Free songs
Home / Editorials / Editorial 9: መስማት እንጂ ማየት የተሳናቸው

Editorial 9: መስማት እንጂ ማየት የተሳናቸው

Nafqot Editorial

Editorial

መስማት እንጂ ማየት የተሳናቸው

  የሰው ልጅ እንደተፈጥሮው እና እንደ ልምዱ አንድን ነገር የመቀበል ባሕሪዩም ይለያያል። አንዳንዱ ከሰው የሰማውን ነገር ለሌላ ሰው ከመንገሩ በፊት የነገሩን ትክክለኛነት ማጣራት ሲፈልግ፣ ከፊሉ ደግሞ የሰማውን ነገር ሳይጨምርና ሳይቀንስ ለሌላው ማውራት ይወዳል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ የሰማውን ነገር ቆርጦ እና ቀጥሎ ለእሱ በሚያመቸው መንገድ ላገኘው ሁሉ የሚያቀብል አለ። ቆርጦ ቀጥል የሚሉት ዓይነት።

ለምን ይሆን ሰዎች ከማየት ይልቅ መስማት የሚቀናቸው? ለማንበብ ወይም በቦታው ከመገኘት ይልቅ ከሌላው ሰው መስማት ቀላል ስለሆነ ወይስ የጊዜ ቁጠባ?

ዘመኑ አብዛኛውን የሰው ልጅ ወደ ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ወለድ ወደሆነው የኢንተርኔት እይታ ወደማተኮር ካሸጋገረው ከረምረም ብሏል። በእርግጥም ይኽ የኢንተርኔት ዘመን ከጊዜ ቁጠባ ባለፈ በከፍተኛ ጥናት የተደረሰባቸውን መረጃዎች በአንድ መስኮት ስር አቀናጅቶ በማቅረብ በኩል ወደር የማይገኝለት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፣ በማድረግም ላይ ይገኛል። እንዲህም ሆኖ በዚህ የዌብሣይት ድረጎፆች ላይ ያሉት ቁም ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ለቁጥር ያስቸገሩ ሀሰተኛ መረጃዎችና አሉባልታዎች እንደሚገኙበትም ከማንም የተሰወረ አይሆንም።

በዚህ መልእክቴ ላይ እንኳን ማቅረብ የፈለኩት የኛው ጉድ ስለሆነው እና ሥር እየሰደደ ስለመጣው ሳያዩ እና ሳያረጋግጡ ሀሰተኛ ወሬ ማባዛት እና ማዛመት ስለሚወዱ ግለሰቦች ነው። የኢንተርኔቱንም የሀሜትና የሃሰት መረጃዎች በተመለከት የምለውም አላጣም።

አስቲ ያልተፈጠረን ነገር ፈጥሮ እና ከሌላ ሰምቶ ሳያጣሩ ወሬ ማዛመት የሚወዱ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።

እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ያላቸው ማኅበራዊ እድገት ከአሉባልታ ጋር የተያያዘ እና ባደጉበት ቤተሰብ ወይም መንደር ውስጥ ተመሳሳይ ባሕሪይ በሚታይባቸው ግለሰቦች የተሞሉ እንደሆኑና ከእነሱ ይህንን በማኅበረሰባቸው ውስጥ ነውር የሌለበትን ጠባይ እንደቀሰሙ ለመረዳት ብዙም ምርምር አያስፈልገውም።

በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ያድጉና የልጅነት ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ ሲሸጋገሩ፣ ያ ባሕሪይ አብሯቸው ያድጋል። ጭራሹኑንም ከጊዜው ጋራ እያዳበሩት የግል መታወቂያና ልምዳቸው በማድረግ ይጣባቸዋል።

አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ስውር እና በሌሎች ሰዎች ወይም በኅብረተሰቡ ዘንድ በጨዋነታቸው የሚታወቁ ሆነው ዋናው የሐሰት ወሬ አፍላቂና አቀባይ በመሆን ከበስተኋላ ሆነው በመስራት በሌሎች የተከለሉ ናቸው። (ማስተር ማይንድ) እንደሚባሉት ዓይነቶች መሆናቸው ነው። እነሱ በፈለሰፉት የሐሰት ወሬ ሌሎችን ለመጉዳት በፈለጉበት መንገድ ይጠቀሙበታል።

እነዚህ እኩይ ፍጡራን ሌላውን ለመጉዳት ሰው ወይም ድርጅት አይመርጡም። የሚያናፍሱት ወሬ በሌላው ተደማጭነት እስካገኘ ድረስ የአሉባልታ ሐራራቸውን መወጣት ቀዳሚ ዓላማቸው ነው።

አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ።
ሁለት ተፋቃሪዎች ሁለት ጉልቻ ለመመስረት ይስማሙና የሥርጋቸውን የግብዣ ጥሪ ከአንድ ወር ቀደም ብለው ለእንግዶቻቸው ይበትናሉ። ይኽ በሆነ ከሣምንት በኋላ አንድ ያልተጠበቀ ወሬ በአካባቢው ይናፈሳል። ወሬውም «በቅርቡ ባል ልታገባ የተዘጋጀችው ዕጩ ሙሽራ ሃገር ቤት እያለች በሴትኛ አዳሪነት የምትተዳደር እንደነበረ የሚያበስር ዜና ነበር»

ይኽ ዜና እየተባዛ ይሄድና የወደፊት ባለቤቷ ከሚሆነው ዕጩ ሙሽራ ጆሮ ይገባል። ይኽንንም ዜና የነገሩት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ጓደኞቹ ነበሩ። እንደያውም ለአንደኛነት ሚዜ የተመረጠው ከጎኑ ሊቆም እንደማይችል እና ሚዜነቱን ማውረዱን ይነግረዋል። በዚህ ሁኔታ ግራ የተጋባው ዕጩ ሙሽራም ለፍቅረኛው ያለው ቅርበት እየሻከረ ሲመጣ እሷም በበኩሏ በነገሩ ተቸግራ የቅርብ ጓደኞቿን ማማከር ስትጀምር፣ ወሬውን የሰሙ ይነግሯታል። ይኽ በዚህ እንዳለ ወንዱ አፍቃሪ ስለነገሩ ፍርጥ አድርጎ ለእሷ በመንገር ጋብቻውን እንደማይፈፅምና ሠርጉ እንደማይከናወን ይነግራታል። የረዥም ጊዜ ፍቅረኛዋን በትዳር ለማሰር አንድ ሐሙስ የቀራት ሴትም አእምሮዋ በጣም ይጎዳል። ራሷንም ለማጥፋት ከመጠን በላይ የሆነ የሕመም ማስታገሻ እንክብል በመውሰድ ራሷን ታጠፋለች። ይሕ ታሪክ በዚሁ ተደመደመ። ይኽች ሴት ግን እንኳን በሴትኛ አዳሪነት መተዳደር ቀርቶ የሴትኛ አዳሪዎችን ሠፈር የማታውቅ ንፁሕ ሴት ነበረች።

ይኽን ታሪክ አለምክንያት አላነሳሁትም። አንዳንዴ የወሬ ፈጣሪዎች እኩይ ተግባር ምን ያህል ሌላውን የመጉዳት አቅም እንዳለው ለማሳየት ፈልጌ እንጂ።

እንዲህ ያሉት የውሸት ዜና ፈጣሪዎች ዋና ዓላማቸው ምንድነው? ብላችሁ ራሳችሁን ብትጠይቁ ለምናልባቱ መልስ ልታገኙለት አትችሉ ወይም እንቆቅልሽ ይሆንባችሁ ይሆናል።

የእነዚህ ግለሰቦች ዓላማ የተፈጠሩበትን እና የተካኑበትን ተግባር በሥራ ማዋል ነው፣ ይኽ ለእነሱ መደበኛ ወይም የትርፍ ሠዓት ሥራቸው ነው። የፈጠሩት የሐሰት ዜና ግቡን ሲመታ ልባቸው የደስታ ጮቤ ይረግጣል፣ መንፈሣቸው በእርካታ ይሞላል፣ በእነሱ የሀሰት ወሬ ሌላው ሲጎዳ ጉልበተኛ እና ኃያል መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፣ አንዱን ሥራቸውን በድል አጠናቀው ለነገ የሚያጠፉትን መልካም ሰው ሥም ደግሞ በአጀንዳቸው ማስፈር ይጀምራሉ።

ይኽቺም የናፍቆት ኢትዮጵያ መፅሔት ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች እጅ ሰለባ ለመሆን በተለያየ ወቅት ወድቃለች። የሚያድነን እና ሌላ ተቀባይ ማግኘት ያልቻሉት የምናወጣቸው የፅሑፍ ሥራዎች እና የእነሱ ቅስቀሳ አልጣጣም እያለና ተቀባይ በማጣት ነው።

የናፍቆት ኢትዮጵያ መጽሄት የማንንም ዓላማ የማትደግፍ ወይም የማትነቅፍ፣ ባሕል እና ቋንቋ በባዕዱ ዓለም እንዳይረሳ የበኩሏን ጥረት የምታደርግ እንጂ አንዳንድ ግለሰቦች ለማናፈስ እንደሚፈልጉት ከአንዱ ወገን ቆማ ሌላውን የምታወግዝ መፅሔት አይደለችም፣ ዓላማዋም አይደለም።

በአንድ ወቅት አንዱን የፖለቲካ ድርጅት ካባ ሲያለብሷት፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ የመንግስት ድጋፍ እንዳላት ለማድረግ ብዙ መሠሪ ሙከራዎች ሲደረጉ ይኼው አምስት ዓመት ሞላን። አንዳንዱ ሙከራ ተመሳሳይ ተግባር በሚያከናውኑ እና ተቀናቃኝ የመጣባቸው ከመሠላቸው ክፍሎች ሲመነጭ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለሚፈልጉት ዓላማ የእነሱ ልሣን እንድንሆን የሚቀርብልንን ጥያቄ ስለማንቀበል ሳይሆን አይቀርም። እኛ ማንም ባሕልና ቋንቋ በባዕድ አገር እንድረሳ ተመሳስይ ጥረት ቢያደርግ ከጎኑ ለመቆም ወደኋላ የማንልና ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት በጋራ ጠንካራ የሆነ ተቀባይነት ያለው ሥራ ለመሥራት ምንግዜም ዝግጁ ነን።

በሌላው ላይ ክፋት እና የበላይነት ከማሳየት ይልቅ ተባብሮ መስራትን የመሰለ ውጤታማ እና ስኬታማ ተግባር አይኖርም። ሁሉም በተናጠልም ሆነ በጋራ ከተንኮል የራቀ ተግባር ካከናወነ በሰው አገር ያለውን ወገናችንን በአቅማችን እና በሙያችን ልንጠቅመው እንችላለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top