Free songs
Home / Mark's Corner / Mark’s Corner 10: ገቢ እና ወጪን ብቻ ሳይሆን ታክሱንም አይዘንጉ

Mark’s Corner 10: ገቢ እና ወጪን ብቻ ሳይሆን ታክሱንም አይዘንጉ

Mekuria-M-Negia

Mekuria M. Negia

ገቢ እና ወጪን ብቻ ሳይሆን ታክሱንም አይዘንጉ

የሚለንን ያህል፣ ለዚያ ገቢ መጎልበት ተጨማሪ ማምጣት እና ሰፋ አድርገን መኖር እንድንችል ገቢ ለማምጣት ከምንደክመው አስር እጅ እንኳን የማንሞላው ለወጪያችንና ለገቢ ቀረጥ (ታክስ) ፕሮግራም ማድረግና ማመጣጠን  ያለመቻላችንን ተገንዝበዋል?

ይኽ በተለይ በእኛ ሰዎች ላይ አመዝኖ የሚታይ ያልተፈታ ችግር ነው። ሌት ተቀን ደክመን ያገኘነው ሁሉ ቶሎ ተመልሶ ሲወጣና ከእጃችን ሲለየን ማየት የሁልጊዜ ተግባራችን ሆኖ እንዳይቀጥል ባለኝ ሙያ ትንሽ ምክር መሰንዘር ወገንን መርዳት ሰለሆነ በዛሬው መልዕክቴ ይሕንኑ ላሰምርበት ፈለግሁ። ይኽንን ምክር በጥሞና ካነበቡት በኋላ ከቤተሰብ እና ከጓደኛ ጋር ቢነጋገሩበት፣ የጥቅሙና የጉዳቱን ገፅታ ሊመዝኑ ስለሚችሉ፣ በምክሩ ተጠቅመው የደረሱበትን ሁኔታ መልሰው ቢያካፍሉን ደግሞ ሌሎች ወገኖችዎን በበለጠ እና በዳበረ መልኩ እንደሚረዳ አይጠራጠሩ። መደጋገፍ እና አብሮ ማደግ ማለት ይኽ ነውና።

ገቢ ስንል ፦

በተሰማራንበት የሙያ መስክ በተለያየ መልኩ ገቢ ሊኖረን ይችላል። ከነዚህም ለምሳሌ በሥራ ተቀጥረን ከምናገኘው ደመወዝ፣ በራሳችን ሰርተን የምንሰበስበው ፣ ንግድ ነግደን የምናተርፈው ፣ ከባንክ ወይም በሌላ መልኩ የምናገኘው የአራጣ ገቢ፣ አከራይተን የምናገኘው፣ በተለያየ መንገድ ያገኘነውን ገቢ በሙሉ ያጠቃልላል።

የገቢ አጠቃቀም እና ወጪን የመቆጣጠር ጥቅም

በመሰረቱ ገቢ ሲኖረን እንደገቢያችን መጠን ለመኖር ብናስብም አንዳንዶቻችን ደግሞ እንደጎረቤታችን ለመኖር እንሞክራለን፡፡ ለምሳሌ፦ በወር $5000 የሚከፈለው ወይም የሚያተርፍ ሰውና በወር $2000 የሚከፈለው ወይም የሚያተርፍ እኩል መኖር የሚችለው ምናልባት በቀን ሶስት ጊዜ መመገቡ ካልሆነ በስተቀር እኩል ወጪ ለማድረግ ስለማይችሉ፣ በገቢ መጠን መኖር ካልተለማመድን፣ ትንሽ ያገኘው ሰው የእለት ተእለት ኑሮውን ሲያማርርና ገቢው በምርታማነቱ ላይም ተፅእኖ በማሳደሩ መቀነስ አዝማሚያ ሲያሳይ፣ ከሰዎች ጋር ያለውን መከባበር ፍቅር ሲያደፈርስ ይታያል፡፡ ፋይናንስ ለኑሮአችን ለእለት ተእለት ውሎአችን ወሳኝ እና ዋናው ስለሆነ በአጠቃቀም በኩል  ካለፈው እየተማርን የዛሬውን በማስተካከል የወደፊቱን እያሰብን መሆን አለበት።

ሁላችንም ወደዚህ ምድር ስንመጣ ምንም አልነበረንም። ነገርግን ያደግንበት ሁኔታና ቦታ ምናልባት አንዳችንን ፈጣን አሳቢ፣ አንዳችንን አዝጋሚ ወይም ችላ ባይ ሆነን ካልሆነ በስተቀር በተሰማራንበት የኑሮ መስክ አነሰም በዛም ገቢ አለን። ይህን ገቢ በተገቢው መንገድ እና በሥነ-ሥርዓት  ለመጠቀም ደግሞ የዘመኑን የሂሳብ (ገቢ) አጠቃቀም ብንከተል ተጠቃሚ እንደምንሆን አያጠያይቅም። ይኽም ዘዴ በፕሮግራሙ በሚኖሩ ሰዎች የተፈተነ፣ አጥጋቢ ውጤት ያለውና እራሱን በአቅምና በገቢ መጠን ለመኖር የሚያስችል መርሃ ግብር ነው።

በምሳሌ ለማሳየት ያህል የእኔ የወር ገቢዬ $3000 ቢሆን የመጀመሪያ 1/3 ወይም $1000 ከገቢው ላይ ለመጠለያ የሚከፈል ይሆናል ማለት ነው። የምፈልገው ወይም የቤተሰብ ብዛት ሁኔታ መኖር ከምፈልገው አካባቢ በ$1000 ቤት መከራየት ወይም ገዝቶ የባንክ እዳውን በየወሩ ለመክፈል አይችል ይሆናል።

በዚህ ሁኔታ ላይ የምገኝ ከሆነ አንድም ገቢዬ የሚጨምርበትን መንገድ በቶሎ መፈለግ አሊያም ተመጣጣኝ ክፍያ ላደርግ የምችልበትን መፍጠር እንጂ $2000 ለቤት ክራይ ወይም ያለ አቅም ለባንክ እዳ ክፍያ አውሎ በቀረው $1000 ተጨናንቆ መኖርና ነገ ባጋጣሚ ያ ገቢ ቢቋረጥ ራስንም ቤተሰብንም ይዞ የከፋ ችግር ውስጥ መግባትን መጋበዝ ነው።

ለዚህ መፍትሄው ከገቢያችሁ 1/3 ለቤት ክራይ ወይም ሞርጌጅ ክፍያ፣ 1/3 ለምግብ ለልብስ ለመድሃኒት ለመዝናኛ ….1/3 ተቀማጭ የማይነካ ለክፉ ቀን መጠባበቂያ  ቢሆን የተረጋጋ ኑሮ እና ዘዴውም ውጤታማ ይሆናል።

ሌላው በአቅም ባለመኖር ወጭን ባለመቆጣጠር የሚፈጠር ብድር ይከማችና ከዚያ እንዴት መውጣት እንዳለብን በየቀኑ ስለዚህ በማሰብ እና በማንሰላሰል ጭንቀት ውስጥ ገብተን ጊዜያችንን እናጠፋ ይሆናል፡፡ ወርቃማው  ቀን ዕዳን  በማሰብ  ሲያልቅ ማየት  መጨናነቅ ይፈጥራልና እባካችሁ ማሰብ ብቻ  መፍትሔ ስለማይሆን ተረጋጉና ወይ ባለሙያ አማክሩ ወይም ደግሞ ተራ በተራ ትልቅ ፐርሰንት ወለድ የሚጠይቀውን መጀመሪያ በዛ አድርጎ በመክፈል ወደ ዜሮ ዕዳ ማምጣት ከአቅም ጋር በተገናዘበ ሁኔታን መጨነቅን ማስወገድ መሆኑን ተገንዘቡ።

ባለቤቴ ይህን ኩፖን  የሚሉትን ዓይተን ከመጣል ለምን ለሚያስፈልገን እና መግዛታችን ለማይቀር ሸቀጥ የሚመሳሰለውን ብላ ሰብስባ የምብግና የልብስ የመሳሰሉት ሱቅ ስትሄድ  ብዙ ጊዜ ተጠቅማ አታውቅም ነበርና በኩፖን ያተረፈችውን ስታሰላው ቀላል ቁጠባ እና ወጪን ማዳን መሆኑን መገንዘቧን ተወያይተንበታል። በአንድ   ሳምንት ብቻ በ $150 ሸቀጥ ስትገዛ $29 አትርፋለች፡፡ ጥቅሙ ቀላል ይምሰል እንጂ ይኽንን ከየሳምንቱ ወጪ ጋር ብታሰሉት $29 X በ52 ሣምንት=$1508  በዓመት ማለት ነው፡፡

ሌላውና ያው የኔ ወገኖች የተቸገሩበትና መልመድ ያቃታቸው የገቢና የወጪ ሰነድ ሰብስቦ ማስቀመጥ ነው፡፡ ነፃ ጊዜ ሲኖራቸው ያን እየመረመሩ ማስቀመጥ ሲችሉ ወደፊት ለጉዳዩ ሲፈልጉት መተራመሳቸው የተለመደ ነው፡፡ ሰነድ በአግባቡና በተስተካከለ ሁኔታ ከያዝን ጊዜና ገንዘባችንን ይቆጥባል፤ በፈለግነው ጊዜም በቀላሉ ይገኛል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ገቢ ካለ የገቢ ታክስ (ታክስ) መክፈል ግዴታ መሆኑን እያወቅን ይህን ገቢ ለመሰብሰብ ያወጣነውን ወጪ በመረጃ አስደግፈን ገቢውን ለመሰብሰብ ያወጣነውን ወጪ ማቀናነስ ብንፈልግም መረጃውን ግን (የሀገር ውስጥ ገቢ / IRS  ) በሚጠይቅ ጊዜ የዛሬ ሶስት ዓመቱን ከየት ነው የማመጣው የሚል ጭንቀት ውስጥ እንገባለን። የሀገር ውስጥ ገቢ (IRS) ሕግ መረጃ የሚጠይቅበት 5 ዓመት ጊዜ ገደብ አለው ፡፡ እኛ ደግሞ ሦስት ዓመት አለን፡፡ የረሳነውን ገቢም ሆነ ወጪ መጨመር ወይም መቀነስ እንችላለን ማለት ነው፡፡

ምክሬን ለማጠቃለል በመጨረሻ ለማሳሰብ የምወደው በአቅም መኖር ገቢን በአግባቡ መጠቀም ሠነድ በዓይነቱ ሰብስቦ በትንሹ ለአምስት ዓመት በቀላሉ በምታገኙበት ሁኔታ ማስቀመጥ፣ ወረቀት መሰብሰብ ካልፈለጋችሁ ደግሞ እድሜ ለቴክኖሎጂ ስካን አድርጋችሁ በተለያየ መልኩ ማቆየት ትችላላችሁ፡፡ ይኽን ማድረግ ደግሞ አንድ ቀን የIRS ባለዕዳነት ሊያድነን ይችላል።

– Mekuria M. Negia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top