Free songs
Home / Editorials / Editorial 13: አህያ እና ዘመን

Editorial 13: አህያ እና ዘመን

Nafqot Editorial

Editorial

በአንድ ጦርነት ላይ ነው አሉ። ሰውዬው ከተፋፋመ ጦርነት መሐል ሾልኮ ሸሽቶ ለማምለጥ ወደ ኋላው ሲያፈገፍግ ገደል ገብቶ ይሞታል። ለዘመቻው ስንቅ ጭኖ ያመጣው አህያ ግን ባለቤቱን ፍለጋ ጦርነቱ መሐል ሲንከራተት በጥይት ይመታና ይሞታል። ይኽ ወሬ ይዛመትና ገደል ገብቶ የሞተው ሰውዬ ሠፈር መርዶው ደርሶ ለቅሶ ይደረግና አስለቃሽ ደረት ታስመታለች አሉ።

ታዲያ እንዲህ ብላ ገጠመች።

«አዬ ጉድ እናንተ ነገር ተዛወረ

የአህያው አማሟት ለጌታው በሆነ» አለች አሉ።

የአስለቃሿ አባባል እውነትነት አለው። ምነው መሞቱ ካልቀረ ከነክብሩ በሞተ ማለቷ ነው። የጫነው አህያ ከጀግኖች መሐል ወድቆ ጌታው ሲሸሽ መሞቱ የአህያውን ያህል ክብር እንኳ ማጣቱ፣ ይኽን ግለሰብ ለራሱም መጥፎ ታሪክ ለቤተሰቡና ለሃገሩም አሳፋሪ ተግባር ፈፅሟል ያሰኘዋል። ግን ሸሽቶ ሕይወቱን ቢያተርፍስ ኖሮ? «ብልህ ወይስ ፈሪ ለናቱ ይባል ነበር?» መልሳችን ከሁለት አንዱ ላይ ይወድቃል።

ይኽን ያለምክንያት አላነሳሁትም፣ የምለው ስላለኝ ነው። ለመሆኑ በያዝነው ጦርነት ማን ለማን ነው የሚሞተው ብላችሁ አስባችሁ ታውቃለችሁ? የትኛው ጦርነት ብላችሁ ልትጠይቁ ስለምትችሉ ግልፅ ላድርገው መሰለኝ።

በሃገራችን ላይ በሚታየው የዘር፣ የኃይማኖት፣ የፖለቲካ መስመር ክፍፍል ሁሉም ራሱን በሚጠቅመው መንገድ ስለሚመለከተው የሀገር ጉዳይ ከራስ ጥቅም ተለይቶ የማይታይበት ደረጃ ላይ ያደረስን ይመስለኛል። በእኔ ግምት ላይ ተቃዋሚ ሊኖር ይችላል። ለእኔ የሚታየኝን ነው ለመናገር የፈለኩት። እንግዲህ የዘመኑ ጦርነት ያልኩት ይኼንን ነው። አሁን ግልፅ ከሆነና ከተግባባን ከዚሁ ልጀምር ወይም ልቀጥል።

የምንሳተፍበት ማኅበር፣ የምንመራው ፓርቲ፣ የምንታገልለት የጎሣ ድርጅት፣ የምንዋጋለት የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የምናገለግልበት የረድዔት ድርጅት፣ የተሾምንበት ሥልጣን በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር ራሳችንን ካልጠቀመን በስተቀር በሐቅ እና በነፃ ለማገልገል ፍቃደኛ የሆንን ስንቶቻችን ነን? እነዚህን በዘመኑ ለከፍተኛ ጥቅም የሚያበቁ ተቋሞች የሚያስገኙትን ጥቅም ሞክረን ሳይሳካልን በመቅረቱ፣ ከተመረጥንበት ድርጅት፣ ኪሳችንን ይሞላል ብለን ካቋቋምነው ፓርቲ ወይም የረድዔት ተቋም ሸርተት ብለን የወጣን እንኖር ይሆን? ወይስ መልኩን እና ስሙን ቀይረን በአዲስ ሥም ብቅ ያልን እንጠፋ ይሆን?

በሃገራችን ታሪክ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ በየትኛውም ሀገር  ታይተው እና ተሰምተው የማይታወቁ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ የፖለቲካ፣ የዘር፣ የትናንሽ ጎሣዎች ድርጅት ታይተዋል። እኔ በቁጥር እንዳሰላኋቸው ቁጥራቸውም ከዘጠና አራት ቢዘል እንጂ አያንስም። እነዚህን ድርጅቶች የሚያቋቁሟቸው ጥቂት ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች የዘመኑ ገበያ በደንብ የገባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። መጀመሪያ ድርጅቶቹ ከመመሥረታቸው በፊት የሚያጠኗቸው ቀደምት ሁኔታዎች አሉ። የሚያሰባስቡት አባላት ብዛት፣ ሞኝ አባላት ሊያዋጡት የሚችሉት የገንዘብ መጠን በአማካይ በታሳቢነት ይመዘገባል። ከዛም የአባላትን ልብ ሊያማልል የሚችልና በሕልምነቱ ተጨባጭነት ባይኖረውም እውነት የሚመስል የዓላማ እና ግብ ደንብ መቅረፅ እና ተመሳሳይ አቋም ያላቸውን ሰዎች ከጎን መኮልኮል ይሆናል። ይኽ ከተከናወነ በኋላ የሠላ ምላስ፣ የሚያሳምን አንደበት፣ ሕልሙን እውን፣ ውሸቱን እውነት ለማድረግ የሚችሉ አንደበተ ርቱዕ ድምፃውያን ተናጋሪዎች ማዘጋጀት ቀደምት ተግባራት ይሆናል።

ከዚያ በኋላ ሥራ ይጀመራል። ነፃ የሚያወጡት ጎሣ እና ዘር፣ የሚገነጠለው ሃገር፣ ለእያንዳንዱ የሚደረሰው የመሬት ስፋት ልብን በሚያማልልና ሃገርና ወገኑን ሊጠላ እና ለማይደረስበት ነፃነት ዘለዓለማዊ ትግል ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። ይኽ ታዲያ በነፃ የሚመጣ ስላልሆነ «ነፃነት ካለደም አታገኝም» ይባልና ወደ ቀዝቃዛውና ወደማያቋርጠው ጦርነት እንዲገባ ይፈረድበታል። ገበያው ከቀና ድርድር ምንትስ ቅብርጥስ የሚሉ ማባበያ መንገዶችም ሊከፈቱ ይችላሉ። ገበያው ካልቀና ግን መሥራቾች እጅ ሰጥተው አቋማቸውን ቀይረው ወደ ገደል ወይም ወደ ጥቅሙ ገደል ገቡ ሲባል አህዮቹም በጦርነቱ መሐል ያልቃሉ። የአስለቃሿ ነገር የሚደርሰው እንግዲህ የዚህ ጊዜ ነው።

የሃገራችን የፖለቲካ ጉዳይ ሲነሳ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ይሆናል። እንደ ዘማቹ ሰውዬ እና እንደ አህያዋ ዓይነት ማለቴ ነው። መሆን ያለበት እንዲህ መሰለኝ። አምባ ገነኖችም ይሁኑ የንገሣዊ አገዛዝ መሪዎች የሚሉት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ አገር አንድ ናት፣ ሕዝብ አይለያይም፣ ድኅነት እና ችገር ከሃገራችን ይጥፉ፣ የጋራ ጠላታችን ላይ በጋራ እንዝመት የሚል መርህ ይከተላሉ። ይኽም ለአገዛዝ ዘመናቸው ማራዘሚያና የሕዝብ ተቀባይነታቸውም እንዲሰፋ ያደርገዋል። የኛ ግን ከዚህ ተቃራኒው ይመስላል።

«ኤርትራ አትገነጠልም ወንድምና እህቶቻችን ናቸው ሲባል፣ ማነው አንድ ነህ ያለህ? አሰብ ወደባችን ነው፣ ማነው ያንተ ያደረገው? በዘር በኃይማኖት አንለያይም፣ ማነው ዘርህ አንድ ነው ያለህ? ሁላችሁም የራሳችሁን ዘር እና ማንነት አጠንጥኑ። ታፍነህ እንዳታውቅ ተደርገህ እንጂ ሁላችንም የተለያየን ነን። አሁን ስለልዩነታችን እናውራ፣ አንድነቱ በኋላ ይምጣ።» ተብሎ ሲነገረን አንድነታችንን እና የሃገራችንን ጥቅም ያስጠብቃል ከምትሉት መንግሥት ሲመጣ «ዘመኑን ምነካው?» ማለታችሁ አይቀርም።

ከዚህ ባለፈም በተቃዋሚነት መቆም ራሱ ከጥቅም ጋር ካልተያያዘ ትግሉ መቅኖ ያጣል። የቆምንለት የሕዝብ የነፃነት ትግል እና የሠብዓዊ መብት ጥያቄ ከሚያስገኘው የግል ጥቅም ጋር በደባልነት ካልመጣ ትግሉ ቅመም የለውም የሚሉ እና ይኽንንም በተግባር ያሳዩ ወገኖች አልጠፉም።

አንዳንዴ በዚህ ዘመን በተለይ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ በጥልቀት ስታስቡት «ለሀገር መቆርቆር እና ለአንድነት መቆም የሚያስወቅስ፣ የሚያሳስር እና ግዜው ያለፈበት መርሕ አይሆንባችሁም?»  ወይም «ኢትዮጵያዊ ነህ ስትሉት ቀልድህን አቁም፣ አይደለሁም የሚል ወገን አልገጠማችሁም?» ኢትዮጵያዊነትንስ በዘር በኃይማኖት ተንትናችሁ፣ የትኛው ክፍል ነው ለኢትዮጵያዊነት የቆመው ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ?

በያዝነው ዘመን መሪ መሆን ማለት፦ ነጋዴ መሆን ማለት ይመስላል። ጠንካራ የሕዝብ ተወካይ ባለሥልጣን መሆን ማለት ትርፍራፊ የሚሻማ፣ ለሥጋው ያደረ፣ ሕሊናውን የሸጠ ካልሆነ በሕዝብ ተወካይነቱ መንግሥት አይቀበለውም፣ የመሪውን እና የመንግሥት ሥልጣን ተቀብሎ ሕዝብን ለማገልገል ቃልኪዳን የገባ ማለት፦ በደራው ገበያ መሐል የኢትዮጵያዊነት ዓይኑ የታወረ፣ ስለ አንድነት ሳይሆን ስለመከፋፈል የሚሰብክ፣ ነዋይ በሚያስገኝ ጉዳይ ላይ ሐገሩንም ሕዝቡንም ለመክዳት ወደኋላ የማይል ካልሆነ በስተቀር ለሕገመንግሥቱ እና ለልማታዊ ጉዟችን እንቅፋት የሚሆን ማለት ከሆነ፣ በእርግጥ ኢትዮጵያዊነት በጅምላው ምንድው?

በተለያየ መንገድ ለኢትዮጵያ አንድነት ለመቆም በጦርነቱ አውድማ ውስጥ ሕዝቡን አሳምነው እና ጭነውት የገቡት ሰዎች ጥቅማቸው ሲነካ በጦር አውድማ ውስጥ ሕዝቡን በትነው ይክዱታል ብለን ካሰብን፣ እኛስ በእነሱ ስብከት የተጫንን የሕዝብ አካላት አህያዋ መሆናችን ይሆን?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top