Free songs
Home / Editorials / Editorial 14: ሕሊና እና ጥቅም የተጣሉ ለታ

Editorial 14: ሕሊና እና ጥቅም የተጣሉ ለታ

Nafqot Editorial

Editorial

ጊዜው የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ አስቆጥሯል። ከአንድ ሰላሳ ዓመት በላይ ሳያልፈው ቀረ ብላችሁ ነው? ግዜው እንዴት ይሮጣል እባካችሁ!

የርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ መስመር  ልዩነት ያጣላቸው አብሮ አደጎቼ ብዙዎቹ ወደማይመለሱበት ዓለም ሄደዋል። የዛን ጊዜ የአመለካከት ልዩነት እና የፍፁም ነፃነት ጥያቄ ነበር ግማሾቹን ሜዳ አውጥቶ ለዓላማቸው እንዲታገሉ የገፋፋቸው። ከፊሎቹ ደግሞ ከተማ ውስጥ የፖለቲካ ድርጅታቸው የሰጣቸውን ተልዕኮ ሲፈጽሙ እና ሲያስፈጽሙ ሁሉም እንደ ሾላ በግ ወደመታረጃቸው እየተነዱ አለቁ።

እንደ አሁኑ ዘመን ፖለቲካ «የዘር ሽብር» ሳይሆን የዛን ጊዜ መጠሪያው የገልበተኞቹ «ቀይ ሽብር» ሲባል ለተቃዋሚዎቻቸው የሰጡት ስም ደግሞ «ነጭ ሽብር» እየተባለ በቀለም ተለይቶና የፈረስ ሥም ወጥቶለት አንዱን አራጅ ሌላውን ታራጅ እድርጎት ነበር። እንግዲህ ብዙዎቹ አብሮ አደጎቼ እና ጓደኞቼ ነበሩ የዚህ ሰለባ የሆኑት። እኔና ጥቂቶች እንዴት ያንን ጊዜ እንደሸወድነው እግዜር ይወቅ። ለወሬ ነጋሪ፣ የምናውቀውን ለመተረክ፣ የጀግኖቹን ታሪክ ለአሁኑ ትውልድ ለማሳበቅ ቀርተናል። ተመስገን ነው። ለዛውም እስራቱን እና ግርፋቱን ሳንቀምስ አልቀረንም፣ ሞቱ ግን ዘሎናል። ከዛም አልፎ የጥይት ቅሪት እስካሁንም በሰውነቱ ውስጥ ተሸክሞ የሚኖርም ጓደኛችን አሁንም በሕይወት አለ። አትሙት ያለው ማለቴ ነው። እንደ ሕልም ሽው ብሎ ያለፈ ታሪክ እና ዕድሜአችንን እንደ ብል ያለፋይዳ በልቶ ያለፈ ዘመን።

ግን ከዚያ ክፉ ጊዜ ግን አንድ መልካም ነገር አይቼበታለሁ። ለድርጅት ፍጹም ታማኝነት። ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶች ለድርጅታቸው ታማኝ ነበሩ። የፖለቲካ ድርጅት መዋጮ የስለት ገንዘብ ያህል ነበር። አይቦጨቅለትም፣ ተጨልፎ ወደኪስ አይገባም። የድርጅቱ አምላክ የሚታዘባቸው ይመስላቸዋል። ለድርጅት ሕልውና መሞትም የዛኑ ያህል ነው።

አንድ መታገያ እና የማታገያ ድርጅት ምርጫ ብቻ ሳይሆን እምነትም ጭምር ነበር። ግዜው የድርጅት ወረትና ብርቅ ሆኖብን ነው መሰለኝ ሁሉም ለድርጅቱ ያለው ፍቅርና ታማኝነት ካሁኑ ጋር ሳወዳድረው ለካስ የሰው መልኩ ሁለት ነው ያሰኛል። የባህርይ መልኩ።

ሁሌ እንዲህ ነበር እያልኩ የድሮውን መተረኩ አንዳንዴ ራሴን እንድታዘብ ያደርገኝና ያሁኑን ሳስብ ደግሞ ካለፈው ጋር ለተምሳሌነት እንዳነፃፅር እገፋፋለሁ። ያለፈው አልፏል፣ እሱን ዝለልና ወደ አሁኑ አተኩር የሚለኝን ስሜቴን እጋፋዋለሁ። ለምን ቢባል ካለፈው መማር አልቻልንም እንጂ ሕዝባቸችን ያሳለፈው ታሪክ መልካምም ሆነ ክፉውን በታሪክነቱ ልንማርበት፣ ልንታረምበት የሚገባው ብዙ ገፅታዎች አሉት። የኛ ነገር «ታጥቦ ምን ሆነ» የሚለውን ዓይነት ሆንን እንጂ።

ዛሬ ድርጅት የሸሚዝ ያህል ነው። በየጊዜው ይቀየራል። ያውም ሳይታጠብ። ከቀደምት የፖለቲካ ድርጅታቸው ጋር ተጣብቀው እስካሁን ያሉ ጥቂቶች ናቸው።

አንዳንዴ ፖለቲካ ድርጅቶችን የመተዳደሪያ ደንብ እና ፕሮግራማቸውን ከሌላው ጋር ጎን ለጎን አስቀምጬ ሳስታየው በጣም ይገርመኛል። የብዙዎቹ የቃላት ለውጥ እንጂ ምንም የአቋም እና የግብ ልዩነት አታይበትም። ፍጹም አንድ የሆኑም ያጋጥሟችኋል። ታዲያ ለምን ከአንድ ይልቅ ዘጠና ዘጠኝ ለመሆን መረጡ ብላችሁ ጥያቄ ማቅረባችሁ አይቀርም። ለጥንካሬም ለሃሳብ ምንጭነት አንድነቱ ከፍተኛ ኃይል ይኖረዋል ብላችሁ መገመታችሁ አይቀሬ ነው።

ይኽንን በታዘባችሁበት ዓይናችሁ ደግሞ የድርጀቶችን መሪዎች የትናንት ምንነት ለመመርመር ሞክሩ።  ትናንት የአንዱ ድርጅት አባልና በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ደግሞ ለገዢው ድርጅት ማደራቸውን ወይም አዲስ ስም አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋማቸውን ይፋ ሲያደርጉ እና አዲሱን ፓርቲያችንን መርቁልን ሲሉ ስታዩ ፖለቲከኞቻችንን ምን ነካቸው ብላችሁ አታስቡም?

እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ሚዛን ላይ ካስቀመጣችሁ በኋላ ለመከፋፈሉ እና የአዲስ ድርጅትን ጥቅም አስልታችሁ መዝኑ። በዚህ በከፋ ዘመን፣ ሃገር የሰው ያለህ ብላ በምትጮኽበት ጊዜ፣ አንድ ሆኖ ከመቆም ይልቅ ተከፋፍሎ መሸነፍን መምረጥ እንቆቅልሽ አይሆንባችሁም?

የእኔ ስሌት ወደ አንድ ወገን ሚዛኑ ያደላል። ሕሊና እና ጥቅም ሳይጋጩ የቀሩ አይመስለኝም። ግዜው መረማማጃ ፈልጎ ራሰን የተቋም ተጠቃሚ መሆን ላይ ሳያደላ አይቀርም።

በሀገር ስም ፖለቲካ ድርጅት አቋቁሞ ወይም በፕሮግራሙ ላመነበት ድርጅት ቆሞ ከመታገል ይልቅ ሌላ ስም እና ካባ ለብሶ ወይም የዘር ካርታን በመምዘዝ አዲስ ድርጅት ማቋቋሙ ተመራጭ የሚያደርገው ሰፊ ምክንያት አለው። ጥቅም። በተለይ በትኩሱ።

ድርጅቱ ነፋስ ሳይነፍስበት፣ ተቃዋሚ ሳይተነፍስበት፣ የግለሰቦች ተንኮል ከመገለጡ በፊት። በአፍላው። ለአዳዲስ ፓርቲና ድርጅቶች ምረቃ ደግሞ እጅን ለመዘርጋትና   ለአንዱ ተገኝቶ ለሌላው መቅረት ትዝብት ላይ ከመጣሉ ባሻገር ነገ በለስ ቀንቶት ሥልጣን ቢይዝስ ምን ይውጠኛል? በሚል ስጋትም ጭምር ባንደግፍም ፊታችንን ለሹሞቹ ማስገረ ረፋችን ኪሳችንንም ለሙዳያቸው መዳበሳችን አይቀሬ ነው።

አንዳንዶቹ በዚህ ሥራ የከረመ ልምድ አላቸው። ዛሬ ታይቶ ነገ ስለሚጠፋው ድርጅታቸው ቅድመ እውቅና ቢኖራቸውም በትኩሱና በወረት የሚያመጣው ጥቅም ቀላል እንዳልሆነ ያውቁታል። የድርጅቱ የመክፈቻ ጥብጣብ  በመቀስ የሚቆረጥበት ዕለት እና በገንዘብ ድጋፍ ዝግጅት፣ በግብዣና እና በድርጅቱ ፕሮግራም ውይይት እለታት የሚገኙ ገቢዎች ሁሉ የሂሳብ መርማሪ የማይጎበኛቸው ኪስ ደጓሚ ንፁህ ከቀረጥ ነፃ ገቢ ናቸው።

መንፈሴ፦ ሐቀኞች፣ ለሀገር ተቆርቋሪ የሆኑ ኃይሎች እውነተኛውን የመታገያ መድረክ ፍለጋ የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል እያለ  ቢነግረኝም፣ አለመተባበሩ እና አንድ መሆን አለመቻሉ ለጠላት እንዳጋለጣቸው አለማወቃቸው ደግሞ ከበስተኋላ ሌላ ነገር እንዳለ እንድጠረጥር ይገፋፋኛል።

ይኼ ቀን ያልፍና፣ የውጪውም የውስጡም የነቃ ለታ ያዘጋጁት መልስ ይኖር ይሆን? አዲስ እናቋቁም ከማለት ይልቅ ያለነው ተዋሕደን አንድ እንሁን የሚል ሀሳብ የሚያቀርብ ምነው ጠፋ?

ሰውዬው ግንባባሩ ላይ ቆስሎ ሲሄድ ያየው ሰው፣ «አያ እገሌ ምን ሆነህ ግንባርህ ቆሰለ?» ቢለው «በጥርሴ ነክሼው» ይለዋል። «እንዴት ግንባርህን በጥርስህ መንከስ ቻልክ? ቢለው «ወንበር ላይ ቆሜ» አለው አሉ።

ነገ ለሕዝቡ የሚሰጡት መልስ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ይሆን? ነገራችን ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን እየሆነ ለመሸነፍ ስንመቻች ልቤ ያዝናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top