Free songs
Home / Editorials / Editorial 10: ጁሓራዊ በረከት

Editorial 10: ጁሓራዊ በረከት

Nafqot Editorial

Editorial

ጁሓራዊ በረከት

መጀመሪያ ዓብዮት የሚባል አዲስ ግኝት በደሃዋ አገራችን እንደ ዝናብ ጎረፈ። እኛም በዕልልታ ተቀበልነው፣ በዓብዮቱ የተጎዱም ኃዘናቸው በረታ። 17 የቁጣ እና የሰመመን ዓመታት አስቆጠርን እና ደግሞ ራሳቸውን ነፃ ሊያወጡ ጫካ የገቡት በለስ ቀናቸውና በድንገት እኛንም ነፃ አወጣናችሁ አሉን። ከማን እንደሆነ ባናውቅም ነፃ ወጣን። ነፃ አውጪው በዛና አገራችን በድንገት ነፃ አውጪ በነፃ አውጪ ተጥለቀለቀች።

ነፃ አወጣናችሁ ያሉን ለሌሎችም ነፃ አውጪ ፈጠሩላቸው። ማ ማንን ነፃ እንዳወጣ ሳናውቅ ሁላችንም ለነፃ አውጪዎቻችን አጨበጨብንላቸው። በጫካ ጥናት የተቋቋሙ ነፃ አውጪዎች፣ በድንገት የተፈጠሩ ነፃ አውጪዎች፣ የሠፈር እና ጎሣ ነፃ አውጪዎች እንደ አሸን ፈሉብን። መለያቸው እንዲሆንም ሁሉም ባለባንዲራ ሆነው የሃገራችንን ታሪካዊውን እና በዱር በገደል ከጠላት ጋር ሲዋደቁ የሞቱለትን ባንዲራ እንደ ጠላት ተቆጠረ።

ከትናንት ወዲያ ዓብዮት፣ ትናንት ነፃ አውጪ እና የጎሣ ዓብዮት፣ ዛሬስ ምን ታዘብን? ምን ሸተተን? ምን ተዘጋጅቶልናል? በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም ብቸኛዋ በዘር ለተደራጀችዋ ሃገር የሚጠብቃት ምን ይሆን? እንግዲህ እዚህ ላይ ነው እነ ጁሐር መሐመድ ብቅ ለማለት አጋጣሚውን የተጠቀሙት።

የአክራሪ እስልምና ኃይማኖት በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች እንዲሁም በሠሜኑ የአፍሪካ ክፍል በአስደንጋጭ እና አሳሳቢ ሁኔታ በተከሰተበት በአሁኑ ወቅት የእነ ጁሐር መሀመድ ግልፅ መልዕክት ያለምክንያት አልነበረም።

ጁሓር አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረስ እና ተከታይ ለማብዛት የተጠቀመበትን በጣም ጥበብ የተሞላበት ዘዴ መመልክት በእጅጉ ጠቃሚና ወደየት እንደሚሄድም ለመገመት ጥቆማ ይሰጣል። በመጀመሪያ የተመረቀበት የሃርቨርድ ዩኒቨርሲቲ መንገዱን ለመጥረግ መልካም መሰላል ሆነለት፣ ተከትሎም በግል ያዳበረው የንግግር ችሎታ ሌላውን ለማሳመን እንዲችል አድርጎ ልምምዱን አጠናቀቀ፣ በተከታይም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ሃገር አቀፍ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ተቆርቋሪነቱን በመግለጽ ብቅ ማለት ጀመረ፣ ይኽ ለሃገር ተቆርቋሪ የሚመስል ሥራው በታዋቂ ሚዲያዎች ግብዣ እንዲቀርብለትና ስሙ እንዲገን መልካም አጋጣሚ ፈጠረለት። ለመጨረሻ ዒላማው የሚፈልገውም ይኽ ስለነበር ጁሓራዊ ጭምብል ያጠለቀ ፍላጎቱ ከዚህ በኋላ ወደ እውነተኛ ጁሓራዊነት ተሸጋገረ።

እነ ጁሓር፣ የኢትዮጵያ እስላም ለምዕት ዓመታት ከሌላው ኅብረተሰብ በተለየ መልኩ እንደተጨቆነ እና በአሁኑ «የኦሮሚያ እስላሚያ» ትግል ሃያ እጅ የሚሆነውን የክርስቲያን ኦሮሞዎችን ይዞ ነፃ እንደሚወጣ ይሰብኩናል። በኢትዮጵያ የሃይማኖት አሰላለፍ ከሃምሳ እጅ የሚበልጠውን ድርሻ የሚይዘው «እስላሚክ ኦሮሞው» ትግሉንም የመምራት ኃላፊነት ታሪክ ጥሎበታል ይለናል።

በጁሓር መሐመድ እና በመንፈሳዊ አባቱ ሃጂ ነጂብ ስሌት የኢትዮጵያ እስላም ኅብረተሰብ ቁጥሩ ሃምሳ ሚሊዮን ነው በሚል ማረጋገጫ የሚነግሩን እኒህ ግለሰቦች በየትኛው የማባዣ ቁጥር እንደተራባ ባይገባኝም፣ እንደሚመስለኝ ከሆነ፣ ከሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ የሃምሳ ሚሊዮን ቁጥር ያለው ኃይማኖት ኃይልና ጉልበቱም ቀላል እንዳልሆነ ሊነግሩን የፈለጉ ይመስላሉ። ለነገውም እስላሙን ኅብረተሰባችንን ምን እንዳዘጋጁለት አላህ ይወቀው።
«እኔ እና ሌሎች እኔን መሰል ኦሮሞዎች በቅድሚያ «ኦሮሞ» ቀጥሎም በጫና ወይም በምርጫ «ኢትዮጵያዊ» ሆንን» የሚለው ጁሓር መሐመድ ስለ ኢትዮጵዊነቱ ጫና በተለያየ መንገድ ሊነግረን ይሞክራል። የኢትዮጵያ እስላም ኅብረተሰብም ትዕግሥተኛ ስለሆነ እንጂ በብዛትም በሞራልም ከማንም በላይ እንደሆነና ይኽንንም ባለፉት ዓመታት ያሳየውን ቆራጥነት እንደምሳሌ አድርጎ ይነግረናል። ይኽ ወጣት ለረዥም ዓመታት በፍቅር እና በመተሳሰብ የኖረውን የክርስትና እና እስልምና ኃይማኖት ተከታዮችን ዛሬ ሚናቸውን እንዲለዩና አንዱ የአንዱ ጠላት፣ አንዱ የሌላው ጨቋኝ ሆኖ እንደኖረ ባገኘው አጋጣሚ ይሰብከናል።

በእኔ እውቅና የኢትዮጵያ እስላም እና ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ተቻችለው የኖሩበትን ዘመን አላስታውስም፣ የኖሩት ተዋደው እና ተፋቅረው ነው። ተቻችለው እና ተጠባበቀው መኖር የጀመሩት አሁን ይመስለኛል። በመቻቻል እና በመፋቀር መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። መቻቻል፡- አንድን ነገር ወይም ችግር ተዳፍኖ እንዲቆይ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ብቻ ሲባል የሚደረግ ዘዴ ሲሆን፣ ተፋቅሮ እና ተዋዶ መኖር ግን ቀድሞ እንደምናየው በሁለቱ ኃይማኖቶች መካከል ይታይ የነበረውን የማኅበራዊ እና የሥነ-ልቦናዊ ትስስር፣ በጋብቻ፣ በግብዣ፣ በጉርብትና፣ በባሕላዊው ዕቁብ እና የጋራ ማኅበራት ተሳስሮ መኖር ነው።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ እስልምና ኃይማኖት ተከታዮች የመብት ጥያቄ ይዘው በመነሳት ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ የሠላማዊ ሠልፍ ትግል ላይ ናቸው። ይኽ ትግል በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ድጋፍን አግኝኝቶ እስካሁን ዘልቋል።

ይኽን ሕጋዊ የእስልምና ጥያቄ ተገን በማድረግ እነ ጁሓር ደግሞ ከመብት ጥያቄ በዘለለ የማንነት ጥያቄ ከጎኑ በማሰለፍ ሌሎች ኢትዮጵያዊ እስላሞች እንዲከተሉት እና የእሱን አርማ እንዲያነግቡ በየአጋጣሚው ቅስቀሳውን በማድረግ ላይ ይገኛል። ለመሆኑ «ጁሓር መሐመድ ማነው?» የሚል ጥያቄ ያነሳ ሰው ይኖር ይሆን? ጁሓር መሐመድ ገዢው መንግሥት በድል ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ ከአምስት ዓመት የዘለለ ዕድሜ ያልነበረው፣ ስለ ኢትዮጵያ የኃይማኖትም ሆነ አጠቃላይ ስለ ሃገሪቱ ጥንታዊ ታሪክ ቅንጣት እውቀና የሌለው አጋጣሚውን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን እስልምና ተከታዮች ለሃይማኖታቸው እኩልነት እና ለመብታቸው ከሚያደርጉት ትግል ጎን በስሜታዊነት «የማንነት ጥያቄ» እንዲያነሱ እና የእርስ በእርስ እልቂት እንዲፈጠር እድሉንም ካገኘ «ኦሮሚያ እስላሚያ» እንድትፈጠር «ጁሓራዊ በረከቱ»ን ሊሰጠን የተዘጋጀ ፍጡር ነው።

ኦሮሞም ሆነ አማራ፣ ትግሬም ሆነ ጉራጌ እንዲሁም ሌሎች ብሐረሰቦች እስከ ዛሬ «ማንነታቸውን ሚዛን ላይ ያስቀመጡበት እና ጎሣችን ወይም ኃይማኖታችን ከኢትዮጵያዊነታችን በላይ ሚዛን ይደፋል ያሉበት ወቅት በታሪክ ታይቶም አይታወቅ። የእነ ጁሓር መሐመድ ምክር እና ግፊት ፍሬ ያፈራል ወይስ ማንነቱን አጋልጦ በኢትዮጵያዊ እስላሞች ያስተፋዋል?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top