Free songs
Home / Editorials / Editorial 17: ሳይላክ የቀረ ቃልኪዳን

Editorial 17: ሳይላክ የቀረ ቃልኪዳን

Nafqot Editorial

Editorial

አሮጌው በአዲስ ዓመት ሊተካ ቀናት ሲቀሩት ወይም በዋዜማው በሕይወታችሁ ልታሻሽሉት ወይም ጭራሽ አውልቃችሁ ልትጥሉት የምትፈልጉትን መጥፎ ባሕሪይ ወይም ልምድ አስባችሁ ታውቃላችሁ?በእርግጥ ፈጽማችሁታል ወይስ በአዲሱ ዓመት ማግስት ለሚቀጥለው ዓመት አስተላልፋችሁታል?

· ይኼን የተጠናወተኝን የሲጋራ ዓመል በዚህ ዓመት ለመጨረሻ ጊዜ መሰናበት አለብኝ፣ ሁለተኛ ንክች አላደርግም፣

  • በሚመጣው ዓመት ይኼን ማታ ማታ እያመሸሁ ወደ ቤት ስገባ የማስቀይማቸውን ቤተሰቦቼን ለመካስ ከሥራ እንደወጣሁ ወደቤቴ ለመግባት ቃል እገባለሁ፣
  • አለአግባብ በግብዣ የምበትነውን ገንዘብ ቆጥቤ ቁም ነገር ለመሥራት የምችልበት ወቅት አሁን ነውና በመጪው አዲስ ዓመት ገንዘብ ቆጣቢ ለመሆን ወስኛለሁ፣
  • ይኼን ቦርጬን በስፖርት ለማጥፋትና ሸንቃጣ ለመሆን ስፖርት ክበብ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ እመዘገባለሁ፣
  • ከብቸኛነት ኑሮ ወጥቼ ትዳር የምመሰርትበት ዓመት አዲሱ ዓመት መሆን አለበት፣
  • ያቺን ነገረኛና ነዝንዛ ፍቅረኛዬን እኔን ከመግደሏ በፊት  የሠላም የምለይበት ዘመን እንዲሆን ወስኛለሁ፣
  • በየሣምንቱ ቅዳሜ እና እሑድ ከሰካራም ጓደኞቼ ጋር የማጠፋውን ጊዜዬን ከልጆቼ ጋር ለማሳለፍ በአዲሱ ዓመት ቁርጠኛ ሆኛለሁ፣
  • ባሌን በረባው ባልረባው ከምነዘንዘው ይልቅ በፍቅር ዓይን እንዳየውና ሁሉንም በውይይት ለመፍታትና ልጆቻችንን ከመሳቀቅ ማውጣት ያለኝ እድል በአዲሱ ዓመት ጠባዬን መቀየር ነው።
  • ያቋረጥኩትን ትምህርት በአዲሱ ዓመት እጀምራለሁ፣

በአዲስ ዓመት ልንቀይር የምንፈልገው አዲስ እና የተሻሻለ የሕይወት በመስመር ተዘርዝሮ አያልቅም፣ እንደ ግለሰቡ ወይም እንደ ቤተሰቡ ፍላጎት ይለያያል።

ዓመት በተቀየረ ቁጥር እኛም ሕይታችንን ወደተሻለ ለመቀየር  የማንገባው የቃል ኪዳን ብዛት የለም። በተለያዩ መስኮች ወንዶችም ሴቶችም ደካማ ባሕሪያቸውን ለመቀየርና ለተሻለ ሕይወት ራሳቸውን ለማዘጋጀት ቃል የሚገቡበት ጊዜ በአብዛኛው አዲሱ ዓመት ነው።

ግን ደካማ ጠባይን ወይም ልምድን ለማቆም ወይም በተሻለ ለመቀየር ለምን አዲስ ዓመት ብቻ ይጠበቃል? ወይም ይመረጣል? ለሕይወታችን የማይጠቅም እስከሆነ ድረስ ለምን በአመቱ አጋማሽ ወይም እንደአስፈላጊነቱ ወዲያው እርምጃ አንወስድም?

አዲስ ዓመት ምንጊዜም አዲስ ነገር የመፈለግ እና ምኞትን ለማሟላት የመጀመሪያ እርምጃ አድርገን መውሰዱ ከፈረንጁ ባሕል ጋር የተያያዘና የተገኘ ልምድ አድርገን የምናስብ እንኖራለን። አይደለም። ከኛ በፊት የነበሩ ኢትዮጵያዊ አባቶቻችን በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ለመሰነቅ አዲስ ቃል የሚገቡበት እንደነበረ ከግል የቤተሰብ አንጋፋዎች አንደበት ሳንሰማ አንቀርም። የሀገር መሪዎች ለወንጀለኛ እስረኞች ምህረት የሚሰጡበት፣ የሀገራቸውን ዓመታዊ ዕቅድ የሚያሳውቁበትና ለተግባራዊነቱም መልካም ምኞታቸውን የሚገልፁበት ወቅት አዲሱ ዓመት ነው።

የአዲስ ዓመት ምልካም ምኞትና ውሳኔ ነገር ከተነሳ አፈፃፀሙ ላይ ምን ያህል ጠንካራ ነን?

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ለአዲሱ ዓመት መግቢያ ዋዜማ ሕይታቸውን ወደ ቀናው ጎዳና ለማሸጋገር ቃል የሚገቡና ከአጉል ልማዶች ራሳቸውን ለማስወገድ መሃላቸውን ከሚፈጽሙት ውስጥ በተግባር የሚተረጉሙት ከመቶው ሃያአምስት እጁ ብቻ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ቃልኪዳናቸውን ለጥቂት ጊዜ ጠብቀው እንደገና ወደነባሩ ባሕሪያቸው የሚሚለሱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

አንድ በግል የማውቀውን ምሳሌ ልጥቀስ፦

ለረዥም ዓመታት በቅርብ የማውቀው ወዳጄ በሱስ የተጠመደበትን የሲጋራ ዓመል እርግፍ አድርጎ ለመተው ባለፈው ዓመት ዋዜማ ቃል ይገባል። ይኽንን የሰማን ወዳጆቹም ውሳኔውን በማድነቅ መልካም ተመኘንለት። በእርግጥም ሲጋራ በአፉ ሳይዞር ቀናቶች እና ወራቶች ተቆጠሩ። በአንድ እሑድ በአንድ አጋጣሚ ዘወትር ከምንገናኝበት ቦታ ራቅ ያለ የገበያ ቦታ እንገናኛለን፣ በእጁ የተለኮሰ ሲጋራ ሲይዝ ከአፉም የተጥመለመለ ጥቁር ጭስ ይወጣል። የተገናኘነው ድንገት ስለነበረና ሰርቆ እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ ሰው መደናገጥ ይታይበታል።

«አንተ ምነው ደህና የተውከውን ተመለስክበት ወይ?» የሚል ጥያቄ ባቀርብለት፣ የመለሰልኝ መልስ ግን በእጅጉ አሳቀኝ። መልሱን ሳስበው እስካሁን ያስቀኛል።

«እባክህ ኪሴ ውስጥ የተረሳ ሲጋራ አግኝቼ ከምጥለው ብዬ ነው» የሚል መልስ ነበር።

ከልጆቼ ጋር በየሣምንቱ መልካም ጊዜ አሳልፋለሁ ያለው ባለ ቃል ኪዳን የልጆቹ ሥም እስኪረሳው ድረስ ውጭ በማምሸት ቃሉን ካልጠበቀ፣ ያቋረጥኩትን ትምህርት እጀምራለሁ ያለውን መሃላ በልቶ እንኳን ትምህርት ቤት ቀርቶ የመጽሐፍ ገጽ መግለጽ ካቃተው፣ አለአግባብ የምበትነውን ገንዘብ ቆጥቤ ለራሴና ለቤተሰቤ ቁምነገር እሰራለሁ ብሎ ቃል የገባበትን ቀን ረስቶ የመሸታ ቤት ግብር ከፋይነቱን ከቀጠለ፣ ባሌን ሁለተኛ በረባው ባልረባው አልነዘንዘውም ያለችው ሴት ቃሏን አጥፋ የገባችው ቃል ሳይደርቅ እጥፍ ምላስ ካወጣች፣ የብቸኝነት ኑሮዬ ማብቂያው ዓመት ይኽ መሆን አለበት ብሎ የዛተው ላጤ ጉብል «የምን ትዳር ነው ደግሞ ላጤነቴ ጥሞኛል» ካለ፣ ያቺን ነዝናዛ ፍቅረኛ ተብዬን በሠላም የምገላገልበት ዘመን መጪው ዓመት ነው ብሎ የፎከረው ሰው ከዛችው ነዝናዛ ካላት ሴት ጋር ተጣብቆ ጨጓራው የሚላጥ ከሆነ የቃል ኪዳን እና የአዲስ ዓመት ውሳኔ ትርጉሙ ምን ሊሆን ነው?

ለመሆኑ በአዲሱ 2013 ዓመት ሕይወታችንን ወደተሻለ ለመቀየር ውሳኔ አድርገናል? ለራሳችንስ ቃል ገብተናል? ይኽንንስ ቃልኪዳን ለመጠበቅና በጽናት ለመቆም ዋስትናችን ምንድነው? ወይስ እንደወዳጄ ሲጋራ እኛም የረሳነው ሽፍጠት ኪሳችን ውስጥ ቀርቷል?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top