Free songs
Home / Mark's Corner / Mark’s Corner 2: ለዓመቱ መጨረሻ ሲዳረሱ፣ ታክስን በተመለከተ ምን ማድረግ ይኖርብዎታል?

Mark’s Corner 2: ለዓመቱ መጨረሻ ሲዳረሱ፣ ታክስን በተመለከተ ምን ማድረግ ይኖርብዎታል?

Mekuria-M-Negia

Mekuria M. Negia

ለዓመቱ መጨረሻ ሲዳረሱ፣ ታክስን በተመለከተ ምን ማድረግ ይኖርብዎታል?
(የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን)

በየዓመቱ ታክስን ፋይል ማድረግ የግድ ቢሆንም በቅድሚያ መረጃዎችን ማሰባሰብ ግን ሁሉም ታክስ ከፋይ የማይወደው ትልቁ የራስ ምታት ነው። ዓመት ሙሉ የሰበሰቡት ወረቀት ብዛት የትኛውን ከየትኛው ለመለየት እና የተገኘውንም የማሰባሰቡ ጉዳይ ብዙ የማይመቸው ግን ደግሞ ከፍ ያለ የታክስ ተመላሽ የሚጠብቁ እንዳሉ ከሥራ ልምዴ የተገነዘብኩት ነው።

 ከአገር ውስጥ ገቢ (IRS) ጋር ቁማር መጫወት በፍፁም አያዋጣምና ከፍ ያለ ተመላሽ በህጋዊ መንገድ ለማግኘት ብርቱ ጠንቃቃ መሆን እና የወጪዎችን ደረሰኞች አሰባስቦ ማዘጋጀት በእጅጉ ጠቃሚ ነው።

 ይኽንን ለማናቸውም ታክስ ከፋይ በሚገባው መንገድ በምሳሌ መልክ ላቅርበው።

 እኔ ቤቴ ውስጥ ታክስን በተመለከተ «ታክስ» የሚል ስያሜ የሰጠሁት ሳጥን አለ። በዚህ ሳጥን ውስጥ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በዓመቱ መጨረሻ ለታክስ ተመላሽ የምንጠቀምባቸውን ማንኛውንም ደረሰኞች እናጠራቅምበታለን። ዓመቱ ሲያልቅ በዓይነት ከፋፍለን በመደመር በየአርእስቱ በወረቀት ላይ በማስፈር ከገቢያችን እና ከኑሯችን ጋር ለውጥ የሚያመጣውን ተጠቅመን በታክስ ፎርሙ ላይ ሞልተን እንጠቀምበታለን ማለት ነው።

 በታክሳችሁ ላይ ሊሰፍሩ የሚገባቸውና ጠቀሜታ ያላቸውን

እንደሚከተለው ላቅርብ።

 ከጃንዋሪ መጀመሪያ እስከ ዲሴምበር መጨረሻ ዽረስ ከኪስ የወጣ የጤና እና የጥርስ ሕክምና በደረሰኝ የሚረጋገጥ፣

 ለፕሮፐርቲ (ቋሚ ንብረት) የተከፈለ ታክስ፣

 ለሞርጌጅ የተከፈለ ወለድ፣

 በገንዘብ እና በዓይነት የተሰጠ የእርዳታ ማረጋገጫ፣ (ዓመቱ ከማለቁ በፊት አሮጌ ልብሶች፣ ጫማ፣ እና የቤት ዕቃዎች ለሳልቬሽን አርሚ ወይም በቅርብ ለምታገኙት ዕርዳታ አሰባሳቢ ተቋም በመስጠት ደረሰኝ መያዝ)

 በዓመቱ ውስጥ በማናቸውም ቀን በሌባ የመዘረፍ አጋጣሚ ከተፈጠረ ይኽንኑ ለፖሊስ ሪፖርት አድርጎ የተዘረፉትን ጠቅላላ ንብረት ግምቱን በመጥቀስ በታክስ ፎርሙ ላይ በተገቢው ቦታ በመሙላት ሊጠቀሙ ስለሚችሉ የፖሊስ ሪፖርት ቁጥሩን በጥንቃቄ መያዝ፣

ከአንድ ሥራ በላይ የሚሰሩ እና የሥራ ቦታቸውም ከዋናው አድራሻ ውጪ እየወጡ የሚያከናውኑ ከሆነ (ለምሳሌ፡-ፒዛ ማድረስ ወይም ለሽያጭ ሥራ ከአንዱ ቀጣና ቢሮ ወደ ሌላው ቢሮ የሚዘዋወሩና አሠሪው የማይከፍላቸው) ከሆነ የመጓጓዣ ወጪ በግል መኪናቸው ለሥራ የተጠቀሙበትን ማይል እና የነዳጅ ወጪ በመጥቀስ ማቅረብ ይችላሉ። ነግር ግን ይኽንኑ ወጪ በትክክል መመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። (Mileage Log)

 ለታክስ ማሰሪያ የከፈሉበት ደረሰኝ፣

 በተጨማሪም ከሥራዎ ጋር በተያያዘ የተደረጉ ወጪዎች (የሥራ ልብስ፣ ለሞባይል ስልክ፣ ከሥራ ጋር የተገናኘ ሥልጠና፣ ከቤት የሚሰሩ ከሆነ ማንኛውንም ከሥራው ጋር የተገናኘ ወጪዎች አሰባስበው በማስላት ዓመቱን በሙሉ ቢሮአቸው ክፍት ከሆነና ተከታታይ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የታክስ ባለሙያ በመምረጥ ማሰራት የአሜሪካ ነዋሪነትዎ ግዴታ ነው።

 የአገር ውስጥ ገቢ (IRS) የሚመክረውና ለታክስ አሰሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው አንዱ ቁልፍ የሆነ ምክር ቢኖር፡- በታክስ ጊዜ ጊዜያዊ ቢሮ በመክፈት ለአንድ ሰሞን ብቅ በማለት የታክስ ሥራን ሽፋን በማድረግ «ከፍተኛ የታክስ ተመላሽ እናስገኝልዎታልን» ከሚሉ ክፍሎች በብርቱ መጠንቀቅና፣ ከታክስ ጋር በተያያዘ ከIRS ሊመጣ የሚችለውን ጥያቄ እንኳን ለመመለስ በነበሩበት ቢሮ ሊገኙ ከማይችሉ ጊዜያዊ ታክስ ሠራተኞች መራቅ በእጅጉ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ ሕጋዊ በሆኑና በዚህ ሙያ የተሟላ ዕውቀት ባላቸው የታክስ ሠራተኞች የታክስ ተመላሽዎን ማሰራት በተከታታይ ሊመጣ ለሚችለው ጥያቄ ታክስዎን ካዘጋጀው ህጋዊ ክፍል ፈጣን መልስ ሊያገኙ ያስችልዎታል።

 ታክስ ለመክፈል ወይም የታክስ ተመላሽዎን የሚያዘጋጅልዎ

ባለሙያ ሲመርጡ ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ መመዘኛዎች

 1. በቂ የሆነ የታክስ ሥራ እውቀት ያለውና ባዘጋጀው የታክስ ፎርም ላይ የIRS (አገር ውስጥ ገቢ) የሙሉ ሥልጣን የምዝገባ ቁጥር ያለውና ሊመጣ የሚችለውን ኃላፊነት የሚጋራ፣

2. ሙያውን እና ተጠቃሚውን የሚያከብር፣ በፈለጉት ጊዜ የሚያገኙትና በስልክም ሆነ በአካል ለሚቀርብለት ታክስ ነክ የሆኑ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥና ቢሮው ዓመቱን ሙሉ ለደንበኞቹ ክፍት የሆነ፣

3. ለታክስ ማሰሪያውን የአገልግሎት ወይም የሙያ ክፍያ ከሚያገኙት የታክስ ተመላሽ ጋር በፐርሰንት ወይም በኋላ ችግር ውስጥ የሚከት ጊዜያዊ ተስፋ በመስጠት የማይገባዎትን የታክስ ተመላሽ አስገኝልዎታለሁ ይኽን ያህል ይክፈሉ ከሚሉ እና በቂ እውቀት ሳይኖራቸው የአገልግሎት ክፍያው ከሚጠይቀው በታች ከሚጠይቁ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እንደዚህ ዓይነቶቹ በታክስ ወቅት እንደአሸን የሚፈሉ ጊዜያዊ የታክስ ሰራተኞች የታክስ ሠነድዎን ሊያበላሹብዎት እና በIRS በታክስ አጭበርባሪነትም ጥቁር ነጥብ መዝገብ ውስጥ ሊያስገብዎት መቻላቸውን አይዘንጉ።

4. በማንኛውም ወቅት ከIRS ሊመጣ የሚችለውን ጥያቄ መልስ ሊሰጡ የሚችሉና ለዚህም አገልግሎት ምንም ዓይነት ተጨማሪ ክፍያ የማይጠይቁ መሆናቸውን ያረጋግጡ፣

5. በመግቢያዬ የጠቀስኳቸውን ሠነዶች እና የተለያዩ መረጃዎችን አሟልቶ ያቀረበ ታክስ የሚያሰራ ደምበኛ፣ ከታክስ ሠራተኛው የሚጠብቀው ባቀረበው መረጃ መሠረት ሁሉንም ተመላሽ የሚያስገኝለት የታክስ ባለሙያ መሆኑን በቅድሚያ ማረጋገጥ፣

6. ያልተሟላ እና ባዶ ፎርም ላይ ይፈርሙና ሌላውን እኔ እጨርሰዋለሁ ከሚል የታክስ አዘጋጅ በእጅጉ መራቅ፣

7. ከመፈረምዎ በፊት የተሞላውን ፎርም ከመጀመሪያው እስከመፈረሚያው ድረስ በትክክል ለመሞላቱ ደጋግሞ በማጣራት ማረጋገጥ በአይዘንጉ፣

8. በፊት፣ የታክስ አዘጋጁ ሕጋዊ የአዘጋጅነት መታወቂያ ቁጥር፣ የቢሮ አድራሻና ስልክ ቁጥር በፎርሙ ላይ መስፈሩን እና ኮፒውን በእጅዎ ማስገባትዎን ማረጋገጥ፣

9. የታክስ ሠነዶችን የምናሰራው በዓመት አንድ ጊዜ በመሆኑና ይህም የታክስ ሠነድ በማናቸውም ጊዜ ለቤት ግዢ እና ለመኪና የባንክ ብድር ጥያቄ ወቅት በብዙዎች የሚቀርብ በመሆኑ በጥንቃቄ መሰራትና መዘጋጀት ያለበት ከፍተኛ ሠነድ ነው። ስለዚህ ለዚህ ፍፁም የግል ሚስጥራዊ ለሆነ ሠነድ የሚመርጡት የታክስ አዘጋጅ ሕጋዊና እነዚህን የግል ሠነዶች በሚስጥራዊነት የሚጠብቅ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ሲገባ ለዚህም የታክስ አገልግሎት ተመጣጣኝ ክፍያ ለመክፈል ራሳችን ማዘጋጀት ይጠበቃል።

 ከላይ የተጠቀሱትን ምክሮች እንደሚጠቀሙበት ተስፋ በማድረግ በዚህ ላይ ያልተጠቀሱ፣ ነገር ግን ሊያውቁትና ሊብራራልዎት የሚፈልጉት ተጨማሪ ጥያቄ ካለ በቢሮ ስልክ ቁጥር 703-256-9113 እና 202-541-7979 ወይም በእጅ የስልክ ቁጥር 202-253-4414 በመደወል የበለጠ ማብራሪያ ሊያገኙ ይችላሉ።

– Mekuria M. Negia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top