Free songs
Home / Editorials / Editorial 8: የትውልድ አሳፋሪነት በአባቶች ኩራት ሲሸፈን

Editorial 8: የትውልድ አሳፋሪነት በአባቶች ኩራት ሲሸፈን

Nafqot Editorial

Editorial

የትውልድ አሳፋሪነት በአባቶች ኩራት ሲሸፈን

  ውድ አንባቢዎቻችን ‹‹እንኳን ለኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት በሠላም አደረሳችሁ›› ለአዲሱም የኛ ዘመን አንባቢዎቻችንን ባቅማችን ያገኘነውን ለማካፈል ከዚህም ከዚያም ብለን በተለያዩ አምዶቻችን ያካተትናቸውን ይዘን ብቅ ብለናል፡፡ አንብቦ ከመረዳትና ከማወቅ ይልቅ ማውራት ሳይቀናን አልቀረም ብትሉኝም መልሴ አልተሳሳታችሁም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህቺ ነገ ለምታልፍ ዓለም ባውቅ ባላውቅ ለኔ ምን ይጠቅመኛል፤ ለዛሬ በልቼና የምፈልገውን አድርጌ ካደርኩ የነገው ለኔ ምኔ ነው የምንል በቁጥር እየበዛን የመጣን ይመስለኛል፡፡ አውርተነውና ተርከነው ግዜያዊ እርካታ ከፈጠረልን ለእውነትነቱ ወይም የተዛባ ለመሆኑ ግድም አይሰጠን፡፡

ጥንት አያቶቻችን የፈፀሙትን ጀግንነት እየተረክን እነሱ ለሃገራቸው የሰሩትን መልካም

ሥራና ጀብዱ እኛ የፈጸምነው ይመስል መኩራራትና እነሱን እንደምሳሌ በመጥቀስ ተረት፤ ተረት ማውራት ከጀመርን ዓመታት አስቆጠርን፡፡ አያቶቻችን ለሃገራቸው በሰሩት መልካም ስራ ላይ የጨመርነው ነገር ሳይኖር በጀግንነት ካቆዩት የቀነስነው፤ ካወረሱን ድንቅ ታሪክ የሚያሳፍር ቀለም የቀባነው እየበዛ የመጣ ይመስላል፡፡ ደግሞ እኮ አውርተን ያለማባራታችን እና አለማፈራችን ነው የሚደንቀው፡፡

ከጥንቶቹ አያቶች የጀግንነት ሥራቸውን በሥም እየጠቀስን ‹‹እገሌ የተባለው መሪያችን እንዲህ አድርጎ…ጠላትን አሳፍሮ..፤ እንትና የተባለው ንጉሳችን በጀግንነት ሥራው ዓለም ያደነቀው ነበር›› እያልን በጠረጴዛ ዙሪያና በአደባባይ ከማውራት አልፈን ለሌሎችም ታሪካችንን ለማያውቁ መተረክ ጀምረናል፡፡ በአያቶቻችን መልካም ታሪክ ላይ የጨመርነው አዲስ ነገር የለም፡፡ ድንገት ከእነሱ በኋላ የሰራነው ቢኖር እንኳን አምርቶ ከመብላት ወደ መለመን፤ ከመከባበር ወደመናናቅ፤ ከአንድነት ወደ መከፋፈል፤ ከልበሙሉነት ወደ ወደ አቅመቢስነት በሠላም ተሸጋግረናል፡፡ ሌሎች አገሮች በተፈጠሩና ሕልውና ባገኙ በአጭር ዓመታት ራሳቸውን ችለው ለሌላ መትረፍ ጀምረው አዲስ ታሪክም መስራትና ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ያሉ ይመስላል፡፡

የኛ ነገር ደግሞ የጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ ባሉበት መቆምም እኮ ጥንካሬ ነው፡፡ ወደፊት መራመድ ቢያቅት የነበረውን ይዞና ካለሁበት አልነቃነቅም ማለት ቢገፋ የማይወድቅ የጠንካራ ሰው አቋም ይመስለኛል፡፡ የኛ ነገር ባለህበት ሂድ እንኳን በዝቶበት ወደኋላ መጓዝና እንደካሮት ቁልቁል ማደግ በሕግና በእርግማን የተሰጠን ሽልማት እየሆነ መጥቷል፡፡ የአንድ ሰው የዓመት ገቢ በአማካይ $227 ዶላር በሆነበትና ከ80 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለሚኖርበት አገር እንዲሁም ከ66% በላይ ሥራ ፈት በበዛበት አገር ሁሉም ሰው በልቶ ማደር አለበት ከተባለ በ3 ቀን አንድ ግዜ መብላቱም ያጠራጥራል፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት ጠግበን እናድር ነበር፤ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ስለረሃብና ስደት ብዙም እውቅና አልነበረንም፤ ከሰላሳ ዓመታት በፊት የልመና ከረጢት ይዞ መውጣትና ከሀገር እየኮበለሉ መሰደድና መሸሽ ተማርን፡፡ የዛሬ ሃያ አመት ገደማ መበታተንና የሰው ልጅ የመጀመሪያው የዚች ዓለም ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጠውን ሕግ ጥሰን በዘር ሃረጋችን መደራጀት ጀመርን፡፡

አሁንም ጉዳቱን አውቀን ከስህተታችን አልተማርንም፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ዓይነት፡፡ የእርዳታ እህል ልመናውም በሕይወት ቀጥል መድኃኒትነቱ የወደድነው ይመስላል፡፡ ጭራሽ እርዳታ መለመንን መብት ከማድረጋችን አልፎ እርዳታው በወቅቱ ካልመጣልን በህግ ለመክሰስና ረጂዎቻችንን ለመወንጀል ወደኋላ አንልም፤ መብታችን አርገነዋልና፡፡ ረጂዎቻችንም መብታችንን እረግጠዋልና፡፡

የግዜው ፋሺን ሆኖ በሃገራችን በአሁኑ ግዜ ከተቋቋሙ ድርጅቶች በአብዛኛው ‹‹አትራፊና የመንግሥት ያልሆኑ›› የሚል ሕጋዊ ሥም የያዙ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እንደአሸን ፈልተዋል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ለሚሰደደው ዜጋ ተቀባይ ያፈላልጋሉ፤ ለተራበው ያበላሉ፤ ወላጅ የሌላቸውን ሕጻናት ይሰበስባሉ፤ በረንዳ አዳሪዎችን መጠለያ ይሰጣሉ፡፡ በጣም እጅግ በጣም ድንቅ በአገልግሎት ነው፡፡ በምድር የሚያስመሰግን በሰማይ የሚያጸድቅ ሥራ፡፡ ግን ይህ እርዳታ ለምን ያህል ግዜ የሚቆይ ነው?…..ባለፈው አያያዛችን ዘለዓለማዊ ይመስላል፡፡

የ1966ቱ ድርቅ ባመጣው ግዜያዊ እርዳታ ሳቢያ ዛሬ ግዙፉ የሃገራችን ተቋማት ‹‹እርዳታ…እርዳታ…እርዳታ…›› በሚል ሽፋን በሰፋፊ ቢሮና በጮሌ የሃገር ውስጥና የውጭ ሠራተኞች የተሞሉ ናቸው፡፡ በየትኛውም ሃገር ግዜያዊ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ይደርሳል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ሱናሚ፤ የጎርፍ መጥለቅለቅ፤ የእሳተ ጎሞራና የመሳሰሉት ሲፈጠሩ የሃገሩ መንግሥት ካልቻለ እጁን ወደ ሌሎች የበለጸጉ አገሮች መዘርጋቱ አይቀርም፡፡ እርዳታው ግን ግዜያዊ ሲሆን ኅብረተሰቡ አቅሙን አጠናክሮ ለችግሩ የደረሱለትን በማመስገን ወደአምራችነቱ ይመለሳል እንጂ ቋሚ ለማኝ አይሆንም፡፡ የኛ ግን ሥር ነቀል ልመና መሰለኝ፡፡

ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ለመሆኑ ሶስት ሶስት የሆኑ የአሜሪካና የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ከመቃብራቸው ቢነሱ ምን የሚሉ ይመስለናል? እንደምሳሌ አድርገን ከኢትዮጵያ የቅርቦቹንና የምናቃቸውን አፄ ቴዎድሮስ፤ አፄ ዮሐንስ፤ አፄ ምኒልክ ከአሜሪካ ደግሞ ቶማስ ጃፈርሰን፤ ጆርጅ ዋሺንግተን እና አብርሃም ሊንከን ለአንድ ቀን የልጆቻቸውን ሥራ ለመታዘብ ከመቃብር ቢነሱ ምን የሚሉ ይመስላችኋል፡፡

አሽሙረኛ ብትሉኝም ባትሉኝም መቼም ግድ የለኝ፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የኛዎቹ የቀድሞ መሪዎች ልጆቻቸው በሰሩት ደካማ ተግባር የሚኮሩ ሲመስለኝ የአሜሪካን የቀድሞ አባቶች ደግሞ በልጆቻቸው ሰርቶና ደክሞ ማደግ የሚበሳጩ ይመስለኛል፡፡  ምን ዓይነት ግምት ነው ልክ አይደለህም ልትሉኝ ትችሉ ይሆናል፡፡ ለዚህ የምለው ስላለኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ እኔ የማስበው እንደራሳችን እና እስካሁን እየሄድንበት ባለነው መስመር ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ አስተሳሰብ ‹‹ሥራ የሞኝ ነው፤ የሃገር ህዝብ በልቶ ከጠገበ በመሪዎቹ ላይ ያምጻል፤ ዲሞክራሲና ነፃነት ለእኛ ሕዝብ የማይታኘክ ድንጋይ ነው›› የሚል አስተሳሰብ ስላለኝ ነው፡፡

የአሜሪካኖቹ የቀድሞ አባቶች ደግሞ ልጆቻቸውን አለእንቅልፍ ይህን አገር ካሰቡት በላይ በማሳደጋቸው ቅር የሚሰኙ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ምነው ልጆች አለእረፍት ይህን ያህል ድካም ተገቢ ስላልሆነ ቅጣት ይገባችኋል›› የሚሉ ይመስለኛል፡፡

እንዲያው ለሁሉም የቀድሞ አያቶቻችንን ሥራ እንደ ተረት ባንተርከውና የኛ ስራ እያደረግን ባናቀርበው ይሻላል፡፡ እነሱ በራሳቸው ግዜ መልካም ሰርተው አልፈዋል፤ እኛም እየሰራን ባለነው ውርደት ወይ ማስተካከል ወይም መኩራት፡፡ አሊያ ግን እነሱ በተኮሱት ጥይት እኛ ስንገድል እነሱ በገደሉት ጠላት ሬሳ ላይ እኛ ቆመን ስንፎክር ትዝብት ላይ እንወድቃለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top