Free songs
Home / Ahmaric / ታምራት ላይኔ – የፖለቲካ አማካሪ?
ታምራት ላይኔ – የፖለቲካ አማካሪ?

ታምራት ላይኔ – የፖለቲካ አማካሪ?

በታፈሰ ወርቁ

 

የትናንት ጀግኖቻችንን ዛሬ እንዘክር፣ የነገ ጀግኖቻችንን እንፍጠር! (የኔሰው ገብሬ እና በህወሃት እጅ የወደቁ እና የታሰሩ በርካታ ዜጎችን እንደ ምሳሌ)

አካፋንም አካፋ እንበል! (ታምራት ላይኔን እንደ ምሳሌ)

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መጽሃፋቸው ገጽ 15 ላይ ያለችው አንዲት አንቀጽ የውድቀታችንን አንዱን እና ዋነኛ ምክንያት ጠቅልላ ትናገራለች።

“… እንደ ኢትዮጵያ አርበኞቹን የገደለ በዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም፤ እነ በላይ ዘለቀን፣ እነ ራስ አበበ አረጋይን፣ እነ መስፍን ስለሺን ስንትና ስንት ሌሎች አርበኞችን ገድለናል፤ በአካል የተገደሉት አርበኞቹ ቢሆኑም ልጆቻቸው ደግሞ በመንፈስ ሞተው የእሳት ልጅ አመድ ሆነዋል፣ በሰፈሩት ቁና ሆነና አጼ ሃይለ ስላሴ እንቅልፍ አጥተው ላቋቋሙት የአፍሪካ ህብረት ሃውልት የተሰራው ለሳቸው ሳይሆን ለንኩሩማ ሆነ! በዚህ ሁሉ ውስጥ አርበኞችንና ባንዶችን መለየት የማይችሉ ክብርና ኩራታቸውን የተገፈፉ ትውልዶች እያለፉ ነው፣ አንገታቸውን የሚደፉ የአርበኞች ልጆችና ደረታቸውን የሚነፉ የአርበኞች ልጆች እየታዩ ነው፣ ከዚህ የበለጠ መክሸፍ ምን አለ?…”።

ኢትዮጵያዊያን አርበኞቻችንን/ጀግኖቻችንን እናወድሳለን? በበቂ ባናደርገውም እያደረግነው እንደሆነ ለምሳሌ የሜልቦርኑ ኢሳት እገዛ ማሰባሰቢያ ላይ ያየነውን፤ በዚያ ግሩም ሰዓሊ የተሰራው አይነት የኮሎኔል ደመቀ እና የአትሌት ፈይሳ ምስል ተሰብሳቢውን ብቻ ሳይሆን እኔንም ስሜቴን ወጥሮ የያዘ ነበር። ግን ከዚያም በላይ ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ “የሞገስ/ሰማዕት/ጀግኖች” ቀን/ሳምንት…” የሚል ስም መፍጠር እና በየጊዜው እየተዋደቁ እና እየወደቁ ያሉ ዜጎቻችንን በየመገናኛ ብዙሃኑ ስማቸውን ከፍ ማድረግ ይቻላል።

የግራፊክስ ሙያ ሊቅ መሆን ሳያስፈልግ፣ የሰማዕታቱን ፎቶዎች ከነስማቸው እና ገድላቸው በየተራ፣ ቢያንስ የአንድ ወይም የሁለት ሰማዕታት በየቀኑ ወይም በየተወለዱበት/መስዋዕት በሆኑበት ቀን ማውጣት፣ የህወሃት/ማሌሊትን ሞት አፋጥኖ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻነት ያቃርባል፣ ይህንንም ቀን “የሞገስ ሳምንት/ወር/ቀን/…” የሚል ስም በመስጠት አንድ ፕሮግራም በሁሉም የመገናኛ ብዙሃን (ድረገጾች፣ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ሬዲዮዎች ጋዜጦች ወዘተ…) አማካይነት በአንድነት እና በተመሳሳይ ቀን እያንዳንዱ ሜዲያ ባለቤት እንደሚመቸው በማውጣት፣ እነዚያ ሰማዕት ጀግኖች እንዲዘከሩ ማድረግ፣ የሰማዕቱን ዘመዶች እና ወዳጆች ያጽናናል፣ የነሱ ሞት የህወሃት ሞት እና የኢትዮጵያዊያን ትንሳኤ መሆኑን ወዳጅ ዘመዶቻቸውም ሆነ በህይወት ያለው ሌላው ታጋይ ሁሉ እንዲያውቀው ማድረግ ሌሎች ጀግኖችን መፍጠር ይሆናል። በተለይ ኢሳት እና ሌሎቹም አለም አቀፍ ተደማጭነት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን፣ እንዲሁ  እጅግ ጠቃሚ የሆነ የአየር ጊዜን በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዩች ላይ ማዋል ይጠበቅባቸው ይመስለኛል።

አካፋንም አካፋ ለማለት ድፍረቱ ያስፈልገናል። ከአብዛኛዎቹ የምዕራባዊያኑ የሞራል መሰረት ሁሉ የሚያስደስተኝ አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር፣ ከአስር አመት እና ከዚያም በፊት የተሰራ ወንጀል/ጥፋት መሆኑን እና ምንም አይነት ማስረጃ እንደማይገኝባቸውም እንኳን እያወቁ፣ እየተንሰቀሰቁ እያለቀሱ ጥፋታቸውን የመናዘዝ ባህላቸው ነው። የሚገርመው ነገር፣ ከይቅርታው በኋላም እንኳን፣ ምናልባት ቅጣቱን ያቀልልላቸው እንደሆነ እንጂ፣ በጥፋተኛነት እንደሚያሰቀጣቸው እያወቁ የሚያደርጉት መሆኑ ደግሞ ጸጸታቸው ካንጀት መሆኑን እና ይበልጥ የመልካም ሞራል ሰብዕናቸውን ይመሰክራል።

የቀድሞ የህወሃት ጠ/ሚ/ር ታምራት ላይኔ እና ታጋይ ርስቴ መብራቴ እንደየድርሻቸው በሃገራቸው ላይ በደል አድርሰዋል። የቅርቧን የወ/ሮ ርስቴን ጸጸት እና በዝርዝር ላደረሰችው በደል በአደባባይ ኢሳት ላይ ወጥታ ይቅርታ መጠየቋ እና የህወሃቶችን ማንነት ማጋለጧ ራሱ ትልቅ አስተዋጻኦ ሆኖ፣ ከአሁን በኋላም በተቻላት ሁሉ ለአገሯ ነጻነት እንደምትሰራ መናገሯ ትልቅ አርዓያነት ነው። ታምራት እና ርስቴ እንደማንኛውም አሰርቶቹ ውስጥ ያሉ የወቅቱ ወጣቶች፣ ለሃገራዊ እና ህዝባዊ ጥቅም ብለው ያደረጉት እንደሆነ እርግጥ ነው። ርስቴ ከመሰረቱ በህወሃት ርዕዩት በመማለሏ እና በማመኗ ያደረገችው ከመሆኑ በቀር፣ በህወሃት ቆይታዋ፣ አገር እና ህዝብ በሚጎዳ መልኩ አድርጋዋለች/ተናግራዋለች ተብሎ የሚጠቀስ ብዙም የጎላ ታሪክ የላትም። ታምራት ላይኔም ይቅርታ መጠየቁን የሰማሁ መስሎኛል። ግን በዝርዝር ምን በደል አድርሷል?

የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ለገባበት አበሳ እና መከራ ትልቅ ሚና የተጫወተን ሰው፣ ስልጣን ላይ በነበረበት ግዜ እና በኋላም፣ በተለይ  በአማራ እና ኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን መካከል ትልቅ ጥላቻ ፈጥሮ፣ እንዲያውም እርስ በርስ እንዲተላለቅ በአደባባይ የተናገረውን የቀድሞውን ጠ/ሚ/ር፣ ስለ አገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ምክር ከመጠየቅ በፊት፤ እውነት “እነዚህን ነፍጠኞች በሏቸው!” የማለቱን እና በአደባባይ የመናገሩን ነገር ቃል በቃል አንስቶ ማለት አለማለቱን መጠየቅ እና የሚለውን መስማት ሲኖርበት፣ የSBSሱ ጋዜጠኛ እንደ

አማካሪ ምክር መጠየቁ አግባብ አይደለም። እውነት ለመናገር ታምራት እውነትም ተናግሮት ከሆነ (እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የተጻፈበት እና የተነገረ በመሆኑ አልተናገረም አይባልም፣ ማረጋገጫ ባይኖረኝም፣ እኔ የSBSን ጋዜጠኛ ብሆን ኖሮ፣ ወይ ከየትም አፈላልጌ ለማግኘት እሞክራለሁ፣ አለዚያም በተለያዩ ሜዲያዎች የተጻፉ በርካታ ስነጽሁፎች ስላሉ እሱን መሰረት አድርጌ እጠይቀዋለሁ) ወንጀለኛን እንደማበረታታት ይቆጠራል። (ታምራት ላይኔ በስልጣኑ ዘመን ተናገረ ተብሎ የሚነገርለትን የ“እነዚህን ነፍጠኞች በሏቸው….” ንግግር ቅጂ ያላችሁ፣ ወይም ያያችሁ እባካችሁ ኮፒውን ለጥፉልን)።

በተረፈ፣ ታምራት ላይኔ በሃገር ላይ በተለይም በአማራው ላይ አደረሰው ለተባለው በደል፣ በ2013 ዓም SBS ጋዜጠኛ ራሱ ግለሰቡን ቃለ መጠይቅ ካደረገ በኋላ የተሰጡትን እና ከቃለ መጠይቁ ስር የተኮለኮሉትን የአድማጭ አስተያየቶች መሰረት አድርጎ፣ “….እውን …. ይህን ብለሃል? ወይስ አላልክም…?” ብሎ መጠየቅ ይችል ነበር።

በመሰረቱ ታምራት ላይኔ ለምን ቃለ-መጠይቅ ተደረገለት የሚል አቋም የለኝም። አዶልፍ ሂልተር አርጀንቲና ማዶ አማዞን ጫካ ውስጥ ራሱን ለውጦ ሲኖር ኖሮ በ110 አመቱ በህይወት ተገኘ ቢባል፣ የመጀመሪያው ለመሆን እየተሰባበረ ጫካውን የሚያቆራርጠው ጋዜጠኛ ብዛት ይታየኛል። ነገርግን ጋዜጠኛ ከይሉንታ ወጥቶ መጠየቅ የሚገባውን መጠየቅ እና፣ በቃለ መጠይቅ ተደራጊው አይምሮ ውስጥ ያለውን ሁሉ ለማውጣት መቻል ያስፈልጋል። ለምሳሌ የትራምፕ እና ክሊንተንን የቀድሞ ጥሩም ሆነ መጥፎ ድርጊቶች እና ንግግሮች እየጎለጎሉ ከሚያወጡት ጋዜጠኞች መማር ያለባቸው ይመስለኛል።

SBS በታምራት ላይኔ ላይ ያባከነውን የአየር ጊዜ፣ ሌሎች ባለሙያዎችን እና ምሁራንን በማቅረብ፣ አለዚያም እንደ የኔሰው ገብሬ የመሳሰሉትን እና መስዋዕትነትን የከፈሉ ዜጎችን ቤተሰቦች በማቅረብ፣ በህወሃት እየተናደ ያለውን ብሄራዊ አንድነት እና ህዝባዊ የሞራል መሰረት በመገንባት ላይ ባዋለው በተሻለ ነበር።

እንደ ታምራት ላይኔ ያሉትን ሰዎች አስሰልፎ፣ በሰብዓዊነት እየቀለደ እና ከሞራል አንጻር እጅግ እየወረደ እና እኛንም እንደ ህዝብ እያወረደን ያለውን ህወሃትን ያገለገሉትን፤ ላደረሱት በደል እንኳን ከልብ መጸጸታቸውን ለመናገር የሞራል መሰረት የሌላቸውን ሰዎች ዛሬም የፖለቲካ አማካሪ አድርጎ ማቅረብ፣  የየኔሰው ገብሬን መስዋዕትነት “… የአይምሮ በሽተኛ ስለሆነ ራሱን አቃጥሎ ገደለ…” በሚል በህዝብ የሞራል መሰረት ላይ እየቀለደ ያለውን ህወሃትን ሽልማት እንደመስጠት ይቆጠራል።

ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሃፋቸው ያሰፈሩትን ላሳጥረው እና ዛሬም፡ “አርበኞች አንገት እየደፉ፣ ባንዳዎች ደረት እንዲነፉ…” እንዳናደርግ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ለማንኛውም አንባቢዬ በታምራት ላይኔ ቃለ-መጠይቅ ላይ ተነስተው የሰጡትን እንደ “…እርሶ [ታምራት ላይኔ] የዘሩት ነው አሁን የሚታጨደው፤ ኦጋዴንና አርባጉጉ ያሉትን [የተናገሩትን] [እኛ] የገፈቱ ቀማሾች አንረሳውም በተለይ አሩሲ ላይ መሰል አስተያየት ማንበብ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Scroll To Top