Free songs
Home / Editorials / Editorial 15: በምን እንጣላ?

Editorial 15: በምን እንጣላ?

Nafqot Editorial

Editorial

የሰው ልጅ ተፈጥሮ እንደግል ባህሪዩ ይለያያል። እንደ ሰውኛው አስተሳሰብ ነገሮችን አገላብጠን ማየት ከቻልን፣ የሰው ልጅ ከውልደት ጀምሮ እስከ እድገት እና እርጅና በራሱ የሚያከውነው ወይም የሚያሳየው ባሕሪያት በራሱ ሥነ-ልቡና ዘሪያ የሚያጠንጥን ሆኖ የሌላውን ስሜት ላለመጉዳት የሚያሳየው ቅንነት ግን ሚዛን ላይ የወጣ አይሆንም። ለምን ቢሉ ሁሉም እንደ ዓይነቱና እንደ ባሕሪዩ ለሌላው ክብር የመስጠት ሚዛኑ ወደ አንድ ወገን ያደላ ሊሆን ይችላልና ነው። ሚዛኑም የራሱ እንጂ ሌሎችን ሊለካበት በሚገባው ሚዛን ላይ ራሱን ማስቀመጥ እንደስስት ስለሚቆጥረው ይሆናል።

የሰው ልጅ ተፈጥሮ በራሱ ወደ ግለኛነት በሚያደላ ንፍገት የተሞላበት በመሆኑም ይመስላል ከሌላው ጋር የተቀራረበ ሃሳብ ላይ ለመድረስ እና የጋራ አቋም ከመያዝ ይልቅ ለመራራቅ እና ለማፈንገጥ የሚቸኩለው።

የሰውን ልጅ በየዘመናቱ እየለየን መመልከት ብንችል እንኳን የሰው ልጅ በሂደት ከዘመኑ ጋር ምን ያህል የባህሪይ ለውጥ እንዳሳየ ማየት እንችላለን። ለምሳሌ በዓመተ ዓለም የነበረው ሰው በዓመተ ምሕረት ከነበረው ሰው የባሕሪይ ለውጥ አሳይቷል። በ15ኛው ክፍለ ዘመን ወይም ከዛሬ አስር ዓመት በፊት የነበረው ሰው በያዝነው ዘመን ትልቅ የባሕርይ ለውጥ ሲያሳይ ካለፈው ሰው ጋር ያለው የባሕሪይ ለውጥ ክፍተት በሚዛን የሚለካ ከመሆንም ይከብዳል ወይም ሚዛን የማናገኝለት ትልቅ የባሕሪይ ለውጥ እንደሆነ ለመገመት እንችላለን። ይኽም የመነጨው ከዘመኑ ጋር ራሱን አመሳስሎና በሩጫው ቀዳሚ ወይም ከፊት መሪዎቹ ጋር እኩል ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።

ይኽንን የሰው ልጅ የየዘመናቱን የባሕሪይ ለውጥ ለማጥናት ሰፊ ዘመቻ ያደረጉ የሥነ-ልቡና ሊቃውንት እንደየድርሻቸው የተለያየ መላምት ወይም ግኝት ይኑራቸው እንጂ የሚያስማማቸው አንድ ነገር አለ። በተፈጥሮ የሰው ልጅ ለራሱ ከማድላት ጋር በተያያዘ የራስ ወዳድነት ባህሪይ።

እንግዲህ ይኽ የራስ ወዳድነት ባሕሪይ ቀስ በቀስ ዕድገት በማሳየት ከየስልተ ምርቱ ጋር ለጠብ አጫሪነትም ምክንያት እንደሚሆን በተለያዩ ግዜያት ከቤተሰብ እስከ ኅብረተሰብ አልፎም በሕዝብና ከጎረቤት አገሮች ጋር የተፈጠሩ አለመግባባትና መካረሮች እንዲሁም

ጦርነቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ይኽንን ከላይ ለመግቢያዬ ያኽል ያነሳሁትን የሰው ልጆች ባሕሪይና በየስልተ ምርቱ እና በሂደት የሚያሳየውን ለውጥ ለማሳየት የፈለኩት ወደ ዋናው ጉዳዬ እንዲወስደኝ ለመንደርደሪያ ያኽል ለመጠቀም ፈልጌ እንጂ ማንሳት የፈለኩት ጉዳዬ ሌላ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ለምን እርስ በእርስ በመከባበር፣ በመረዳዳት፣ ተፈላልጎ በመገናኘት፣ በሃገራችን ታሪክ በመኩራት የምንታወቀውን ያኽል ለምን የሚያለያየንን ጉድጓድ እንቆፍራለን? በተለይ ወደንም ሆነን ተገደን ከሃገራችን ምድር የተለየን፣ ቤተሰባችንን ወደኋላ ጥለን በሰው ሀገር የምንንኖር የአንድ አፈር ልጆች ለመጣላት ለምን ምክንያት እንፈልጋለን?

በእርግጥም የስደታችን መንስኤዎች እንደየግለሰቡ የተለያየ ቢሆንም፣ የአንድ አገር ልጆች በባዕዱ ዓለም ሲገናኙ የሚያግባባቸው አንድ ባሕል፣ አንድ ቋንቋ እና ተመሳሳይ መሰረታዊ አንድነቶች ጎልተው መታየት ሲኖርባቸው፣ በእኛ ላይ ብቻ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ለምን የተካረረ ይሆናል?

በተቃውሞ ሠልፋችን ተለያይተን፣ በድጋፍ ሠልፋችን ተለያይተን፣ በሠርጋችን ተመራርጠን፣ በሞታችን ጎራ ለይተን፤ በስብሰባችን ቡድን መርጠን፣ በሃገራችን ጉዳይ ላይ ተከፋፍለን፣ በፖለቲካ አቋም ላይ ዘጠና ዘጠኝ ሆነን።  በየትኛው ላይ እንስማማ?

አንዱ የቋጠረውን ሌላው ለመፍታት ከሮጠ፣ አንደኛው ቡድን ይጠቅማል ብሎ የሰራውን ተቃዋሚው የጠላት ሴራ አድርጎ ከቆጠረው፣ አንዱ በባዕድ ዓለም ነግዶ ካተረፈ ዘርፎ ነው ተብሎ በራሱ ወገን ከታማ፣ በባዕዱ ዓለም የቁጥራችን መብዛት ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው?

ምድረ አሜሪካ በስደኞች የተገነባች አገር ነች። ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ስደተኞች ሠርተው እና ደክመውባት ሰው ሆነውባታል። ብዙዎቹ የተሰደዱበትን ዋና ዓላማ አሳክተዋል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሁሉም በሃገራቸው ቢሆን እየተመኙ ልባቸው ሃገራቸው፣ ሥጋቸው ደግሞ እዚሁ ነው። ማን እንደ ሀገር የሚሉ ይመስላሉ። ግን ሁሉም አንድ ታላቅ ተግባር አከናውነዋል። ፍቅር እና መቀራረብ።

ስደት በእኛ ላይ ያስገኘውን እና ያሳጣንን ለውጥ ለይተን የተመለከትን አንመስልም።

የባዕዱ ዓለም በሃገራችን ከነበረን ኑሮ የብዙዎቻችንን ሕይወት ወደተሻለ የለወጠ ቢመስልም በፍቅርና በመቀራረብ ላይ የምናሳየው ለውጥ እና የወገን አንድነት ግን ከየትኛውም የስደተኛ ባሕርይ የሚገጥም አልሆነም።

ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያውያን የስደተኖች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። ፍቅራችን ግን ከእጥፍ በላይ ቀንሷል። ተነጋግረን አንደማማጥም፣ ስብሰባችን ያለ እልባት ይበተናል፤ ትዳራችን በዘር ልዩነት ይፈርሳል።

በራሳችን የምንወስነው እያለን ሌሎች የሚነግሩንን እንድናደርግ እንገፋፋለን፣ አንዱ የሰራው መልካም ነገር ለሌላው ነውር ነው፣ ሐሜት እና ከኋላ የሚደረገው መጎሻሸም አንዱን ቡድን ይጎዳል፣ መፈራራትና አለመተማመን በእጅጉ ያየሉበት ወቅት አሁን ነው።  ቀኙም ግራውም ያስወቅሳሉ።

አባት የአስራ ሁለት ዓመት ልጁን አስከትሎ በበቅሎ ወደ ገበያ ይጓዛል። በጉዞአቸው ላይ በቅሎው ላይ የተቀመጠው አባትዬው ሆኖ ልጁ ከጎኑ በእግሩ ይጓዛል። ጥቂት እንደተጓዙ የአካባቢው ሰው ሠላምታ እየሰጣቸው ሳለ በቡድን በእግራቸው ወደ ገበያው ከሚጓዙት ውስጥ ሃሜት ይጀምራሉ።

«አሁን ሕፃን ልጅ በእግሩ አስከትሎ እንዴት ይሄዳል? ነውር አይደለም እንዴ?» ይላሉ። ይኽን ሲናገሩ ጆሮው የገባው አባትም ከበቅሎው ላይ ወርዶ ልጁ በበቅሎው ላይ አስቀምጦ እሱ በእግሩ ይከተላል።

አሁንም ጥቂት እንደሄዱ ሌላው ወደ ገበያ የሚሄድ ቡድን ያያቸውና «አሁን አዛውንትን በእግር እያደከመ ወጣቱ በበቅሎው ከሚሄድ ምናለ አባቱን በቅሎ ላይ አስቀምጦ እሱ በእግሩ ቢሄድ? አይ አባት የማይከበርበት ዘመን!» እያሉ ሲናገሩ አባትና ልጅ ይሰሙና፦ ሁለቱም በቅሎው ላይ ተፈናጠው በመውጣት መጓዝ እንደጀመሩ የተመለከታቸው እግረኛ «ተመልከቱ እነዚህ ግፈኞች ይህን ምስኪን እንስሳ ለሁለት ተቀምጠው ሲገድሉት፣ ምናለ አንደኛው እንኳን ቢወርድለት?» ሲሉ ይሰሙና ከሁሉም አፍና ሐሜት ለመዳን ከበቅሎው ወርደው እየተከተሉ በእግራቸው መጓዝ ይጀምራሉ።

አሁንም ጥቂት እንደተጓዙ ያያቸው እግረኛ ገበያተኛ «ይሄን የመሰለ ወደል በቅሎ እየተከተሉ ከሚሄዱ ተቀምጠውበት አይሄዱም፣ የማናቸው ደደቦች» ማለት ይጀምራል።

ምን ቢታደርጉ ይሻል ነበር? በተራ በቅሎ ላይ ተቀምጦ መጓዙ፣ ለሁለት ተቀምጦ መጓዙ፣ ወይስ በቅሎውን እየጎተቱ በእግር መሄድ? ሁሉም አስወቃሽና የሚያጣላ ነው። የትኛው ያስማማን?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top