት የፅሑፍ ውል አስፈላጊ ነው፡፡

በጋራ የሚሰራ ንግድ፡-

በምንኖርበት አገር አሜሪካ የንግድ ዘርፍን በጋራ አቋቁሞ መስራት በጣም የተለመደና ብዙም ጠቀሜታ ያሳየ የአሰራር ስልት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚጠቀሱት፣ በቀላሉ የምንጠቀምባቸው የስልክ፣ ኬብል፣ ኢንተርኔት ካምፓኒዎች በጋራ ሀብት የተቋቋሙና በየዕለቱ ለእድገት ከፍተኛ ቦታ በመስጠት አገልግሎታቸውን እያስፋፉ ከፍተኛ አትራፊ ሆነው  ለዓመታት አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆኑ የሚያገኙትንም ከፍተኛ ጥቅም ለአባሎቻቸው በዓመቱ መጨረሻ ላይ በውላቸው ደንብ መሠረት እንደየድርሻቸው ያከፋፍላሉ፡፡

በጋራ የተቋቋመ የንግድ ዘርፍ የውስጥ አሰራር ደንብ ሊኖረው የሚገባ ሲሆን፣ በዚህም ሥልጣኑ ከሚፈቅድለት ውጪ ያለውን ድርጅቱን የሚመለከት ማናቸውንም ውሳኔ በምልዓተ-ጉባዔ ወይም በቦርድ አመራር እያስወሰነ ሥራውን በማከናወን በንግድ ተቋሙ ውስጥ የአሰራርና የሥራ አፈፃፀምን ደንብ ይከተላል፡፡ ፡፡

የጋራ ሥራ ወይም ንግድ የተለያየ አወቃቀር ስልት ቢኖረውም በጣም እርግጠኛ መሆን የሚያስፈልገው በጽሑፍ የሰፈረ እና በሕግ ሁሉም በስምምነት ያጸደቀው የጋራ ሥምምነት እና የሥራ መተዳደሪያ ደንብ የግድ መኖር ይኖርበታል፡፡ ይኽም የዕለት ከዕለት ሥራውንም ሆነ የኃላፊነት ተዋረዱን በቀላሉ ተግባራዊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

የጋራ ሥራ ወይም ንግድ ላይ አባል የሆነ ሁሉም ወይም በከፊል በሥራ ላይ እውቀታቸውና ጊዜያቸውን ሊሰጡ ይችላሉ፣ ለዚህም ተገቢው ክፍያ ለሰሩበት መከፈል አለበት፣ እናም በመጨረሻም የጋራ ካምፓኒው አባል ስለሆኑ ደግሞ ከጥቅሙ ተካፋይ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የጋራ ስምምነቱ ላይ ገንዘብ፣ ኃላፊነት እና ዕውቀቱን ያስተባበረ አባል ሁሉ በሕጋዊ ውል የተቀመጠና የተስማሙ ከሆነ በቂ ይሆናል፣ ሌላ የተለየ ክፍያ የማይጠይቅበት አገልግሎት ይሆናል ማለት ነው፡፡

በታክስ አከፋፈል ላይ የሚኖረው ጥቅም፡-

የጋራ (ፓርትነርሺፕ) ንግድ መመሥረት ለአባሎቹ በግል ታክሳቸው ላይ የደረሳቸውን ዓመታዊ ክፍያ ትርፍም ይሁን ኪሣራ ፋይል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ የጋራ ካምፓኒው ግን በማትረፉ ታክስ አይከፍልም፡፡

ቀላል የሥራ መዋቅር እና ለማስተዳደር የማያስቸግር የጋራ ንግድ እና በፓርትነርሺፕ የሚሰራ፣ በቂ የስራ ዕቅድና ካፒታል ያለው ሲሆን የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡

ጉዳቶቹ፡-

በግልጽ በሕጋዊ ውል የተጻፈ ስምምነት የሌለው የጋራ የንግድ ዘርፍ ዋናው ቁልፉ በአባላት መካከል ሊኖር የሚገባ መግባባት እና ለንግዱ መሻሻል የጋራ ጥረት እንጂ፣ የንግድ ዘርፉን ባቋቋሙት አባላት መካከል መግባባት ከሌለ በአጭር ጊዜ የንግድ ዘርፉ ኪሳራ ውስጥ በመግባት መለያየትን ያስከትላል፡፡

የሥልጣን እና የውሳኔ ሰጪነት ኃላፊነትን በተገቢው መንገድ ክፍፍል ካልተደረገ እና የሥራ ክፍፍሉ በአግባቡ ተግባራዊ ካልሆነ የመለያየትና ኪሳራ ማስከተሉ የማይቀር ሲሆን ይኽንንም በአጭር መንገድ ለማስረዳት፡- ለምሳሌ አቶ ተስፋዬ፣ ወ/ሮ አጸደ እና አቶ ካሣ በጋራ የሚሰሩበት ለንግድ ዘርፉ የሚሆን ቢሮ ከፈቱ እንበል፡፡ አቶ ተስፋዬ ዛሬ ቢሮ ገባና ማንንም ሳያማክር እና የኃላፊነቱን ደረጃ በሕጋዊ መንገድ ባለመረዳቱ ለቢሮ የሚያስፈልጉ ናቸው የሚለውን የ$7,000 ዕቃ አዘዘ፡፡ ወ/ሮ አጸደ ደግሞ ቢሯዋ በጣም ያማረና የተሟላ እንዲሆን በፊናዋ $9,000 የቢሮ ዕቃ አዘዘች፣ አቶ ካሣ በራሱ መንገድ የሚመችና ለቢሮው ይሆናል የሚለውን $8,000 ዕቃ አዘዘ፡፡ እነዚህ ፓርትነርስ የሥራ ኃላፊነት እና የውሳኔ ሥልጣን ተዋረድ በስምምነታቸው ላይ በግልጽ በዝርዝር የተጻፈ ነገር ስለሌለ ያላቸው ካፒታል $14,000  ሆኖ ባለመነጋገር እና ሁሉም ለአዲሱ ቢሮ አሳቢ ሆነው $24,000 ለቢሮ ዕቃ ግዢ አዋሉ፡፡ ይኽም ካለመነጋገር እና በተናጠል የፈፀሙት ሥራ ተቋማቸውን በተገቢውና በህጋዊ መንገድ እየመሩ ለውጤት ከማድረስ ይልቅ ከጅምሩ ወደ ኪሣራ በመምራት በመጀመሪያው ወር ላይ ራሳቸው በፈፀሙት ግድየለሽነት ድርጅታቸውን አዘግቶ እነሱንም ይለያያቸዋል ማለት ነው፡፡

ከዚህም ባለፈ በጋራ ስምምነት እና በሕጋዊ መንገድ የፀደቀ ውል  ከሌለ፣ አንድ አባል መውጣት ቢፈልግ ወይም የሞት አደጋ ቢገጥመው የአባሉ ድርሻ ምን እንደሚሆን ከመገመት ባሻገር አወዛጋቢ ይሆናል፡፡ በጋራ ለመሥራት እና ለመነገድ በጋራ  ማሰብ እና መወያየት ያስፈልጋል፡፡

ብዙዎች በጋራ መስራት ቢፈልጉም ከማን ጋር እንደሚሰሩ ቅድመ ጥናት ባለማድረግ ከፍተኛ ችግር ላይ ሲወድቁ ይታያል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለማቃለልና ብሎም ለማስወገድ የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ ቢደርጉ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን አይጠራጠሩ፡፡

ንብረት፡-

በጋራ ለመሥራት የምናስበው ሰው በዕዳ ውስጥ የተዘፈቀ እና በቂ ንብረት ከሌለው ለወደፊቱ አስተማማኝነቱ ደካማ እና አደገኛ ስለሆነ ሌላ መፈለጉ ይመረጣል፡፡ ነገ ውዝግብ ወይም ክስ ቢመጣ የሌላውንም ንብረት ይዞ እንደሚሄድ ከወዲሁ መገመት ተገቢ ነው፡፡

ባሕርይ (ፐርሰናሊቲ)፡-

በጋራ ሲሰራ በመወያየት ያሉትን ችግሮችን በመፍታት ፋንታ የሚጨቃጨቅ፣ ለሥራ ባልደረቦቹ አክብሮት የሌለው፣ አስፈላጊ ባልሆነ ቦታ ሁሉ ስለ ድርጅቱ የውስጥ አሰራር ወሬ የሚነዛ፣ እወቁኝ እና የበላይ ነኝ ባይ ከሆነ ሰው መራቅ ብልህነት ነው፡፡

ተግባር፡-

በጋራ ለተቋቋወው የንግድ ዘርፍ ምን ያበረክታል? በሥራ ክፍፍሉ ውስጥ በየትኛው ዘርፍ ማገልገል ይችላል? የሚሉትን በቅድሚያ መመዘን ይገባል፡፡ በችሎታ ወይም በእውቀቱ አስተዋጽኦ ማድረግ የማይችል፣ ግን ገንዘብ ብቻ በማዋጣት በሥራ አፈጻፀም እና በውሳኔ ላይ እኔ በምለው ብቻ ተግባራዊ ይሁን የሚል ዓይነት ጋር የጋራ ንግድ ዘርፍ መቋቋም ከጥቅሙ ጉዳቱ በከፍተኛ ደረጃ ያመዝናል፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸውን ጠቃሚ ነጥቦች ጥቅም ላይ ያዋለ፣ በጥንቃቄ የተዋቀረ የጋራ ሥራ /ንግድ/ በእቅድ ከተመራና አፈጻጸሙን እየመረመረ እና እያረመ ከሰራ ትርፋማና ለአባሎቹም መከታ የሚሆን ድርጅት ይወጣዋል፡፡

– Mekuria M. Negia

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top