Free songs
Home / Editorials / Editorial 12: ልብ ያመስግን ሲባል እሰማ ነበር…ለካስ…?

Editorial 12: ልብ ያመስግን ሲባል እሰማ ነበር…ለካስ…?

Nafqot Editorial

Editorial

ናፍቆት ኢትዮጵያ መጽሔት ከአንድ ምዕራፍ ወደሚቀጥለው በተሳካ ሁኔታ ተሸጋገረች። ይኽንንም በቅርብ የተመለከቱና ለ5ኛ ዓመት የልደት በዓላችን ያዘጋጀነውን የሰሙ ብዙዎች ማበረታቻ መልዕክታቸውን አዥጎደጎዱልን። የኛ ጥረት ብቻ  ሳይሆን የሁሉም የናፍቆት ኢትዮጵያ ቤተሰቦች ውጤት በመሆኑ ምሥጋናው የእነሱም በመሆኑ ተቀበልነው።

አንዳንድ ሰዎች ሌላውን ለማመስገን ፈጣን የምሥጋና ቃላት ያገኛሉ፣ ሌሎች ደግሞ ምሥጋናቸው ጥልቅ እንዲሆን ለቃላት ምርጫ ጊዜያቸውን ያራዝሙታል። የምሥጋና ቃላት ለመምረጥ። የኛ ግን ከሁለቱም ወገኖች ጎራ አይወድቅም፣ ለምን ቢሉ ድጋፍ የሰጡንን እና እዚህ ለመድረስ የተባበሩንን የምናመሰግንበት ቃለት የለንም። በደፈናው «ልብ ያመስግን» የሚለውን መረጥን።

ጅምራችን ወዴት እንደሚወስደን ባናውቅም በደፈናው «ባሕልና ቋንቋ በባዕዱ ዓለም እንዳይረሳ» የሚል መርህ ይዘን ነበር የተነሳነው። ለመጽሔቱ የሚሆኑ ፅሑፎች፣ ለተከታታይ ወራት የሚሆን የማሳታሚያ ወጪ፣ ድጋፍ የሚሰጡ ወገኖች ከየት እናገኛለን የሚሉትን እና የመሳሰሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከግምት ውስጥ ያላስገባ ጭፍን ጅምር ነበር ብንል አልተሳሳትንም። እውነቱም ያ ነበር። ያኔ የዛሬ አምስት ዓመት መጽሔቷን ስንጀምር።

ለአንድ ለሁለት ወራት ከቆዩ የግል ሥራዎች እያውጣጣን እና ከጠቃሚ መጽሐፍት ያገኘናቸውን እየቃረምን በመጽሔቷ ላይ በማስፈር መንገዳገድ ጀመርን። ወኔው ጠንካራ የነበረ ስሜት ለጊዜው የሚሸነፍ አይመስለውምና ወራት እየቆጠርን ሶስት ወራቶች አደረስናት። በእነዚህ ጊዜያት ጥቂት አንባብያን ማፍራት ብንችልም ከሕትመት አካባቢዋ መውጣት አለመቻሏና ራሷን በሕትመት ወጪ በኩል አለመደገፏ ትልቁ ራስ ምታት እየሆነብን መምጣቱ አልቀረም። በዚህ ጊዜ ነበር ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመፈለግ መሯሯጥ የጀመርነው።

በአካባቢያችን ያሉ ጥቂት ቢዝነሶችን እና የምንግባባቸውን ሰዎች ማማከሩ በአንድ እጅ ከማጨብጨብ እንደሚያድነን በመገመት ጥቂቶቹን አነጋገርን። ከመረጥናቸው ውስጥ ብዙዎቹ አላስቀየሙንም። ከጎናችን ለመቆም ተስማሙ። ግን ለምን ያህል ጊዜ? ያም በገደብ የሚለካ ባለመሆኑ ሌላው ሃሳብ ላይ የጣለን ነገር ቢሆንም በጊዜያዊነት ባገኘነው የተስፋ ቃል ድጋፍ ብቻ በመመርኮዝ እና በመርካት የመጽሔቷን ስርጭት ቀጠልን። ይኽ በእንዲህ እያለ አንድ ሃሳብ ድንገት ብልጭ አለ። ወደ ሌሎች ስቴቶች መጽሔቱን ማስተዋወቅ። ለጊዜው ተስፋ ያገኘነው ከወደ ቴክሳስ ዳላስ ከተማ በመሆኑ ለሙከራ በሚል ጥቂት መጽሔቶች ለመላክ ወሰንን። ግን አሁንም ለማን እና በየትኛው መደብር በኩል? አካባቢውን የሚያውቁ ሰዎች አጠያየቅን። የቱ ይሻላል? በሚል። ለ«ማሩ ግሮሰሪ» ላኩላቸው አሉን። እስካሁን በናፍቆት ኢትዮጵያ ቤተሰብነቱ ላልተለየን።

ስልክ ደወልንና ፍቃደኝነታቸውን ጠየቅን። ምንቸግሮን ተባልን። እንግዲህ በፍጹም ለማናውቃቸው ሰዎች የመጀመሪያውን ስርጭት  ከአካባቢችን ውጪ መጽሔቶቹን በፖስታ ቤት በኩል ሸኘናቸው። ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ተጨማሪ እንድንልክ ጠየቁን። «የለንም ያሳተምነው ይህን ያህል ብቻ ነው»  አልናቸው። ከአካባቢያችን ይልቅ የውጪው ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ እየታየን ሳይሄድ አልቀረም።

መጽሔቷ የምትታተምበት ዋናው ቤቷ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ጭራሽ አንባቢ እንደሌለ ያወቅነው የዛን ጊዜ ነበር። መጽሔት አገላብጦና አይቶ የሚመልስ እንጂ ገዝቶ የሚያነብ የለም። ያውም በዛን ወቅት የአካባቢያችን ስርጭት ካለምንም ክፍያ በነፃ ነበር። እኛም ለምናልባቱ የዚህ አካባቢ ሕዝብ የለመደው ጥራት ያለው መጽሔት እንጂ እንደናፍቆት ኢትዮጵያ ያለውን መጽሔት ለማንበብ ጊዜም ያለው አልመሰለንምና የመጽሔቷን ጥራት ለመጠበቅና ለማሻሻል ሙከራችንን ቀጠልን። ከጊዜ ወደ ጊዜ መጽሔቷን ደረጃዋን የጠበቀች ለማድረግ ባደረግነው ጥረት ግን በአካባቢያችን ያለው አንባቢ በቁጥር መቀነስ እንጂ ሊጨምር አልቻለም።

አማርኛ የሚናገርና የሚያነብ የለም እንዳንል «የአማርኛን ቋንቋ ጎጆ ያወጡ የሚመስሉ» ተናገሪዎች ያሉበት ከተማ ነው። ድክመቱ ከኛ ስለመሰለን የመጽሔቷን ብቃት የእነሱ መለኪያ ሚዛን ላይ ለማውጣትና የአንባብያንን ልብ ለማሸነፍ ትጋታችን ቀጠለ። የሚገርመው ግን እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ የአካባቢያችንን ልብ በአብዛኛው ማሸነፍ አልቻልንም። ምናልባት «በእጅ የያዙት ወርቅ..» እንደሚሉት ዓይነት ነገር ሳይሆን አልቀረም። ይሕንንም ሽንፈታችንን በሁለት መልኩ ከፈልነው። አንድም የአካባቢያችን ሰው አማርኛ ቋንቋ ማንበብ እረስቶ ወደ እንግሊዝኛ ጋዜጦች አድልቷል፣ አሊያም የኛ መፅሔት ሚዛን የአካባቢውን አንባቢ ሚዛን አልደፋችም የሚሉ ግምቶች። ከሁለቱ አንደኛው ልክ ሳይሆን አይቀርም።

በዚህ ሁኔታ እንደ ሕፃን ልጅ እድገት ቀስ ብለን በትዕግስት እና ተስፋ ባለመቁረጥ እዚህ ደርሰናል። ባሁኑ ወቅት በመላው አሜሪካ አስራ ሁለት ስቴቶችና ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያን ጨምሮ ከአንድ መቶ በላይ የማከፋፈያ መደብሮች መጽሔቷን በማከፋፈል ይረዱናል።

እንግዲህ የናፍቆት ኢትዮጵያን መጽሔት እርምጃ እና እድገት በተመለከተ በዋናው ጽሑፋችን ላይ የምንለው ይኖረናል። እስካሁን ባደረግነው ጉዞ ከጎናችን በመቆም ከጅምሩ የረዱንን ግለሰቦች እና ድርጅቶችን ለማመስገን ቃላት ስለሌለን «ልብ ያመስግን!» እንላለን። አዛውንቶቻችን «ልብ ያመስግን ሲሉ እሰማ ነበር…ለካስ እውነት ኖሯል!» ማመስገኛ ቃላት ሲያጡ ምን ያድርጉ?

በጉዟችን ላይ እንቅፋት ለመሆንና ተስፋ ለማስቆረጥም ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉትንም ግለሰቦች ሳናመሰግን አናልፍም። የእነሱ እኩይ ፍላጎት እኛን ሳያጠናክረን አልቀረምና። ማንም ኃይል ካለተቃዋሚ በተደላደለ ነገር ላይ ከቆመ «ከማደግ ይልቅ መዘናጋት እና መፍዘዝ» ሳይጫነው አይቀርም የሚል አባባል አለና። ግን ሰዎች ተባብሮ ከመስራት እና ለወገን ጥረት ቢቻል በሞራል መደገፍ ካልተቻለ ደግሞ ገለልተኛ ሆኖ መቆም እያለ ለምን ለማጥፋት ይፈልጋሉ? «እኛ ካልሰራነው ሌላው መሞከር የለበትም» በሚል ፈሊጥ ይሆን? ዘመን አመጣሿ በሽታ ይሏችኋል ይኽቺ ናት!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top