Free songs
Home / Editorials / Editorial 16: ሙሴ ያጣች አገር

Editorial 16: ሙሴ ያጣች አገር

Nafqot Editorial

Editorial

እስራኤላውያን እምነታቸው ቆሸሸ። ፍቅራቸው ቀዘቀዘ። አንድነታቸው በእጅጉ ላላ። በፀሎት አምላኩን ከሚማፀነው ይልቅ በጣኦት የሚያምነውና፣ ራሴ ጣኦት ነኝ የሚለው የእስራኤልን ምድር አጥለቀለቃት። ሁሉም የእስራኤል አለቃ መሆን ቃጣው። ቀረጥ ቀራጩ፣ አሥራት ሰብሳቢው የእምነት ቦታዎችን በቡድን ተከፋፈላት፣ በየምንጩ እና በየኩሬው ውሃ ለመቅዳት የሚመጡ እናቶችና እህቶች ተደፈሩ። ትዳር ተበተነ፣ ኅብረት ፈረሰ። በሃገሪቱ ጩኽት በረከተ፣ ሕፃናት አለቀሱ፣ አዛውንቶች ከሕፃናት ለቅሶ እና ከእናቶች ጩኽት ይልቅ በዓለማዊው ሕይወታቸው በረቱ። በወቅቱ ፈጣሪ የተቆጣ መሆኑን ያወቀ ግን አልነበረም። ቁጣውን በተግሳፅ ያስከተለው አምላክ በእስራኤላውያን በእጅጉ አዘነ። የኃዘኑንም ተከትሎ ቁጣውን በቅጣት ፈፀመው።

የእስራኤላውያንን ስህተት እና የፈጣሪን ቁጣ ተከትሎ አንድ ሰው አምርሮ ወደ አምላኩ ጮኽ፤ ፈጣሪ ምሕረቱን እንዲያወርድ፣ ቅጣቱን እንዲያቀል በፀሎት ተማፀነ። ራሱን ከሕዝብ ለይቶ ወደ ተራራ ወጥቶም ፀለየ። ፈጣሪውን ለረሳው የእስራኤል ሕዝብ ተንበርክኮ ምሕረት ጠየቀ። ሕግና ደንብን አውርድልን ሲል አጥብቆ ፈጣሪውን ለመነ። መሐሪው አምላክም ለሙሴ በእሳት የፃፈውን ሕግ አወረደለት። ለዳግም ጥፋት እሣትን መቅጫው እንደሚያደርግም በምሳሌ ነገረው።

የተሟላ የኃይማኖታዊ ትንተና ገፅታ ይኖረዋል ባልልም፣ ይኽን ምሳሌ ያለምክንያት አላነሳሁትም። ዛሬ ለምለው በር ከፋች ይሆናል ብዬ ስላሰብኩም ነው። በአማካይ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በየግዜው አበክሮ የሚያነሳው ጥያቄ ይኖራል ብዬ ስለገመትኩም ይመስለኛል። እስቲ ከሃገራችን ልጀምር።

ኢትዮጵያ የምትባለው ዛሬ በቆዳ ስፋት መጠኗ  ተመናመና፣ የሕዝቧ ቁጥር በእጥፍ እና በፍጥነት እየጨመረ የሚገኝባት ሃገር በትክክል መቼ ሃገር እንደሆነች እና ስፋቷም ምን ያክል እንደነበር በትክክል በመረጃ የተደገፈ እና የተሟላ ታሪክ ባይቀርብም በመጽሕፍ ቅዱስ ላይ በሠፈረው መረጃ መሠረት የረዥም ዘመን ታሪክ እና ቀደምት ከሆኑ ጥቂት ሃገሮች እንዷ እንደሆነች፣ እንኳን ወዳጆቿ ቀርቶ ጠላቶቿም ቢሆኑ የማይክዱት ነው። አንዱ በአፈ ታሪክ የሰማውን ወይም ከጥንታዊ የታሪክ መፃሕፍት አግኝቼዋለሁ የሚለውን፣ የቆዳ ስፋቷን ከማዳጋስካር እስከ የመን ያደርጋታል፣ ሌላው ደግሞ ግብፅን የጨመረ እና የአፍሪካን አጠቃላይ መልክአምድር የጠቀለለ ስፋት ይሰጣታል። ገዢዎቿንም በወቅቱ በዓለም የገነኑ፣ በጦርነት ሁሉንም የሚረቱ፣ በጦርነት ወቅት ተዋጊ በሠላም ጊዜ ደግሞ ተባብረውና ተከባብረው የሚኖሩ ሕዝቦች ያደርጓታል። ይኽን እሺ ብለን ብንቀበለውም «ያ እኛነታችንን ምን ነጠቀን» ብለን መጠየቃችን አይቀርም።

ትላንት እንዲህ ዓይነት ሕዝቦች ከነበርን፣ ባሕልና ማንነት ከውርስ የሚገኝ ነውና ያንን መልካም እኛነታችንን ያሳጣን ምንድነው? ብለን ብንጠይቅም በ«እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ በላዩ ላይ ተጨማሪ ስህተት ከመደመራችን ባሻገር ልናሻሽለው የጣርንበት አንዳችም ትላንታዊ እኛነታችን በዚህ ዘመን አልታየም።

የዛሬዋ ዓለማችን የዱሮዋ እደለችም። ሁሉም ነገር ከነፋስ በፈጠነ መልኩ በየቀኑ እና በየሰዓቱ ይቀያየራል። የሥልጣኔን ገፅታ የሚያሳዩ ሰው ሰራሽ ምርቶች ለማመን በሚያስቸግር መልኩ ዓለምን በየሴኮንዱ ያጥለቀልቋታል።  በባሕር ውስጥ የሚሰምጡ በየብስ ላይ የሚምዘገዘጉ፣ በሕዋ ላይ ተንሳፈው የዓለምን እንቅስቃሴ ለፈለሰፏቸው ሃገሮች የሚያሳብቁ ቴክኖሎጂዎች በፉክክር ይመረታሉ። አንዱ ሌላውን ለማጥፋትና ከነገው ጥፋት ራሱን ለመጠበቅ የጎረሱትን ሳይውጡ ሕይወትን የሚሰልቡ የጥፋት መሣሪያዎች ይፈለሰፋሉ፣ ከእነሱ የተሻሻሉትንም ፈጥሮ የዓለም ኅብረተሰብ የበላይ ለመሆን የሚጥሩ አገሮች ቁጥራቸው ቀላል እደለም።

አንዱ አገር የራሱን ሕዝብ አጥግቦ ሌላውን ይደጉማል፣ ለተቸገረ አገር በአራጣ ያበድራል ወይም ላበደረው ምሕረትን ያወርዳል። «የምነግርህን ከፈፀምክ ደግሞ ሌላም ይጨመርልሃል» የሚሉም አልጠፉም። እና ዓለም ጦዛለች፣ የመቅለጥ ኃይሏ በርትቷል። ትላንት ያለው ዛሬ አይኖርም። የሰለጠነው ዓለም ስለ ዘር እና ጎሳ፣ ስለ ነገድና ኃይማኖት በክርክር ጊዜውን አያጠፋም። «መሆን ያማረህን ምረጥ» ይለሃል። ለሠለጠኑት የሚታያቸው ሌላ ነው። ጠግቦ መብላት፣ ለሁሉም ሥራ መፍጠር፣ ሠርተው ሲደክሙ በሠላም ጡረተኛ መሆን፣ ልጆቻቸውን በመለልክም ሁኔታ አሳድጎ ለቁም ነገር ማብቃት፣ ሃገራቸውንም እድገትን ማውረስ። ይኼ ነው የዘመኑ ሩጫ።

ፊታችንን ስናዞር ደግሞ ለማደግ የማይፈልገውን፣ በጎሳና በኃይማኖት ልዩነት የተተበተበውን፣ የኔ እንጂ ያንተ ዘር አይረባም የሚለውን እናያለን። አንደኛው የዛሬ  አንድ ሺህ ዓመት የለበሰውን ገና አላወለቀም። አጥቦ ይለብሰዋል። እናቶችና ሕፃናትን ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ፀጉራችሁ ካልተሸፋፈናችሁ ኃይማኖታችሁን አታከብሩም እያለ ያስፈራራቸዋል። አንዱ ኃይማኖቱ ከተተቸ አንድ ራሱን ከመቶ ጠላቶቹ ጋር ይዞ ለመሞት ዝግጁ ነው። ምነው ቢሉ ከውይይት ይልቅ ጥፋትን እንደመፍትሄ መቁጠሩ ገነትን ያወርሳልና።

እንግዲህ እኛ ኢትዮጵውያን በዚህች የዓለም አባዜ እሽክርክሪት መሐል የቆምንና ልንከተለው የሚገባንን ጎዳና መለየት ባልቻልን ሕዝቦች እንመሰላለን። አንዳችን ትላንት ለከፋፈለን እና በዘር ላደራጀን እንባችንን እንደውሃ ስንረጭ፣ ሌሎቻችን ደግሞ ሕዝብ እንባ ባፈሰሰለት ሰው ሞት እስክስታ ሲወርድ እናያለን። አንዱ ዓለም ጊዜውን ጠብቆ የሚመቸውን መሪ ለመምረጥ ታች እና ላይ ሲል እኛ ደግሞ እንደ ቀድሞ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ሥልጣን ከእኛ አይወጣም መፍትሄው «መተካካት» ነው  ብለናል። ንጉሥ ሲሞት ለልጁ፣ ልጅ ሲሞት ለሟች ልጅ እንደምናወርሰው ሰርወ መንግሥት ማለት ነው።

ይኼ ሁሉ ተዳምሮ እንደ ጥንታዊ እስራኤላውያን መቅበዝበዛችንን የሚታዘበው ፈጣሪ መዓት ያመጣብን ይሆን?  ወይስ አሁን ያለንበት፣ ያለመተባበር፣ መከፋፈልና አንድነት ማጣት ራሱ ቅጣት ይሆን? ቅጣቱ ከቀጠለ ራሱን አግልሎ፣ መንፈሱን ሰብሮ ለሀገር በፀሎት የሚበረታ ሙሴ እናገኝ ይሆን? ወይስ በውስጥ እና በውጭ ያሉት ሙሴዎቻችን የሚመክሩበት ልብ ይሰጣቸው ይሆን? ለሁሉም ሃገራችን ሙሴ ትፈልጋለች።  ወይስ ሙሴዎቻችንን ከኋይት ሀውስ በር ላይ እንጠብቃለን?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top