Free songs
Home / Editorials / Editorial 11: ዓመተ ምሕረት ወይስ ዓመተ ፍዳ?

Editorial 11: ዓመተ ምሕረት ወይስ ዓመተ ፍዳ?

Nafqot Editorial

Editorial

በፊት የማውቀውን የ‹‹ቃለ ምሕረትን›› ትርጉም ፍለጋ መዝገበ ቃላት ማገላበጥ ገባሁ፡፡ ባልሳሳት ከሦስት በላይ የአማርኛውን የቃል ፍቺ ሰጪዎች መጻሕፍት ጎብኝቻለሁ፡፡ እንዲያው ለነገሩ እንጂ ይኽ በየዕለቱ ከአፋችን በተለያዩ ሌሎች ቃላቶች ታጅቦ የሚወጣው አንድ ፈርጅ ቃል ‹‹ምሕረት›› አዲስ ሆኖብኝ አይደለም፡፡ ዛሬ ለምለው ወይም ልዘምትበት ለተነሳሁበት ጉዳይ ሁለት ፍቺ ኖሮት ችግር ውስጥ እንዳይከተኝ ለመጠንቀቅ ስል ነው፡፡ የቃሉ ሙሉ ትርጉም በየመዝገበ ቃላቱ እንዲህ ይነበባል፡፡

ምሕረት፡- ማረ፣ ይቅር አለ፣ ያለፈውን በደል ሻረ፣ ለተበደለው ይቅርታ አደረገ፡፡ ይላል መፅሐፉ፡፡

የእኔ አነሳስ ግን ይህንን ትርጉም መሠረት በማድረግ፣ የሰው ልጅ ከዓመተ ዓለም ወደ ዓመተ ምሕረት ከተሸጋገረ በኋላ ነው ወይስ በፊት መከራና ፍዳ የበዛበት? በእርግጥ ዓመተ ምሕረት የተሰኘው የምሕረት ዘመን ቃልና ትርጉሙን ጠብቋል ወይ? ከሚለው በመነሳት ላይ የመነጨ ነው፡፡

በቃል ኪዳን ቃሉ ፈጣሪ ‹‹ከሠማያት ሠማያት ወርጄ ከድንግል ማሪያም ተወልጄ›› በሚለው ቃሉ የሰውን ልጅ ኃጢያት አንፅቶ ያለፈውን በደል ሽሮ ከጥፋት ሊድነው ወደዚህች ዓለም ሲመጣ፣ ተስፈኛው የሰው ልጅ ቃሉን የወሰደው በጥሬው በመሆኑ የፈጣሪን ቃል እና ትዕዛዛት ባለማክበሩ እንደገና ወደ ጥፋት ተመልሶ ያለፈ እና የተሻረለትን ጥፋቱን በእጥፉ ሳይተካው ይቀራል?

ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣትና ለሠው ልጅ ኃጢያት ሲል መከራ ከተቀበለ እና ያለፈውን ከሻረው በኋላ ዘመኑ ለምን የምሕረት ዓመትነቱን አላሰየንም? እስቲ ዓመተ ዓለም እና በዓመተ ምሕረት የነበሩትን ጥፋቶች ወደኋላ ዞረን እንቃኝ፡፡

የኖህ ዘመን የውሃ ጥፋት፤ የሎጥ ዘመን የእሳት ቅጣት፤ይኽ እንግዲህ ከፈጣሪ በመጣ ቅጣትነቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ የሰው ልጅ ሕይወቱን እየለወጠና እየተሻሻለ፣ በኃይማኖት በነገድ እየተከፋፈለ መኖር ከጀመረ በኋላ ያለውን በቅንጭቡ እንመልከት፡፡

ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከራሱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ብንጀምር እንኳን፡- ሮማውያን በይሁዳውያን ከሳሽነት ንፁሑን አምላክ ሰቀሉት፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው የሰው ልጅ ታሪክ ደግሞ እስካለንበት ዘመን ድረስ የምሕረት ሳይሆን የፍዳ ይመስላል፡፡

ኃይማኖትን ለማዛመት የተደረጉ ጦርነቶች የቀሰፉት ሕይወት፣ የአህጉራትን ልዑላዊነት ለማስጠበቅ በሚል የድንበር ክለላ ያስከተለው ሥር ነቀል ዕልቂት፣ የቅኝ አገዛዝና ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት የተደረጉ ጦርነቶች የፈጁትና ያስፈጁት የንፁሃን ሕይወት በአጭሩ እንደ ዋቢ የምንጠቅሳቸው ናቸው፡፡

ይኽንን በዚህች አጭር የመልዕክት ገጽ ላይ መጀመር እንጂ መጨረስ ስለማንችል፣ በዚህ አንጠልጥለን እንለፈውና ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ‹‹የዓመተ ምሕረት›› ጉዞአችን ያለፍንበትን ‹‹የምሕረት ዘመን›› በአጭሩ እንቃኝ፡፡

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ዘመን በሕይወት ያለ ሰው ካየው የደስታ እና የፍቅር ዘመን እና ካለፈበት ችግር ጋር ሲያነፃፅረው የትኛው ጎልቶ የሚታይ ይመስላችኋል? ከእኛ በጥቂቱ ካለፉት እና የእኛ ትውልድን የሕይወት ጉዞ እንኳን ብንመለከት ያለፍንበት ችግር እና መከራ ለምደነው ካልሆነ በስተቀር ቀላል አይደለም፡፡

በትውልድ ሐረግ ቆጥሮ ወይም በጠበንጃ ሥልጣን የያዘ መንግሥት በትረ ሥልጣኑን ከያዘበት ቀን አንስቶ የመበደል፣ የማሰር፣ የመውገር አልፎም የመግደል ሙሉ መብቱ በሥልጣኑ ወንበር ሥር የወደቁለት የማይጠየቅበት ጉልበቱ ናቸው፡፡

ታዲያ በየዘመኑ ዓመታት በተቀየሩ ቁጥር ‹‹እንኳን ከዘመን ዘመን በሠላም አሸጋገራችሁ›› እንባባላለን፡፡ የትኛው ሠላምና ደስታ ያየንበት ዓመት እንደሆነ ለእኔ አይግባኝ እንጂ ልምድ ሆኖ ወይም መባል ስላለበት የመከራ ኑሮአችን ስለተራዘመና ወደፊትም እንዲቀጥል መልካም ምኞታችንን መግለጻችን ሳይሆን ይቀራል ትላላችሁ?

መሪዎቻችንም በየዓመቱ ለእኛ የአዲሱ የፍዳ ዘመን መጀመርና ለእነሱ የአዲሱን የሥልጣን በትር ማጠንከሪያ የ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› መልእክታቸውን ያሰሙናል፡፡ እኛም እናጨበጭባለን፡፡ ደንብና ባሕል መሆኑ መሰለኝ፡፡

እኛ እዚህ በአሜሪካ ምድር ያለነው ብዙዎቻችን ወደን በጣም ጥቂቶቻችን ተገደን ካገር በመውጣት የቀድሞውን ፍዳ ቀምስን ዘመናዊውን ቅጣት አምልጠን በሩቁ ሆነን ሕዝባችንን ለመታዘብ ታድለናል፡፡ አንዳንዶቻችን ለምን ሃገራችን እንደ አሜሪካ አትሆንም፣ ለመሆንስ ምን ያንሳታል? ብለን ራስን ከመጠየቅ ባለፈ ልናደርግ እና ልንለውጥ የምንችለው ነገር ስለሌለ ቀን ያመጣውን ቀን እስኪወስደው ብለን ዳር ቆመን እናያለን፣ ከፊሎቻችን ደግሞ በተለያዩ የስብሰባ ዓይነቶች እንገናኝና ሀገር የበደሉትን ሙልጭ አድርገን በመስደብና በመርገም ጊዜያዊ የሆነ እርካታ በማግኘት ጥሩ እንቅልፍ ይዞን ያድራል፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ በጋራ ተራግመን ‹‹የጋራ ሕክምና››(Group Therapy) የምናደርገበትን መንገድ እንፈልጋለን፡፡

አሮጌው ዘመን ግን እኛን እያስረጀ፣ አቅማችንን እየቀማ፣ ፊታችንን በብስጭት እያጨማደደ አዲስ ነኝ ብሎን ብቅ ይላል፡፡ በአዲስ ዓመት ደግሞ አዲስ ነገር መመኘቱ አይቀሬ ነውና ለሃገርና ለሕዝባችን መልካም ነገር እንመኛለን፣ የሚቀየር ነገር ግን የለም፡፡ ቆራጥ ሆነን በጋራ የመጣውን ተቀብሎ ለውጥ ለማምጣትና እውነተኛውን ‹‹እንኳን ለአዲሱ እና ለተሻለው ዓመት አደረሰዎ!›› ለማለት አልታደልንም፡፡ ዘመኑም ይሮጣል፣ ሕዝባችንም ለአዲስ ዱላ ራሱን እያዘጋጀ ይሮጣልን፡፡ ለውጥ ሳይኖር፣ መልካም ነገር ሳናይ ‹እንኳን ለአዲሱ….አደረሳችሁ!› የሚለው ቃልም ላልተወሰነ ዘመን ይቀጥላል፡፡ እንግዲህ ዓመተ ምሕረት ወይም ዓመተ ፍዳ መሆኑን ሳላረጋግጥ እኔም ‹‹እንኳን አደረሰን!!!›› ልበል መሰለኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top