Free songs
Home / Mark's Corner / Mark’s Corner 11: አብሮ የማደግ ንግድ

Mark’s Corner 11: አብሮ የማደግ ንግድ

Mekuria-M-Negia

Mekuria M. Negia

አብሮ የማደግ ንግድ

በቁጥራችን ብዛት ተፈላልገን በአንድ አካባቢ መኖር የመውደዳችንን ያኽል እና የማደግ ፍላጎታችንን በሚመለከት እኛ ኢትዮጵያውያንን የሚያክል ሌላ ዜጋ ይኖራል ለማለት ያስቸግራል። ተባብሮ የመሥራቱን ባህል ግን ገና ያላዳበርነውና ብዙ ውይይት እና መተማመንን መገንባት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በዕለት ተእለት ኑሮአችን፣ በየቀኑ በየሳምንቱና በየወሩ የሚያስፈለጉንን ፍጆታዎች ሁሉ ከሌሎች ቸርቻሪዎች በምንሸምትበት ወቅት እነሱን እያበለፀግን እና ደግሞ የነገው ሌላ የገበያቸው ምንጮች እየሆንን እንደምንመጣ አያጠያይቅም።  ከእነዚህ ቸርቻሪዎች የምንሸምታቸው ሸቀጦች የምናዘወትራቸው የንግድ ድርጅቶች ትርፍ እንዲያገኙ እገዛ ያደርጋል። የእኔ አስተያየት ለምን እነዚህ የንግድ ድርጅቶች ትርፍ አገኙ ሳይሆን እኛው እነዚህን የንግድ ድርጅቶች መሆን አንችልም ወይ? ነው።

እስቲ ለአንድ አፍታ ወገኖቻችንንም ሆነ ሌሎችን ሁሉ ሊያረካ የሚችል የረሳችን የሆነ የገበያ ስፍራ ቢኖረን ብለን እናስብ? ይኽን ለማድረግም የሚጎድለን ምንም ችግር እንደሌለብን ግምት ውስጥ በማስገባት።

እንዲህ በብዛት በምንኖርበት ከተማ እና በአካባቢው የምርጫ ፖለቲካም ተጽእኖ መፍጠር መቻላችንን ባረጋገጥንበት ምድር ላይ ከተቀጣሪነት ወደ ባለቤትነት ለመሸጋገር ምን የሚያግደን ነገር ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁ?

በምንኖርበት አገር ስለአክሲዮን፣ ስለ ኢንቨስትመንት በትምህርትም ሆነ በልምድ በቂ እውቅና ያገኘን ሰዎች እንኖራለን የሚል ግምት አለኝ። እነዚህ ግለሰቦች ተሰባስበው እና እቅድ አውጥተው ኅብረተሰባችን ከፍተኛ የንግድ ተቋም ባለቤት የሚሆንበትን መንገድም ለመንደፍ አቅሙ በሚገባ እንዳላቸው በተለያየ መንገድ አስመስክረዋል። የሙያ ሰዎች ድኽነት የለብንምና።

ግን ይኽን ለማድረግ የሚጎድለን ነገር ምንድነው? ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ፣ በቅድሚያ የማስበው መተማመንን በመካከላችን ያለመገንባት ይመስለኛል። ይኽንን ለማስወገድ ደግሞ በጥቂት በሚተማመኑ ቤተሰቦች፣ ጓደኞች እና ቡድኖች መጀመሩ እና ውጤቱንም ለሌላው ማስተወወቁ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ለወደፊቱም ሌላው እንዲከተለው የሚረዳ ጅምር ይሆናል ባይ ነኝ።

ራሳችንን ችለን የምናቋቁመው የንግድ ድርጅት ከጅምሩ ልምድን እያዳበረ ጎን ለጎን ከመሠረታዊ ችግሮቻችን ጋራ ልንፈታቸው ወደሚገቡ ሌሎች ጠቀሜታዎች ሊያሸጋግረን ይችላል። ለምሳሌ ከታላላቅ የንግድ ድርጅቶች ጎን ለጎን፣ የሕፃናት መዋያ ማቋቋም ሲቻል፣ እኛም እንደሌሎች ስደተኞች በራሳችን ዜጎች አጋጣሚውን በመጠቀም ሕፃናት ባህልና ታሪካቸውን ከመሠረቱ በማስተማር ልናንፃቸው የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል።

የወገን ገንዘብ እና እውቀት ከተባበረ የአሜሪካን የንግድ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት አክሲዮን ገዝተን ሁላችንም አቅማችን በሚፈቅደው መሠረት ተሣታፊ ከሆንን ካሰብነው በላይ  ማድረግ የምንችል ጥሩ ጥንቁቅና ጠንካራ ሠራተኞች መሆናችን ማስመስከር እንችላለን።

በቅድሚያ በመካከላችን መተማመንን እንፍጠር፣ ከዚያም የምናቀቋቁመው ድርጅት ዋስትና እንዲኖረው ሕጋዊ እናድርገው። ይኽ ከሆነ የምናጣው ምንም ነገር አይኖርም። አለመተማማን የሚያመጣው መዘዝ እነኳን ቢኖር ሕጋዊ ድርጅትነቱ  በሚሰጠው ዋስትና የሚፈታ ይሆናል።

እስካሁን በኖርንበት ጊዜ ይኽን ለማከናወን በግል ብዙ ተዋያይተናል። ብዙ ሙከራዎች በወሬ ቀርተዋል። አንድንድ ጅምሮችም ዳር የሚያደርሳቸው ጠፍቶ ተበትነዋል። ሌሎች ከእኛ በኋላ መጥተው ትናንት እኩል ከኛው ጋር ተቀጣሪ ሠራተኞች የነበሩ ዛሬ በጥረታቸው በፈጠሩት ድርጅት ቀጣሪዎቻችን ለመሆን በቅተዋል። እኛም የነሱን ካሰቡት ዓላማ መድረስ ተመልክተን «እኛም እኮ ይኼንን ዱሮ ጀምረነው ነበር» እያልን እንደተረት ማውራታችን አልቀረም።

ገጣጥመን መሠረቱን አሣምረን ብንሠራው ሥራው ራሱን እየመራ ትርፍን ሲሰጠን እኛ ደግሞ ዘና ብለን መኖር ና ስለጤናችን ስለ የእረፍት ጊዜ የት እንደምናሣልፍ ይሆናል ትንሽ ጊዜ የሚወለድብን ሃሳብ ሌላ በራሱ ይመጣል ማለት ነው።

እኛ ለእኛ ብንነግድ ተጠቃሚ እንጂ ጉዳት የማይኖረው እድገት ሲሆን ገበያውን አድምቀን ገዢዎቹ እኛ እና ሸቀጣችን የሚወዱ፣  ትርፉም ከወገን እጅ የማይወጣ፣ በውስጡ የሚሠሩት ሠራተኞችም ባብዛኞው የኛው መሆናቸው ተጠቃሚነታችንን ባለ ብዙ ዘርፍ ያደርገዋል።

እነ እገሌ የሚባሉ ኮሚኒቲዎች ይኽን አደረጉ ብሎ ከማውራት እኛው በእኛው ማድረግ የምንችለውን ተግባራዊ ለማድረግ በኅብረት ጥረት እናድርግ። ይኽን ተግባራዊ ለማድረግም የምንችልበትን ወይይት ለማድረግ እና የተወሰኑ ቁጥር ባላቸው ግለሰቦች ለመጀመር ከአሁኑ መሠረት እንጣል። ይኽንን ተግባራዊ ለማድረግ እና በጅምሩ ላይ ውይይት ለማድረግ በቅርቡ ስብሰባ የመጥራት እቅድ አለኝ።

ቦታ እና ሠዓቱን ከ August 20-2013  በኋላ በ2022534414 ቢደውሉልኝ ለማሳወቅ ዝግጁ ነኝ።

– Mekuria M. Negia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top